Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  አዳማጭ ጠፋ እንጂ ተናግረን ነበረ!

  ሰላም! ሰላም! አንዱ ሰሞኑን በእግር በፈረስ ሲፈልገኝ እንደነበር ነግሮኝ፣ አንድ ታዋቂ ፖለቲከኛ በትዊተር ገጻቸው ያስተላለፉትን መልዕክት አንብብ ብሎ ስልኩን አፍንጫዬ ሥር ደቀነው፡፡ ዓይኖቼን በልጠጥ አድርጌ፣ ‹‹ከደርግ ተማሩ አልናቸው እንቢ አሉ፣ ከሳዳም ሁሴን ተማሩ ከጉድጓድ ውስጥ ተጎትታችሁ እንዳትወጡ ተባሉ አንሰማም አሉ፣ ከጋዳፊ ተማሩ በየገደሉ ሥር እንዳትጎተቱ ተባሉ ጆሮ ዳባ ልበስ አሉና ዛሬ እየተጎተቱ ይመጧት ጀመር፡፡ እኛስ ተረኞቹ ከእነሱ እንማር ይሆን?›› ይላል በአጭር የተሰደረው ግን ቆንጣጭ ጽሑፋቸው፡፡ ይህ መልዕክት ከዚህ ቀደም በተለያዩ መንገዶች ሲነገር መስማቴን አስታውሳለሁ፡፡ እኔም ራሴ ምናለበት እነዚህ ሰዎችና ተከታዮቻቸው አርቀው ቢያስቡ ብዬም መናገሬን አልዘነጋም፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ግን እንዲህ እንዳለኝም አይረሳኝም፡፡ ‹‹አንበርብር! እነዚህ ሰዎች እኮ ወይ ፈጣሪን አያውቁ፣ ወይ ሕገ ልቦና የላቸው፣ የሚነገራቸውን ለማዳመጥ ፈቃደኛ አይደሉ፣ እንዲያው በአጠቃላይ ልባቸው ተደፍኖ የፈጣሪን ቁጣና የሕዝባችንን ዱላ የሚጠብቁ ይመስለኛል…›› ነበር ያለው፡፡ እኔ በበኩሌ ይህ ሁሉ ምክርና ማሳሰቢያ ከበቂ በላይ ነው ባይ ነኝ፡፡ አልበዛም እንዴ!

  ወገኖቼ! እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖትና ውድ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ላለፉት ሃያ ዓመታት በላይ በትዳር ስንኖር፣ ከምንም ነገር በላይ የፈጣሪያችንን ትዕዛዛት ለማክበርና ህሊናችን ንፁህ እንዲሆን የቻልነውን ያህል እንታገላለን፡፡ አንዳንዴ አለመግባባት በመሀላችን ቢፈጠር እንኳ ከጊዜያዊ ኩርፊያ በላይ ርቀን ሳንሄድ፣ ያላግባባንን ጉዳይ በፅሞና ተነጋግረን እንፈታዋለን፡፡ ለጎረቤትና ለወዳጅ ዘመድ ስሞታ ሳናቀርብ እንደ አገር የምናየውን ትዳራችንን እንንከባከበዋለን፡፡ ምክንያቱም ትዳርን ሳያፀኑ አገሬ እያሉ ማቅራራት ተራራ ውሸት ስለሆነ ነው፡፡ እናም እኛ ከአንደኛ ደረጃ በላይ ባልዘለቀው ትምህርታችን ይህንን ያህል ማሰብ ከቻልን፣ ኮሌጅ ደጋግመው በመበጠስ ዲግሪዎችን በየዓይነቱ የጫኑት ምን ነካቸው እንላለን፡፡ ለነፃነት ታግለናል ያሉት ነፃነትን ደፍጥጠው ወገን አሰቃይተው፣ አገር አተራምሰውና መጠኑ የማይታወቅ የአገር ሀብት ከዘረፉ በኋላ አርፈው ተቀመጡ ቢባሉ አልሰማ አሉ፡፡ ጭራሽ አገር ለማፍረስ ጦርነት አስነስተው በውርደት ፍፃሜያቸውን አጣደፉት፡፡ አሁን ዋናው ቁምነገር ይህ ክስተት እኛን ጭምር ካላስተማረ ምን ልንማር ይሆን እላለሁ፡፡ ነግ በእኔ ነውና!

  ዕውቀት በዕውቀት ላይ የደራረቡት የጋን ውስጥ መብራት ሲሆኑ፣ ሥልጣን ላይ መቀመጥ የዕውቀት ሁሉ ምንጭ ነው ብለው የሚያስቡ በየሥርቻው ሲፈለፈሉ፣ በድሮ የታጋይነትና የተዋጊነት ወኔ ተቸንክረው የሚነገራቸውን የማይሰሙ ተቸካዮች ሲጃጃሉ፣ የሚጣልላቸውን ድርጎ ብቻ እያሰቡ አገርን ከፍላጎታቸው በላይ ያደረጉ ሲበዙ ያሳዝናል፡፡ ብዙኃኑ ደግሞ በይሉኝታና ወገብን በሚያጎብጥ የኑሮ ውድነት ተጠፍንጎ ድምፁ አይሰማም፡፡ ሥልጣንን ብቻ የሚያልሙ፣ ለአገርና ለሕዝብ ህልውና ደንታ የሌላቸውና ለመልካም ምግባሮች ተቃራኒ የሆኑ እንዳይበዙ ሲባል ነው ካለፉት መጥፎ ድርጊቶች እንማር የሚባለው፡፡ እናማ ተማርኩ አወቅኩ የሚለው ደግሞ ባሰ። በቀደም ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ቁጭ ብለን አንድ ካፌ ውስጥ ሆነን፣ አንዱ ድንገት ደርሶ፣ ‹‹ሰው አለው?›› አለን። ወንበሩን መሆኑ ነው። ‹‹የለውም ውሰደው…›› አለው የባሻዬ ልጅ፡፡ ከዚያ ገና ሳይቀመጥ፣ ‹‹ለነገሩ ዘንድሮ ወንበር ፈላጊ ብቻ እንጂ ለአገር የሚያስብ ምን ሰው አለው ብላችሁ ነው?›› ብሎ ጀመረላችኋ። እንኳን ይህችን የዝንብ ጠንጋራ ቀርቶ የዝንብ ወፈፌም እናውቃለን ብዬ በልቤ፣ ‹‹ቢል ታመጣልን?›› አልኩት አስተናጋጁን። ‹‹ካፊያው ያባራ እንጂ ቆይ…›› ሲለኝ የባሻዬ ልጅ ነገረኛ አሁንም ሳይፈቀድለት፣ ‹‹አዬ እንጃ የዘንድሮ ካፊያስ እንዳያያዙ ከሆነ የሚያባራ አይመስለኝም…›› ብሎ ብቻውን ሳቀ። አሳሳቁ ታዲያ ቲፎዞ ፍለጋ ስለሚመስል ነገረ ሥራው አላማረኝም፡፡ ያዋከቡት ነገር መልካም አይደለም!

  መቼስ አንዳንዴ ስሜታዊ እየሆንኩ ጨዋታዬ እንደ ዘመኑ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች ድርቅ ይላል አይደል። ምንላድርግ ቀልድ ጠፋ። ማለቴ ቀልዱ ሁሉ ያው እንደምታዩት የምር የምንኖረው ኑሮ ሆኗል። ቀልድ አሯሯጫችን መሆኑ ቀርቷል። እንደ ሳይንስ ፊክሽን ማለቴ ነው። የዛሬን አያድርገውና በቀደሙት ዘመናት አሁን በእጃችን የጨበጥናቸው፣ ኪሳችን የከተትናቸው፣ ቆፍረን የቀበርናቸው  ቴክኖሎጂዎችና የጦር መሣሪያዎች ትናንት ተረት ተረት ነበሩ። ቀልድና ሳይንስ ፊክሽን የሚያመሳስላቸው ይኼው ነው። ትናንት ቀልድና ስላቅ እንደ ዛሬው እያንዳንዳችን የሚያጋጥመን የምንኖረው ሀቅ አልነበረም። በአብዛኛው ነው የምላችሁ። ዘመኑ የመረጃና የማስረጃ ነውና ማስረጃዬን ላቅርብ። በቀደም አንድ ቪላ ቤት እያሻሻጥኩ ነበር። የማሻሽጠው ቤት የነበረበት አካባቢ አንድ ቡቲክ ሞቅ አድርጎ በሁለት ሞንታርቦ ሙዚቃ ከፍቷል። መቼም ዘንድሮ ሙዚቃ ቤትና ቡቲክ መለየት ተስኖናል። ይኼኔ ነው  ድንገት ጆሮዬ የገባው። ‹‹ምን? የአይጥ ዱለትና የጄሶ እንጀራ ሲሸጡ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በሁለት ዓመት እስራት ተቀጡ…›› ይላል አንዱ። አሁን ይኼ ታዲያ ቀልድ መሆን አልነበረበትም? ፊክሺን መሆን አልነበረበትም? እንዴት በዚህች ድንቅ ምድር አብሮ መብላት፣ አብሮ መኖር፣ አብሮ መሞት በሚሰበክባት አገር እንዲህ ዓይነት ተፋልሶ እንሰማለን? ግን ተፋልሶ አልነበረም እንዴ? እሱም ኑሮአችን ነው። ብቻዬን በግርምት ፈዝዤ እንደቀረሁ ነው ከአላፊ አግዳሚው ከጽንፍ ጽንፍ የሚወነጨፉ አስተያየቶችን የሰማሁት። መስማት አይሰለቸን!

  አንዱ ድምፁን ጎርነን አድርጎ፣ ‹‹እነሱ በትንሹ እንዲታሰሩ መወሰኑ በከተማው የአይጦች  ቁጥር  መብዛቱንና  የጀሶ  ገበያ  መቀነሱን  ከግምት  በማስገባት  ይሆናል፡፡  ወይም  ለዚህ  አመፀኛ  ሕዝብ  አይጥና  ጀሶ  ሲያንሰው  ይሆናል  ተብሎም  ሊሆን  ይችላል…›› ሲል ሌላው፣ ‹‹ሁልሽም በወረፋ በልተሽ አሁን እንትፍ እንትፍ  ትያለሽ። አጣርተሽ አትበይም?›› እያለ ይሸልላል። በጣም ያስደነገጠኝ ግን ሦስተኛው አልፎ ሂያጅ ነው፡፡ ‹‹ዘራቸው ይጣራልን ሲል አልሰማሁም መሰላችሁ?›› ይላል፡፡ ለዚህ ነው ቀልድ የጠፋብን ጎበዝ። ቀልደኞች በበዙበት ዘመን እንዴት ቀልድ የለም ትላለህ እያሉ የሚሞግቱኝ ደላላ ወዳጆቼ ናቸው፡፡ አንደኛው ደላላ፣ ‹‹አንበርብር አይጥ ከድመት እንዴት መደበቅ እንደምትችል አሳምረን እናውቃለን ብለው ጉድጓድ ውስጥ ቢደበቁም፣ ያገኛቸው ድመት ሳይሆን ቆፍጣና ወታደር መሆኑን ባወቁ ጊዜ እጃቸውን አንከርፍፈው ሰጡ ተብሎ ተቀለደ እኮ…›› እያለ ሲስቅ፣ እኔም አብሬው ሳቅኩኝ፡፡ ቁልቁል ማሰብና ቁልቁል ማደግ!

  ያሻሻጥኩት ቪላ ኮሚሽን ተቀብዬ ወደ ቤቴ ስጣደፍ ብሄድ ማንጠግቦሽ ቤቱ እንደተዝረከረከ ለጥ ብላ ተኝታለች። ሰዓቴን ሳይ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ይላል። እንግዲህ ተመልከቱ ይኼን እያየ እየሰማ ራሱ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚጠራጠር አለ? ለነገሩ የእኛ እንቅልፍ በዕድገት የሚረዝም በረሃብ የሚያጥር አይደለም፡፡ እሱ በጥበቡ ሲሠራን በተፈጥሯችን ተኙ ብሎ ፈጥሮናል። ባሻዬ ይኼን አስተሳሰቤን ስለሚጋሩኝ፣ ‹‹የእኛ ጠላታችን ከድህነት ጎን ለጎን የሚቀሰቅሰን ብቻ ነው…›› ይሉኛል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ቀስቃሽ በአየቅጣጫው አለ፡፡ በአቋራጭ ለመክበር የሚጣደፈው ታይቶ የማይታወቅ ሩጫ ሲያበዛ ታዩና ስትደነቁ፣ ላቡን ጠብ አድርጎ የሚሠራውን ግን ከእነ መፈጠሩም ትረሳላችሁ፡፡ አንድ ደንበኛዬን ሲኖትራክ ላጋዛው ወደ ለቡ አካባቢ ሄደን ነበር፡፡ ከሻጩ ጋር ተገናኝተው ከስንት ውጣ ውረድ የበዛበት ድርድር በኋላ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ሻጭ ደንበኛዬንና እኔን ምሳ ልጋብዛችሁ ብሎን አንድ ዘመናዊ ልኳንዳ ይዞን ሄደ፡፡ ልኳንዳ ሳይሆን የላስ ቬጋስ ካዚኖ ቤት የመሰለ ትልቅ ሕንፃ አከል ቪላ ስንገባ የእኛ ሰው ይህንን ጥሬ ሥጋ ይዞታል፡፡ ምሳ ሳይሆን የአንበሶች ልደት የሚከበር ነው የመሰለኝ፡፡ በዚህ ላይ በየጠረጴዛው ጎልድ ውስኪና ዊንተር ፓላስ ቮድካ በብዛት ይታዩኛል፡፡ ዓይን አዋጅ ሆነብኝ!

  በአስተናጋጁ መሪነት ለየት ያለ ቦታ (ቪአይፒ ይሉታል) ተወስደን አንድ መለስተኛ ጠረጴዛ ዙሪያ ተኮለኮልን፡፡ ጋባዣችን የቤቱን ባለቤት አስጠርቶ የበሬ ብልቶችን ዘርዝሮ ሁለት ኪሎ ሥጋ አዘዘ፡፡ የምትጠጡት ሲባል ጎልድ ውስኪ ተባለ፡፡ ሥራ ስላለብን ውኃ ወይም አምቦ ውኃ ይበቃል ቢባልም፣ አንድ ሁለት መለኪያም ቢሆን ሳትቀምሱ አትሄዱም ተብለን ጠርሙስ ሙሉ መጥቶ መሀላችን ጉብ አለ፡፡ የዚህ አካባቢ ባህል ነው መሰል በሥራ ሰዓት ሁሉም ማለት ይቻላል ጥሬውንና ክትፎውን በልቶ የወይን ድብልቅ፣ ውስኪና ቮድካ ያንቆረቁራል፡፡ ጋባዣችንን ይህ ነገር እንዴት ነው ብዬ ስጠይቀው፣ በአብዛኛው የመሬት ደላሎች እንደሆኑና ጊዜያቸውን በዚህ ሁኔታ እንደሚያሳልፉ ሲነግረኝ ደነገጥኩ፡፡ እኔ የገና ሰሞን ሥጋ ከበላሁ ምናልባት ለፋሲካ ይሆናል ጠግቦ ለመብላት የማገኘው፡፡ እናላችሁ የዘመናችን ደላሎች የአገር መሬት እያስወረሩና እያስቸረቸሩ በቅንጦት ላይ ናቸው ለማለት ነው፡፡ ለመሆኑ የእኛ ሰው ደላላ ይሁን ባለሥልጣን ወይም ባለሀብት ከታሪክ ባይማር፣ ሲነገረው ባይገባው፣ ሲጨቀጭቁት ቢደክመው እንዴት እየሆነ ካለው ነገር መማር ያቅተዋል? ተው በልክ አድርጉት!

  በሉ ልንሰነባበት ነው። ብቻየሕይወት ለውጥየሚባል አባባል እንዲህ በትንሽ ትልቁ አፍ መግነኑ ግርም እያለኝ፣ ‹‹ሰው ከሰውነት ወርዶ ወደ ሌላ ፍጡርነት ተቀይሯል እንዴ?›› ብዬ ሳልጨርስ ውዷ ማንጠግቦሽ ትዝ አለችኝ። አስተኛኘቷ ደስ አላለኝም። ከመጮኼ በፊት አንዴ ልሞክራት ብዬ ነካ አደርጋታለሁ፣ ‹‹የቀሰቀሷቸውን ደንበኛ አሁን መነሳት አይችሉም፣ እባክዎ ከሰዓታት በኋላ እንደገና ይሞክሩ…›› ብለኝ ተገላብጣ ተኛች። ደህና ከሆንሽስ ብዬ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ተያይዘን ወደ ግሮሰሪያችን አመራን። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ የማንጠግቦሽን ኩመካ ሰምቶ ሲያበቃ፣ ‹‹አንዳንዱ እንቅልፍ እኮ ለበጎ ነው አንበርብር። ባንነቃ ባንቀሰቀስ የሚሻለን ጊዜ  አለ። ሰሚ የለም እንጂ…››  ሲለኝ፣ ‹‹አንዳንዴ ሳምንቱ ቅጣቱ ሲከብድ፣ ምንም አይሳካም ከእሑድ እስከ እሑድ…›› ብሎ አንዱ በአንድ ወቅት ያጨደው መከራ ትዝ አለኝ። በአንድ ወቅት አንድ ትልቅ ሰው፣ እንደነገሩን በረባ ባልረባው አቧራ ማስጨሱን ትተን አሻራችንን የሚያስቀርልን መልካም ነገር ላይ እንሰማራ፡፡ መነጋገር፣ መደማመጥና የተሻለ ጊዜ እንዲመጣ መመካከር ያስፈልገናል፡፡ የትናንቱን ጉልበተኛ አወዳደቅ ሰምተንና አዳንቀን እኛም እዚያው ውስጥ ከተገኘን ፋይዳም አይኖረንም፡፡ ከዚህ ቀደም እነ ማን ምን ተመከሩ፣ ለምንስ አናዳምጥም አሉ፣ ከዚያስ ምን ደረሰባቸው፣ ወዘተ እያልን ስንመረምር መልሱ በጣም ቅርብ ነው፡፡ አዳማጭ የለም እንጂ ተናግረን ነበረ ብለን ዕድሜ ልክ መጮህ አለብን እንዴ? መልካም ሰንበት!

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት