Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊእናቶችን የሚነጥቀው ደም መፍሰስ

እናቶችን የሚነጥቀው ደም መፍሰስ

ቀን:

ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ደም መፍሰስ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ እናቶችን ለሞት ይዳርጋል፡፡ የደም መፍሰሱ ከወሊድ በፊት፣ በምጥ ጊዜና ከወሊድ በኋላ የሚከሰት በመሆኑ፣ በእነዚህ መጥፎ አጋጣሚዎች አልፈው በሕይወት የተወለዱ ልጆችን ካለእናት የሚያስቀርም ነው፡፡ የጤናማ እናትነት አለመኖር ቤተሰብን የሚበትን፣ አሊያም ለችግር የሚያጋልጥም ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት ረጂ ድርጅቶችና የጤናው ዘርፍ ተዋናዮች እናቶች በተለይ በእርግዝና ወቅት የሐኪም ክትትል እንዲያደርጉ የሚመክሩት፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያም ሆነ በተለይ በደሃና በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ እናቶች ወደ ጤና ተቋም ከመዝለቅ ይልቅ ቤት ውስጥ መውለድን ይመርጣሉ፡፡ የባህሉና የአኗኗሩ ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ፣ የጤናው ተደራሽነት አለመረጋገጥም ለዚህ አስተዋጽኦ አለው፡፡

ይህንን ለመቀልበስ ከዓመታት በፊት ጀምሮ እናቶችና ሕፃናት ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱ እስከ ወረዳ በመድረስ እየሠሩ የሚገኙት ጤና ሚኒስቴርና በሥሩ ያሉ ተቋማት እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት ማምጣቱ ላይ የተሠራው ሥራ ውጤት እያስገኘ ቢሆንም፣ ዛሬም ወደ ጤና ተቋም የማይመጡ እናቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ እናቶች እየሞቱበት ያለው ከእርግዝና ጋር የተያያዘው ደም መፍሰስ ደግሞ በሕክምና ክትትል መቆጣጠር የሚቻል ነው፡፡  

ሆኖም ከወሊድ ጋር ተያይዞ በሚከሰቱት ችግሮች ሳቢያ እናት ለስቃይና ለሕልፈተ ሕይወት ትዳረጋለች፡፡

‹‹በደም መፍሰስ ምክንያት እናት ለምን ትሙት›› በሚል መሪ ቃል ለአንድ ወር የሚካሄደው 15ኛው ዙር ‹‹የጤናማ እናትነት ወር ዘመቻ›› ዘመቻው ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. መጀመሩን በይፋ ያስታወቁት ደረጀ ድጉሜ (ዶ/ር) የጤና ሚኒስትር ዴኤታ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት 3.3 ሚሊዮን እናቶች እንደሚያረግዙ ጠቁመዋል፡፡

እርግዝና ተፈጥሯዊና በራሱ አስደሳች ቢሆንም የሕክምና ድጋፍ፣ እንክብካቤና ክትትል ካልታከለበት ደስታው ቅፅበታዊ ይሆንና ከደም መፍሰስ ጋር በተያያዘ እናቲቱም ሆነ ሕፃኑ ለከፋ ጉዳት ይዳርጋል፣ ጉዳቱም ሞትን የሚጨምር ነው ብለዋል፡፡

የአንድ እናት ሕልፈተ ሕይወት ለጨቅላ ሕፃኑ ብቻ ሳይሆን ለመላው ቤተሰብ ችግር ሆኖ እንደሚቀጥል፣ ከዚህ አኳያ እናትነትን መንከባከብ ቤተሰብን፣ ብሎም አገርን መንከባከብ ነው ቢባል ማሳነስ ይሆናል እንጂ ማጋነን እንዳልሆነ የገለጹት ዶ/ር ደረጀ፣ የጤናማ እናትነት ወር ዓላማ ለእናቶች እንክብካቤና ጥበቃ ማድረግ፣ በተለይ እናቶች በእርግዝና ወቅትና በወሊድ ጊዜ ለችግር የሚዳርጉ ሁኔታዎችን ቀድሞ በማወቅና ችግሩን ለመቀነስ እንዲቻል መወሰድ ያለበትን ጥንቃቄ በተመለከተ ለኅብረተሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ መሆኑንም አክለዋል፡፡

‹‹የሞት መጠኑ የመቀነስ አዝማሚያ ቢታይበትም ዛሬም እናቶች በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸው ሲያልፍ ይታያል፡፡ ልብ የሚነካው ለሞት ምክንያት የሆኑት ችግሮች በቀላሉ መከላከልና ማዳን የምንችላቸው መሆናቸው ነው፡፡ ማዳን ከምንችላቸው ችግሮች መካከልም 50 ከመቶ ያህሉ በእርግዝና ወቅት፣ በወሊድ ጊዜና ከወሊድ በኋላ በሚከሰተው የደም መፍሰስ ምክንያት የሚመጣውን ችግር ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመጀመርያ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ማነስ እንዲሁም እናቶች ወደ ጤና ተቋም መጥተው ለመውለድ አለመወሰን፣ ቤት ውስጥ መቆየትን መምረጥ፣ ወደ ጤና ተቋም ለመሄድ ፍላጎት ቢኖራቸውም በመሠረተ ልማቶች ምቹ አለመሆን የተነሳ ቶሎ ወደ ተቋሙ አለመድረስ፣ ዘግይተውም ሆነ በወቅቱ ጤና ተቋም ከደረሱ በኋላ በሕክምና ቁሳቁስ እጥረት፣ ከባለሙያ ሥነ ምግባርና አቅም ማነስ ጋር በተያያዘ ተገቢውን አገልግሎት አለማግኘታቸው ለእናቶች ሕይወት ማለፍ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች የተካተቱ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

ሕይወታቸው ከሚያልፈው እናቶች መካከል አብዛኛዎቹ በወቅቱ ተገቢውን ሕክምና ባለማግኘታቸውና ቤት ለመውለድ ሞክረው ብዙ ደም ከፈሰሳቸውና ከተጎዱ በኋላ ወደ ጤና ተቋም መምጣታቸው መሆኑን ዶ/ር ደረጀ አመላክተው፣ በወቅቱ ጤና ተቋም መድረስ ቢቻል 70 በመቶ የሚሆኑትን እናቶች ከከፋ አደጋና ሞት መታደግ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

የጤናማ እናትነት ወር ዘመቻ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በሁሉም ክልልና በፌዴራል ደረጃ ከጥር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለ30 ቀናት ንቅናቄ የሚደረግበት፣ እናቶቻችንን በአንድ ላይ የምናስታውስበት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ይህ ዓይነቱ ዘመቻ ባለፉት 15 ዓመታት በተለያዩ መርሐ ግብሮችን ተከናውኗል፡፡ በዘመቻው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በእናቶች ጤና ዙሪያ ተገቢውን እንቅስቃሴ በማድረግ ዕገዛና ትብብር አድርገዋል፡፡ መንግሥትም ለጤና ሴክተሩ በተለይ ደግሞ ለእናቶችና ሕፃናት ጤና በርካታ አስተዋጽኦዎችን ያበረከተበት ነበር፡፡

መንግሥት ካበረከታቸው አስተዋጽኦዎች መካከል በተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ ጤና ኬላዎችን፣ ጤና ጣቢያዎችንና ሆስፒታሎችን መሥራቱ፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎችን አሠልጥኖ መመደቡ፣ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀትና አምቡላንሶች በመግዛት በተለይ እናቶች ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የእናቶች ሞትና ስቃይ እንዲቀንስ የሚያስችል ተግባር ማከናወን እንደሚገኝበት ዶ/ር ደረጀ ተናግረዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ካሉ አገሮች የእናትን ሞት በመቀነስ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦችን በማሳካት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ እንዳደረጋት ገልጸዋል፡፡   

የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ ባለፉት ሦስት አሠርታት ውስጥ አሥር በመቶ ያህሉ ነፍሰ ጡሮች ቤት ውስጥ ሲወልዱ፣ በዓመት 30,000 እናቶች ደግሞ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ችግር በተለይም በደም መፍሰስ ምክንያት ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት ወደ ጤና ተቋም የሚሄዱ እናቶች 10 በመቶ ብቻ የነበሩ ሲሆን ይህ አሁን ላይ ተቀይሯል፡፡ በእናቶችና ሕፃነት ጤና አጠባበቅ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት በመሠራቱ በጤና ተቋም የሚወልዱት ወደ 51 በመቶ ከፍ ማለቱን፣ በዓመት ለሕልፈተ ሕይወት የሚዳረጉ እናቶች ቁጥር ደግሞ 14,000 መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በዓለም ለሦስተኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ15ኛ ጊዜ የሚካሄደው የጤናማ እናትነት ወር ዘመቻ ላይ የእናቶች የጤና ጉዳይ የሁሉንም ትኩረት የሚሻ መሆኑን ለማስገንዘብ የመንገዶች መኖር፣ የሴቶች መማር፣ የውሳኔ ሰጪዎች አቅምን ማሳደግ፣ በኢኮኖሚና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ በእናቶችና ጨቅላ ሕፃናት ጤና አጠባበቅ ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ እንዳለው የሚያስገነዝብ፣ የቅስቀሳና የጉትጎታ፣ የማስገንዘቢያና ለተግባራዊነቱም በቅንጅት የታገዘ ሥራ የሚከናወንበት ወር መሆኑን ዶ/ር ሊያ አክለዋል፡፡

በሁሉም የኢትዮጵያ ሥፍራዎች የእናቶችና የሕፃናት ጤና አገልግሎት በነፃ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህ ዓይነቱን አገልግሎት ቀጣይነትና ጥራቱ በይበልጥ የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ እንዲቻል ለዘርፉ የተመደበው በጀት እየጨመረ መሄድ እንዳለበት፣ የአገልግሎት አሰጣጡም አክብሮት፣ ርኅራኄና እንክብካቤ የተሞላበት ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት እንዳይመጡ ከሚያደርጉዋቸው ምክንያቶች መካከል በየጤና ተቋማት የሚታይ አቀባበል፣ ርኅራኄና እንክብካቤ የተፈለገውን ያህል ሆኖ ባለመገኘቱ የተነሳ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓይነቱ አካሄድ ላይ የማሻሻያ ሥራ ማከናወን፣ በየጤና ተቋማቱ ውስጥም ሆነ ውጪ ማቆያዎችን ማዘጋጀት፣ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ፣ በዚህ ዓይነቱ ዕቅድ ላይ የሚንፀባረቁትንና አላስፈላጊ አመለካከቶችንና አጉል ልማድ ለማስወገድ የሚረዳ ግንዛቤ የማስጨበጡ ሥራ በጤናማ እናትነት ወር ዘመቻ ላይ ተጠናክሮ መከናወን እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...