የቆላና የአርብቶ አደር አካባቢዎችን የተመለከቱ ፖሊሲዎች ሲዘጋጁ፣ እኔ አውቅልሃለሁ ከሚል አስተሳሰብ ወጥቶ ኅብረተሰቡ ለራሱ ያውቃል ከሚለው መነሳት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዲስ ወግ ‹‹አንድ ጉዳይ›› በሚል የቆላና አርብቶ አደር አካባቢዎችን ልማት የተመለከተ ውይይት ሐሙስ ጥር 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲደረግ፣ በመድረኩ መወያያ ሐሳብ ካቀረቡ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በአማካሪነት የሚሠሩት ወ/ሮ ሐኒ ሀሰን እንዳስገነዘቡት፣ የአርብቶ አደሩን አካባቢ በተመለከተ የሚሠሩ ፖሊሲዎችና የሚዘጋጁ ዕቅዶች አርብቶ አደሩን የመረዳት ጉድለቶች እንዳሉበት ተናግረዋል፡፡
በዚህም ምክንያት በተለያዩ ሁኔታዎች አርብቶ አደሩ ያለውን ሀብት በአግባቡ የማይጠቀምና ‹‹የከብት ጭራ ተከትሎ የሚዞር›› እንደሆነ እንዲሁም በአገሪቱ ያለው አርብቶ አደር በሙሉ አንድ እንደሆነ፣ ተደርጎ እንደሚታሰብና ይኼም ስህተት እንደሆነ ወ/ሮ ሐኒ አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ያለው ሀብት ውስን ቢሆንም ባለው ውስን ሀብት የተሠሩ ሥራዎች ግን ከፍተኛ ውጤት እንዳስገኙ ያስታወቁት አማካሪዋ፣ የትኛውም ዓይነት ፖሊሲ ሲሠራ ግን አርብቶ አደሩ ላይ የሚያሳድረውን በጎም ሆነ በጎ ያልሆነ ተፅዕኖ በመቃኘት መሆን አለበት ብለዋል፡፡ ይኼም አርብቶ አደሩን ከመረዳት እንደሚጀምርና ለምን እንደሚንቀሳቀስና ያለውን ሀብት እንዴት እደሚጠቀመው ለማወቅ መጣር ጠንካራ የፖሊሲ ግብዓት ይሆናል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባፈም አርብቶ አደሩን በቴክኖሎጂ ማገዝና የኑሮ ዘይቤውን በተረዳ መንገድ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ማድረግ ግድ እንደሚልም አስገንዝበዋል፡፡
የሶማሌ ክልል መስኖ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱረህማን ኢድታሒር በበኩላቸው፣ ካሁን ቀደም አርብቶ አደሩን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች ሲሠሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተካሄደውን ውይይት መሰል ውይይቶች ባለመኖራቸው፣ ስኬታቸውም በዛው ልክ ውሱን እንደነበረ በማውሳት፣ 15 በመቶ የአገሪቱን ሕዝብ ብዛት ይዘውና 15 በመቶ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት እየሸፈኑ፣ እንዲሁም ከቁም እንስሳት ወጪ ንግድ 95 በመቶ የሚሆነውን እያስገኙ ሳሉ፣ ይኼንን መሰል ትኩረት ሳያገኙ መቆየታቸው አግባብ እንዳልነበረ አውስተዋል፡፡
የአርብቶ አደር አካባቢዎችን የተመለከተ ፖሊሲ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀረፀው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንደነበር፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ያለው የፖሊሲ አቅጣጫ ሰፈራና በመንደር ማሰባሰብ ላይ ያተኮረ እንደሆነ በማስታወስም፣ ለማስተዳደር ምቹ አይደለም በሚል ዕሳቤ ችግሩ እንደቆየ ይናገራሉ፡፡ አሁንም ድረስ የአርብቶ አደሮች ጉዳይ ለምን በሰላም ሚኒስቴር ሥር ሆነ? ለምንስ በግብርና ሚኒስቴር ሥር አልሆነም? ሲሉ በመጠየቅ የአስተሳሰብና የአረዳድ ለውጥ እንዳልመጣ በመውቀስ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ሳቢያ የሚዘጋጁ ፖሊሲዎች ከአርብቶ አደሮች ሁኔታ ጋር የተናበቡ አይደሉም ብለዋል፡፡
ይሁንና ባለፉት 15 ዓመታት የእንስሳት በሽታን በመከላከል ረገድ የተሠሩ ሥራዎች፣ በአማራጭ ከአርብቶ አደሩ መካከል በማስተማር አብሮ እየተጓዘ ትምህርት እንዳይቋረጥ የሚያደርግ የትምህርት ሥርዓት መዘርጋቱ መልካም ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የእንስሳት መኖ በአማራጭ ተመርቶ እንዲከማችና የሚከሰቱ ድርቆች ጉዳት ሳያደርሱ በቶሎ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን አውስተዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መንግሥት ለ15 ዓመታት የቆየውን የግብርና ፖሊሲ እየከለሰ ነው በማለት፣ ከአርብቶ አደሩ ልማት ጋር የተገናኘ ለውጥ የዚህ ክለሳ አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡
ካሁን ቀደም የአካባቢ ጥበቃን ያላገናዘቡና በአርብቶ አደሩ አካባቢ ትልልቅ እርሻዎችን ማስፋፋት አንዱ ትኩረት እንደነበረ በመግለጽ፣ አሁን ግን አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የእርሻ ሥራዎች በፖሊሲው ተከልሰው እንዲካተቱ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ነገር ግን ሁሉም የአርብቶ አደር አካባቢ ወደ አርሶ አደርነት ይቀየራል ማለት እንደልሆነ በመግለጽ፣ ቢነኩ በዘላቂነት ሊቆዩ የማይችሉ አካባቢዎች እንዳይነኩ ይደረጋል ሲሉ አክለዋል፡፡
በፋይናንስና በገበያ ትስስር ረገድም ለውጦች እንደሚኖሩ በመናገር፣ አዲስ የፀደቀው በተንቀሳቃሽ ንብረቶች ተያዥነት ብድር ማግኘት የሚቻልበት አዋጅ ለአርብቶ አደር አካባቢዎች ትልቅ ዕድል እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የግብርና ባንክ የማቋቋም የፖሊሲ አቅጣጫ መያዙን ጠቁመዋል፡፡