Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ያለ ገደብ እንዲንቀሳቀሱ ካልተፈቀደ የበጀት ድጎማ እንደማይለቀቅ የአውሮፓ ኅብረት...

የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ያለ ገደብ እንዲንቀሳቀሱ ካልተፈቀደ የበጀት ድጎማ እንደማይለቀቅ የአውሮፓ ኅብረት አስታወቀ

ቀን:

‹‹የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ግጭት ስለመሳተፋቸው መረጃ ደርሶናል››

የኅብረቱ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል

የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ያለ ገደብ እንዲንቀሳቀሱ እስካልተፈቀደ ድረስ፣ ለኢትዮጵያ ያፀደቀው የበጀት ድጎማ እንደማይለቀቅ አስታወቀ።

የኅብረቱ ምክትል ኮሚሽነርና የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ  ጆሴፍ ቦሬል በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ቀውስ መባባስ የአውሮፓ ኅብረትን በእጅጉ እንደሚያሳስበው፣ በዚህ ጉዳይ ላይም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በስልክ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

በውይይታቸው ወቅትም በትግራይ ክልል ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ኅብረቱን እንደሚያሳስበው ለአቶ ደመቀ እንደገለጹላቸው የጠቆሙት ኃላፊው፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ያለ ምንም ገደብ እንዲንቀሳቀሱ ሊፈቀድ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ዓርብ ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. አስታውቀዋል።

‹‹ይህ የአውሮፓ ኅብረት ጥያቄ አይደለም፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ሕግ የተደነገገ የመንግሥታት ግዴታ ነው፤›› ሲሉም በትዊተር ገጻቸው አመልክተዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ለኢትዮጵያ መንግሥት ግልጽ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የተናገሩት ጆሴፍ ቦሬል የአውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያን ለመርዳት ዝግጁ እንደሆነ፣ ነገር ግን ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ገደብ ሳይጣልባቸው በተሟላ ሁኔታ በትግራይ ክልል እንዲንቀሳቀሱ ካልቀደላቸው ኅብረቱ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ እንደማይለቅ ገልጸዋል። የአውሮፓ ኅብረት ያገደው የበጀት ድጎማ 80 ሚሊዮን ዩሮ እንደሆነ፣ ነገር ግን በጥቅሉ 500 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጉ ሌሎች የልማት ዕርዳታዎችና ድጋፎች የሚቀጥሉ መሆናቸውን ታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ባለፈው ማክሰኞ ታኅሳስ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል ጋር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በስልክ መምከራቸውን አረጋግጠዋል።

በውይይቱ ወቅትም በወቅታዊው የትግራይ ክልል ሰብዓዊ ሁኔታ ላይ ሐሳብ መለዋወጣቸውን ያስረዱት ዲና (አምባሳደር)፣ በትግራይ ክልል ዕርዳታ አቅርቦት  ክላስተርን መሠረት ባደረገ የማስተባበር ዘዴ እየተተገበረ ስለመሆኑ እንዳስረዷቸው ተናግረዋል።

የፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ሥራዎች ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን አቶ ደመቀ ለከፍተኛ ተወካዩ እንዳብራሩም ዲና (አምባሳደር) ገልጸዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካዩ ጆሴፍ ቦሬል ከአቶ ደመቀ ጋር ካደረጉት ውይይ በኋላ፣ ባለፈው ዓርብ በሰጡት አስተያየት በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በላይ እንደሆነ ገልጸዋል።

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ያለውን ሁኔታ ውስጣዊ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንደሆነ ቢገልጽም፣ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከዚያ ያለፈ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ለአውሮፓ ኅብረት እየደረሱት ነው፤›› ሲሉ ቦሬል በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።

በትግራይ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች፣ ግድያዎች፣ ዝርፊያዎችና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እየተፈጸሙ ስለመሆኑ የሚጠቁሙ መረጃዎች ለኅብረቱ እንደደረሱት የገለጹት ኃላፊው ስደተኞችን በኃይል የመመለስ ተግባራት፣ እንዲሁም የጦር ወንጀል ሳይፈጸም እንዳልቀረ የሚያመለክቱ መረጃዎች ለኅብረቱ መላካቻውን ገልጸዋል።

ከሁለት ሚሊየን በላይ የትግራይ ነዋሪዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን የገለጹት ቦሬል፣ የክልሉ ነዋሪዎች በዚህ ሁኔታና አስቸኳይ ዕርዳታ በሚያስፈልጋቸው ወቅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች በአካባቢው በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ መደረጉን አውግዘዋል።

በትግራይ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለሚገኙ አገሮችም ሥጋት መደቀኑን የተናገሩት ኃላፊው፣ ለዚህ እንደ ማሳያ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ በመሳተፋቸው ኢትዮጵያ በሶማሊያ ይገኝ የነበረውን ሰላም አስከባሪ ጦሯን ማውጣቷንና በትግራይ ግጭት ምክንያት 55,000 ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

‹‹የአካባቢው አገሮችን በውስጥ ጉዳይ እንዲሳተፉ ማድረግም ሆነ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ሰለባ እንዲሆኑ ማድረግ፣ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ቀጥተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ያመጣል፤›› ሲሉም ተናግረዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ የሰሜን ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል በላይ ሥዩም ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ ከመቀሌ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መዝለቅ ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄየውጭ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሊዘልቁ የቻሉበት ምክንያት የሕወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቀት በመፈጸሙ እንደሆነ ተናግረዋል።

ድንበር የሚጠብቀው ኃይል ከጀርባው ከተመታ በኋላ ድንበር ለመጠበቅ የሚችልበት ሁኔታ እንዳልነበርና የኤርትራ ወታደሮችም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ለመዝለቅ የሚከለክላቸው እንዳልነበር ሜጄር ጄኔራል በላይ ሲገልጹ የሚያሳይ ቪዲዮ፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች መሠራጨቱ ይታወቃል። ነገር ግን በመንግሥት በኩል የተሰጠ ግልጽ ማረጋገጫ እስካሁን የለም።

የኤርትራ ወታደሮችን ጉዳይ በተመለከተ በትግራይ ክልል የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር የመቀሌ ከንቲባ አቶ አታክልቲ ኃይለ ሥላሴን ሪፖርተር ያነጋገረ ሲሆንከንቲባው የኤርትራ ወታደሮችን በተመለከተ የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ ከሰጡት መረጃ ውጪ በተጨባጭ የሚያውቁት መረጃ እንደሌለ ገልጸዋል።

የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ ከነዋሪዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ እሳቸውም በሌላ የሕዝብ መድረክ ላይ ጄኔራሉ የተናገሩትን መድገማቸውን የገለጹት አቶ አታክልቲ፣ ‹‹የክልሉ ነዋሪዎች የኤርትራ ወታደሮች በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገኙ ሪፖርት ያደርጉልናል፡፡ ነገር ግን በተጨባጭ ስለመኖራቸው በግሌ አላውቅም፡፡ ለማወቅ የምችልበት ሁኔታም የለም፡፡ ይህንን ጉዳይ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መጠየቅ ትችላላችሁ፤›› ብለዋል።

የኤርትራ ወታደሮች በመቀሌ ስለመኖራቸው የተጠየቁት ከንቲባው በመቀሌ አለመኖራቸውን አረጋግጠዋል።

በጉዳዩ ላይ በፌዴራል መንግሥት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊ በመሆን የተሾሙትን ሙሉ ነጋ (/) ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...