ታኀሳስ 30 እና ጥር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው፣ ጥር 1 እና 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ የመጡት አቶ ስብሃት ነጋና አቶ ዓባይ ወልዱን ጨምሮ 20 ተጠርጣሪዎች፣ ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው 14 የምርመራ ቀናት ተፈቀደባቸው፡፡
ዓርብ ከሰዓት በኋላ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተጠርጣሪዎቹ በሁለት መዝገብ ተከፍለው ነው፡፡ በአቶ ስብሃትና በአቶ ዓባይ በተከፈቱ ሁለት መዝገቦች 20 ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ በደረሰው ጥቃትና ሌሎች ተደራራቢ ወንጀሎች ተሳትፈዋል፡፡ በመሆኑም ምርመራዎችን ለማድረግ በሕጉ መሠረት 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን የምርመራ ቀናት በመፍቀድ፣ ለጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ከቀረቡት ውስጥ የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋና ከፍተኛ ከድተዋል የተባሉ የጦር መኮንኖች መቅረባቸው ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ጥር ሦስት ቀን 2013 ዓ.ም. አቶ ስዩም መስፍን፣ አቶ ዓባይ ፀሐዬና አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴን ጨምሮ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች መገደላቸውን፣ የመከላከያ ሠራዊት የኃይል ስምሪት መምርያ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ገልጸዋል፡፡ የሟቾችን አስከሬን በሚመለከት ቤተሰቦቻቸው ወስደው መቅበር የሚችሉ መሆኑም ተገልጿል፡፡