ከሰባት አሠርታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረውን የአዲስ አበባ ስታዲየምን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማደስ ስምምነት መፈረሙን ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ስምምነቱ የተፈረመው የዲዛይን፣ የማማከርና የቁጥጥር አገልግሎቱን ከሚያከናውነው ዮናስ ዓባይ አማካሪ አርክቴክቸርና ኢንጂነሪንግ ከተባለ ድርጅት ጋር ነው፡፡ የዲዛይን ሥራውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጠናቅቆ እንደሚያቀርብ ከኮሚሽኑ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የዲዛይን ሥራው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ስታንዳርድን ጠብቆ እንደሚሠራ ታውቋል።
ስፖርት ኮሚሽን ከወራት በፊት ባካሄደውና ባለድርሻ አካላትን ባካተተው የስፖርት ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ከመከረባቸው ጉዳዮች አንዱ የአዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሳትን የተመለከተ ነበር፡፡
በወቅቱ ኮሚሽኑ የአዲስ አበባ ስታዲየምን በ2013 ዓ.ም. በ25 ሚሊዮን ብር በጀት ለማደስ ማቀዱን ገልጾ ነበር። በስፖርት ኮሚሽን ሥር የሚተዳደረው ስታዲየሙ ከካፍ በመጡ ገምጋሚዎች ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ብቁ እንዳልሆነ መገለፁ ይታወቃል።
በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥቅምት 23 ቀን 1940 ዓ.ም. የመሠረተ ድንጋይ የተጣለለትና እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ ‹‹ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታዲየም›› ይባል የነበረው ዕድሜ ጠገቡ ስታዲየም ሦስት የአፍሪካ ዋንጫዎችን (3ኛ፣ 6ኛ እና 10ኛውን)፣ እንዲሁም የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ማስተናገዱ ይታወሳል፡፡