Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የምንሰማቸው ‹‹ሰበር›› ዜናዎች ካስደነቁዋቸው ሰዎች መሀል አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ጦርነትን መዋጋት ብቻ ሳይሆን መፍጠር የሚችሉ፣ እንደ ገና ጨዋታ ወይም እንደ ገበጣ ባህላቸው መሆኑን በኩራት ሲነግሩን የነበሩ የሕወሓት ጉዶች አይሆኑ ሆነው ሲማረኩና መደምሰሳቸው ሲነገር እንዴት አይደንቀኝ? የሕወሓት ነፍስ አባት የሆኑት አቦይ ስብሃት ነጋ አፈር መስለው እጃቸው በካቴና ታስረው ሲመጡ፣ ዓባይ ወልዱ የሚባሉት የቀድሞ የትግራይ ፕሬዚዳንት ከእነ ኮንጎ ጫማቸው ፈዘውና ደንግዘው ሲታዩ፣ የቀድሞው የገንዘብ ሚኒስትር አብረሃም ተከስተ ከእነ ካቴናቸው ቅዠት ውስጥ ያሉ ይመስል ግራ ተጋብተው ሲስተዋሉ ይገርም ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለ19 ዓመታት አንቀጥቅጠው የገዙት ሥዩም መስፍን፣ የስኳር ፕሮጀክቶቻችንን የተጫወቱባቸው ዓባይ ፀሐዬና የፓርላማው ሥውር ገዥ የነበሩት አስመላሽ ወልደ ሥላሴ መደምሰሳቸው አስደናቂ ነበር፡፡ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ሰዎች የሰውን ልጅ ንቀውና ፈጣሪ መኖሩን ዘንግተው፣ ልባቸው ተደፍኖ እንደነበረ አገሬው የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡

‹‹ምከረው፣ ምከረው እንቢ ካለ መከራ ይምከረው››፣ ‹‹ንገረው፣ ንገረው አልሰማ ካለ በዱላ ነርተው››፣ ‹‹ሲሰማ የሞተን ሲሰማ ቅበረው››፣ ወዘተ ዘመን ተሻጋሪ ምሳሌያዊ አባባሎቻችን ናቸው፡፡ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብና በአገር ደረጃ አስቸጋሪ ባህሪ ያላቸው ሰዎችን ለመግራት መምከርና ማስመከር የተለመደ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው ማለት ይቻላል በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ፣ አስቸጋሪ ሰዎችን በሽማግሌዎች ማስመከር እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ የሽምግልና ሥርዓቱም በአብዛኛው ሰዎችን ከመዳኘት ባልተናነሰ፣ ግለሰቦችን መምከርና መገሰፅ ወጉ ነው፡፡ ነገሥታቱም ሆነ አገረ ገዥዎች ሲበድሉም አቤቱታ የሚቀርበው በዕድሜ በገፉ አዛውንት ነበር፡፡ በዚህ ዘመናችንም ይህ ልማድ አልቀረም፡፡

ሕወሓት የሚባለው ጉደኛ ድርጅት ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲንሰራፋ፣ ይከተለው በነበረው አደገኛና አፍራሽ አስተሳሰብ ሳቢያ ተቃውሞ የገጠመው በጊዜ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል ታሪካዊት አገር ከመቶ ዓመት በፊት እንዳልነበረች፣ የአማራ ገዥ መደብ አገሪቱን እንደተጫወተባት በመቀስቀስ ገና ከጅምሩ አማራን ጠላት በማድረግ፣ ብሔረሰቦች ከፈለጉ መገንጠል እንደሚችሉ፣ ወዘተ አሳዛኝ ዕሳቤዎችን ይዞ ሥልጣን ላይ በመውጣት ዘግናኝ ድርጊቶች ፈጽሟል፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በማንነታቸው የሚከፋፍል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በመመሥረት፣ ትውልዱን አገር አልባ አድርጎታል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ የሚቃወሙትን በጭካኔ አጥፍቷል፡፡ በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶችን በመፈጸም አገራችንን መከራ ውስጥ ከቷል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በርካታ ኢትዮጵያዊያን በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ፣ ለመምከርና ለማስመከር ሞክረው አልተሳካላቸውም፡፡ ብሔራዊ ዕርቅ ወይም መግባባት መፈጠር አለበት ሲባል፣ ‹‹መንገዱን ጨርቅ ያድረግላችሁ…›› እየተባሉ ወደ አመፅ ተገፍተዋል፡፡ አንድ ትውልድ በግድያ፣ በእስር ቤት፣ በሥቃይ፣ በአፈና፣ በስደትና በመሳሰሉ የማስወገጃ ሥልቶች ተቀጥቅጧል፡፡ በጋዜጦች፣ በመጽሔቶች፣ በሬዲዮኖችና በመሳሰሉት የመገናኛ ዘዴዎች ለሦስት አሠርት ያህል ያለ መታከት ምክር ቢሰጥም ሰሚ አልነበረም፡፡ ከእነዚህ አታካች ጥረቶች በኋላ ነበር ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በየአካባቢው ፈንድተው ከሥልጣን መንበሩ የተገፈተረው፡፡ የፈጸማቸው ግፎችና በአገር ሀብት ላይ ያደረሰው መጠነ ሰፊ ዝርፊያ አስደንብረውት፣ ከማዕከል ሸሽቶ ትግራይ ሲገባ አደብ የገዛው ለጥቂት ወራት ብቻ ነበር፡፡

‹‹ዕብድ ቢጨምት እስከ ስድስት ሰዓት ነው›› እንደሚባለው፣ ሕወሓትም ዕብደቱ አገርሽቶበት በዘረፈው ሀብትና በነበረው የስለላ መዋቅር እየተመራ ኢትዮጵያ ላይ ከ130 በላይ ግጭቶችን አስነሳ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተገደሉ፣ ሚሊዮኖች ተፈናቀሉ፣ መጠኑ በጣም ከፍተኛ የሆነ የደሃ አገር አንጡራ ሀብት ወደመ፡፡ በስመ ፌዴራሊስትነት አብረውት ካሰፈሰፉ ኃይሎች ጋር በመሆን አገር ለማፍረስ ጫፍ ላይ ደረሰ፡፡ ሕግ ጥሶ የውሸት ምርጫ አካሄደ፡፡ ታንክ፣ መድፍና ሚሳይል የሚታጠቅ ልዩ ኃይል አሠልጥኖ አገር አክሎ ብቅ አለ፡፡ ይህም አልበቃ ብሎት በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ወረራ በመፈጸም ነውረኝነቱን አሳየ፡፡ በተለይ ዕድሜ የተጫናቸው የቀድሞ አመራሮቹ ዕብሪት ከመጠን በላይ ሆነ፣ አገር ለማፍረስም ተነሱ፡፡ ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን በአገር ሽማግሌዎችና በእናቶቻችን ጭምር ቢለመኑ አንሰማም ብለው ነበር፡፡

ይህንን ጽሑፍ ሳዘጋጅ ከተማረኩትና ከተደመሰሱት በተጨማሪ ሌሎች የሕወሓትና የጦር አመራሮች የተደበቁባቸው ዋሻዎች መከበባቸውን ሰምቻለሁ፡፡ እነ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ጌታቸው ረዳ፣ እንዲሁም ከመከላከያና ከፖሊስ የከዱ ጄኔራሎችና ኮሎኔሎች ዕጣ ፈንታቸው ከሌሎቹ ጓዶቻቸው የተለየ አይደለም፡፡ ያለ እነሱ ጀግና፣ አዋቂና ሕዝባዊ እንደሌለ ቢደሰኩሩም መጨረሻቸው አላማረም፡፡ ቢመከሩ አንሰማ አሉ፡፡ የግፋቸው ዋንጫ ሞልቶ በመፍሰሱ ልባቸው ተደፈነ፡፡ ፈጣሪ መኖሩን ዘንግተው ተመፃደቁ፡፡ ሲናገሩ የነበረውና በተግባር የታየው ለየቅል ሆነና ኃፍረት ተከናነቡ፡፡

አንድ የእነሱ ደጋፊ የሆነች ጎረቤቴ፣ ‹‹መንግሥት የሚለውን አትመን…›› ስትለኝ ከርማ፣ እነ አቦይ ስብሃት በካቴና ታስረው ሲመጡና እነ ሥዩም መስፍን መደምሰሳቸውን ስትሰማ፣ ‹‹አዛውንቶችን በካቴና ማሰርና መግደል ጀግንነት ከመሰለህ ያሳፍራል…›› እያለች ስትውረገረግ ገረመኝ፡፡ ወገኖቼ በሕወሓት ዙሪያ የተኮለኮሉ ሰዎች ዕፅ ይጠቀማሉ መሰለኝ፣ ሁሉም አንድ ዓይነት ነገር ሲያወሩ ይገርመኛል፡፡ በፌስቡክም ሆነ በትዊተር የሚያጋጥሙኝ የሕወሓት ማደጎዎች ተማሩም አልተማሩም አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ እነዚህ ናቸው እኮ፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት አንድ አይደሉም›› ስንላቸው፣ አንድ ለማድረግ ሲዋሹ የነበሩት፡፡ የትግራይ ሕዝብ አንድ በአንድ እየጠቆመ መዥገሮቹን ከላዩ ላይ ሲያራግፍ፣ ማንና ማን የጥቅም ተጋሪና አንድ እንደነበረ አሁን ግልጥልጥ ብሏል፡፡ እናንተ የጥቅም ተቆራኞቹ ከሕወሓት ጋር ተያይዛችሁ መጥፋት ትችላላችሁ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ግን እናንተ እንደምትሉት አይደለም፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ ላይ አንዲት ጥይት ሳይተኩስ አለቆቻችሁን እያደነ በመጠቆም እያስረከበ ነው፡፡ እናንተ መቼም ቢሆን እንደ ተማረኩትና እንደ ተደመሰሱት አለቆቻችሁ ምክር ስለማይገባችሁ፣ ጨጓራችሁ ድብን እያለ ሀቁን ሳትወዱ በግድ ተጋቱ፡፡ ‹‹ከፋብሪካ የወጣ አንድ ዓይነት ሳሙና ትመስላላችሁ›› ያሉዋችሁ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ከሰማይ ቤት እየሳቁባችሁ መሆኑን ሳስብ፣ ውስጤ በደስታ እየተሞላ መሆኑን ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፡፡

(ዓይናለም ሀዲስ፣ ከሲኤምሲ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...