Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አስተዳደሩና ንግድ ምክር ቤቱ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በግሉ ዘርፍ በሽክርና ሊሠሩ የሚችሉ የልማት ሥራዎችን ጨምሮ፣ ሌሎች ተግባራትን በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት በከተማ አስተዳደሩና በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተፈረመ፡፡

በከተማ አስተዳደሩና በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሐሙስ ታኅሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መሠረት፣ ከስምንት በላይ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ስለመድረሳቸው ተጠቅሷል፡፡

በስምምነት ሰነዱ ላይ እንደተጠቀሰውም በከተማው አስተዳደርና በግሉ ዘርፍ በሽርክና ሊከናወኑ የሚችሉ የልማት ሥራዎችን በመንደፍ ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ማድረግ የሚል ይገኝበታል፡፡

በመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የጋራ ጥምረት ሊከወኑ የሚችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ዕቅድ እንዳለው ታሳቢ ተደርጎ ስምምነት ላይ መደረሱንና በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በጥምረት ለመሥራት የሚያስችል እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነባ ያለው የአዲስ አፍሪካ ኢንተርናሽናል ኮንቬሽን ማዕከል አክሲዮን ማኅበር በግሉ ዘርፍ በተለይም በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና በከተማ አስተዳደሩ የጋራ ኢንቨስትመንት የሚከናወን መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቀድሞ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) አስተዳደር ወቅትም የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርና አስተዳደሩ በጋራ አንድ ኩባንያ ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡

እንዲህ ካሉት ስምምነቶች ባሻገር በግሉ ዘርፍና በከተማ አስተዳደሩ መካከል ቋሚ የምክክር መድረክ ለማካሄድ የሚያስችል  ስምምነት በመግባቢያ ሰነዱ ላይ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

የምክክር መድረኮቹ የከተማ አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ምክክር ጉባዔ፣ የከተማ አስተዳደርና የግሉ ዘርፍ ምክክር መድረክና የከተማ የዘርፍ የምክክር መድረክ በሚል ተከፋፍለው የሚካሄዱ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የምክክር መድረኮቹ ዓላማዎችም የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች በራሳቸው ጉዳዮች ዙሪያ እርስ በርሳቸውና ከከተማው አስተዳደር ተወካዮች ጋር በመወያየት ያለባቸውን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር አንዱ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ የሚያጋጥሙት አስተዳደራዊ ችግሮች በአስተማማኝ ተፈትተውለት ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት የሚያስችል እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ የምክክር መድረኮቹ ሌላው ዓላማቸው ይሆናል ተብሎ በሰነዱ የተጠቀሰው ደግሞ በከተማው አስተዳደሩ የሚነደፉ የልማት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ሕጎች ከመፅደቃቸው በፊት እንደ አስፈላጊነታቸው ውይይትና ምክክር ተካሂዶባቸው ዳብረውና ተሻሽለው እንዲወጡ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት እንዲጎለብት ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የንግዱ ማኅበረሰብን የሚመለከቱ ሕጎች ከመውጣታቸው በፊት እንዲመከርበት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የማዘጋጃ አገልግሎቶች ስኬታማና ቀልጣፋ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የግሉ ዘርፍ የሚሳተፍባቸውን ሥርዓቶችና ሥልቶች መለየት የሚለው ነው፡፡ ይህ ስምምነት አንዳንድ ሥራዎችን ለግሉ ዘርፍ እንዲተው እንዲህ ያለውን አሠራር ለመተግበርም የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በከተማ አስተዳደሩና በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በጋራ ለመሥራት ከዚህ ቀደም የተለያዩ ስምምነቶችን ያካሄዱ ሲሆን፣ አሁን ያደረጉት ከበፊቶቹ ስምምነት በተለየ የቀረበ ነው ተብሏል፡፡ ይህንን ስምምነት አዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤና የአዲስ አበባ ንግድና ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ በተገኙበት የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳና የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አቶ ታምራት ዲላ ሰነዱ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡

ከዚህ ስምምነት ጎን ለጎን ምክትል ከንቲባዋና የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለስ ዓለሙ ከንግድ ምክር ቤቱ አባላትና የተለያዩ ባለሀብቶች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚህ ውይይት በወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ከንግድ ከነጋዴው የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው እንደነበር ለማወቅ የቻለ ሲሆን አገሪቱ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር የንግዱ ኅብረተሰብ በኢኮኖሚ ውስጥ ጎልቶ እንዲታይ የሁሉም ኃላፊነት መሆን እንዳለበት ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች