ከአንድ የቁጠባ አካውንት ወደ ተለያዩ በርካታ የባንክ አካውንቶች የሚደረግን የገንዘብ ዝውውር ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገደብ መጣሉን የሚያመለክተው መመርያ ባለፈው ሳምንት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጥር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲተገበር ለሁሉም ባንኮች ባስተላለፈው መመርያ መሠረት ከአንድ የባንክ አካውንት ወደ ተለያዩ በርካታ የባንክ አካውንቶች መላክ የማይቻል መሆኑን ነው፡፡
የዚህ መመርያ መውጣት በብዙዎች ዘንድ ብዥታ የፈጠረ ሲሆን፣ ከባንኮች አንፃርም ተጨማሪ ሥራ የፈጠረ ነው እየተባለ ነው፡፡ መመርያው በአግባቡ የቢዝነስ ሥራዎቻቸውን የሚያንቀሳቅሱ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላትንም አሳስቧል፡፡ በመመርያው መሠረት በአንድ ሳምንት ከአምስት ጊዜ በላይ ከአካውንት ወደ ሌላ አካውንት ገንዘብ ማንቀሳቀስ ካልቻሉ የቢዝነስ ሥራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር በመግለጽ ላይም ናቸው፡፡
ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ዝውውርን በሚገድበው መመርያና ትግበራ ወቅት የባንኮቹ ዋነኛ የሥራ አመራሮች ወይም ሕጋዊ ወኪሎቻቸው ከፍተኛ ኃላፊነት እንዲሸከሙ አድርጓል፡፡ እነዚህ ኃላፊዎች ወይም ወኪሎቻቸው ከተጠቀሰው ሳምንታዊ የዝውውር ገደብ በላይ የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮችን አንድ በአንድ እንዲያፀድቁ የሚጠበቅባቸው በመሆኑ ለባንኮቹ ፈታኝ ነው እየተባለ ነው፡፡
የዚህ መመርያ መውጣት የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የራሱ የሆነ ጫና ሊኖረው ይችላል የሚል አስተያየት ቢኖርም የብዙዎች አስተያየት ነገሩ ብዥታ ቢኖረውም ሕጋዊ አሠራሮችን መተግበር ግድ የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መመርያ የቢዝነስ ተቋማት በአግባቡ ገንዘባቸውን እንዳያንቀሳቅሱ ይጎዳቸዋል የሚለው አመለካከት ላይ ያነጋገርናቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎችም ይህንን ሐሳብ በተወሰነ ደረጃ አብራርተውታል፡፡
የዳሽን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ እንደገለጹት፣ መመርያው በሕጋዊ መንገድ የሚደረጉ ዝውውሮችን የማይመለከት በመሆኑ ያን ያህል የሚያሠጋ አይደለም፡፡ የሰሞኑ መመርያ ላይም በግልጽ እንደተቀመጠው፣ እንደ ሞባይልና የአየር ሰዓት መሙላት፣ የደመወዝ ክፍያዎችን በቀጣሪ ድርጅቶች መፈጸምና የፋይናንስ ተቋማት የፋይናንስ ድጋፎችንና የመሳሰሉት የገንዘብ ዝውውሮችን የማይመለከት በመሆኑ በዚሁ መሠረት ደንበኞች ይስተናገዳሉ፡፡
መመርያው በተወሰነ ደረጃ የሥራ ችግር ሊፈጥርባቸው የሚችሉ ተዓማኒ ነጋዴዎች እንዳሉ እናስባለን ያሉት አቶ አስፋው፣ መመርያው ላይ እንደተጠቀሰው ባንኮች እያረጋገጡና በልዩ ሁኔታ እያዩ እንዲፈቅድ የተፈቀደ በመሆኑ ችግሩ ያን ያህል ላይሆን ይችላል ብለዋል፡፡
በመመርያው መሠረትም ከገበያ ሥራ፣ ሒደትና እንቅስቃሴ እየተመለከተ የባንኩ ሥራ አስፈጻሚ ወይም ሥራ አስፈጻሚው የሚወክለው ውሳኔ እንዲያሳልፍ መደረጉም ሥጋቱን እንደሚያስቀር ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
ይህ ግን ሥራ ላይ ሊፈጥር የሚችለው ጫና ይኖራል፡፡ ሆኖም ካለው ሁኔታ አንፃር እንደ አገር ሲታሰብ ሕጋዊ አሠራር ለማስቀጠልና ሕገወጥ ሥራዎችን ላለማበረታተት ሲባል መመርያውን መተግበሩ አስፈላጊ ይሆናል ይላሉ፡፡ አሠራሩን በልዩ ሁኔታ መመልከት እንደሚገባም የመጠጥ ሥርጭት ላይ የሚሠሩትን በምሳሌ ያነሳሉ፡፡ ‹‹እነሱ በጣም ከፍተኛ ትራንዛክሽን የሚመለክት ከሆነ እዚህ ላይም ዓይተህ ተዓማኒ ውሳኔ መወሰን ነው፣ ግን ሥራ ይጨምራል፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡
መመርያውን በመተግበር ወቅት የባንኮች ቅርጫፎችም ሆነ ባንኮቹ ደንበኞቻችሁን አጥርተው የማወቅና ማነው የሚለውን ነገር የማየት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ መመርያው የወጣበት የራሱ ምክንያቶች ያሉት መሆኑን ገልጸው፣ መመርያውን ለመተግበር ባንኮች ተጨማሪ ሥራ እንዲሠሩ ሊያደርጋቸው ቢችልም የመመርያው መተግበር አግባብ ነው ይላሉ፡፡
በመመርያው ላይ በግልጽ ያልተቀመጠ ቢሆንም፣ ለዚህ መመርያ መውጣት አንዱና ዋነኛ ምክንያት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ በሕገወጥ መንገድ ከሚገባ ሐዋላ አንዱ ነው፡፡ የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ዘበነም፣ የዚህ መመርያ መውጣት ከዚህ ጋር ይያያዛል የሚል ግምትም አላቸው፡፡ አሁን በግልጽ እንደሚታየው፣ ከውጭ ወደ አገር የሚላክ የውጭ ምንዛሪ ከባንክ ውጪ የሚመጣ በመሆኑና የዚህ የገንዘብ ለውጡ ደግሞ የውጭ ምንዛሪው በውጭ እየተከፈለና ከዚያ እየቀረ፣ እዚህ በብር ገቢ እንዲደርስ መደረጉ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡
ምንም ዓይነት ቢዝነስ ሳይኖራቸው አካውንት ከፍተው ወደ ተለያዩ አካውንቶች በተደጋጋሚ የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመግታት አንዱ መንገድ እንዲህ ያለው መመርያ መሆኑንም ካነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
እንዲህ ያለውን ሕገወጥ አካሄድ ለመቆጣጠር የዚህ ዓይነት መመርያዎች አጋዥ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በውጭ አገር ተቀምጠው፣ ቢሮ ጭምር ከፍተው፣ ወደ አገር የሚላክን የውጭ ምንዛሪ እዚያው በመቀበል፣ እዚህ በሚገኙ ተባባሪዎቻቸው በብር ገንዘቡ ወደ ተላከለት ሰው አካውንት እያስገቡ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር መግባት የነበረበት የውጭ ምንዛሪ እዚያው እንዲቀር እየተደረገ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ቢዝነስ የሌለው አንድ ሰው ከአንድ አካውንት ወደ ሌሎች ብዙ አካውንቶች በየቀኑ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ እየታየ ዝም ሊባልም አይችልም፡፡
በተለይ አሁን የሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ ይህንን ሥራቸውን ያቀልላቸዋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱ የበዛ የገንዘብ እንቅስቃሴ እየታየ ከሆነ ደግሞ መቆጣጠሪያ ሥልት ማበጀት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር በሌሎች አገሮችም የተለመደ ነው፡፡ ከተወሰነ ገንዘብ በላይ በወርና በቀን ማውጣት የማይቻልበትን ሕግ የደነገጉ አሉ፡፡ ይህንንም ለመተግበር ከሲስተም ጋር በማስተሳሰር እየተጠቀሙበት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥም አሁን በወጣው መመርያ መሠረት በሳምንት ከአምስት ጊዜ በላይ ወደ ሌላ ሰው አካውንት ማዘዋወር አይቻልም ከተባለ፣ ባንኮች በዚሁ መሠረት አሠራራቸውን ማስተካከል ይችላሉ፡፡ ለዚህም ቴክኖሎጂን መጠቀም ይጠበቅባቸዋል፡፡
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ወደ አገር ከሚገባው ውጪ ምንዛሪ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው ከባንክ ውጪ ወይም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚላክ በመሆኑ፣ ይህን ሰፊ ልዩነት ለማጥበብ ከሕገወጥ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች ለመቆጠብ ወቅቱን ያገናዘበ አሠራር መዘርጋት ግድ ይላል፡፡ ሰሞኑን የተወሰደው ዕርምጃ አንዱ ሊሆን እንደሚችልም የባንክ ባለሙያዎቹ ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ማለት ግን የራሱ የሆነ ተፅዕኖ የለውም ማለት እንዳልሆነም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡
ይህ መመርያ ብቻውን መፍትሔ አይሆንም የሚለውን መከራከሪያ የሚያቀርቡ ደግሞ፣ በተለይ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማሳደግ ወይም ሐዋላን በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር እንዲገባ ለማድረግ ሌሎች አማራጮችም መታየት አለባቸው፡፡ ከሐዋላ የሚገኘውን ገንዘብ ለማሳደግ ከተፈለገ ጉዳዩን ብሔራዊ አጀንዳ አድርጎ መነሳትን ይጠይቃል የሚል እምነት ያላቸው ኢኮኖሚስቶችም፣ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያሻ በመጠቆም በጥቁር ገበያና በባንክ መካከል ያለው የምንዛሪ ዋጋ እስካልጠበበ ድረስ በሕጋዊ መንገድ በባንክ በኩል የሚመጣውን ሐዋላ ከፍ ማድረግ ከባድ መሆኑን ገልጸውልናል፡፡ እንደ መፍትሔ ከሚነሱ ነጥቦች መካከል ደግሞ በቂ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የውጭ ባንኮችን ማስገባት የሚለውም ይጠቀሳል፡፡
ያለውን ችግር በሰሞኑ መመርያ ብቻ መቅረፍ ስለማይቻል ተያይዞ ሌላ መመርያ መውጣት አለበት የሚሉ የባንክ ባለሙያዎች፣ ከውጭ የሚላክለትን ገንዘብ እዚህ በብር የሚቀበል ወይም በአካውንቱ የሚገባለት ሰው ኃላፊነት ያለበት መሆኑን የሚያመላክት መመርያ ያስፈልጋል የሚል እምነት አላቸው፡፡
በጥቅል ሲታይ ግን ከሰሞኑ መመርያና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከታታይ እየወጡ ያሉ መመርያዎች የሚያመላክቱት ሥራዎች ወደ ባንክ መዞር አለባቸው የሚል አንድምታ ያላቸውና ሰዎች ከጥሬ ገንዘብ እንቅስቀሴ እንዲላቀቁ መንገድ የሚከፍቱ ናቸው፡፡ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዳይኖርና ከአገር የሚሸሽ የአገር ሀብትን ለመቆጣጠርም ቢሆን እንዲህ ያለውን መመርያ በማውጣት በባንክ በኩል የሚደረጉ የገንዘብ እንቅስቃሴዎችን ማሳደግ ያስችላሉ፡፡
አቶ አስፋው እንደገለጹትም፣ በተከታታይ እየወጡ ያሉ መመርያዎች እያንዳንዱ ክፍያ በተቻለ መጠን ባንክ ከባንክ ሆኖ ገደብ ይኑረው ከሚለው ጋር ይያያዛል፡፡ እንደ አገርም ከሕግ ውጪ ያለን ነገር ሊበረታታ አይገባም፡፡
ሌላው ከውጭ ከሚላክ ገንዘብ ጋር እየታየ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በሐዋላ ለሚላከው ገንዘብ የሚከፈለውን የአገልግሎት ክፍያ የሚቀንስበት መንገድ መፈለግ ነው፡፡ የገንዘብ አስተላላፊ ኩባንያዎች የአገልግሎት ዋጋ እስከ 20 በመቶ የሚደርስ በመሆኑ ይህንን የአገልግሎት ክፍያ ለመቀነስ የሚያስችሉ አሠራሮች መቀየስ አንዱ ነው፡፡
ከአቶ አስፋው ገለጻ መረዳት እንደተቻለውም፣ እንደ ሞባይል ባንኪንግ ባሉ ቴክኖሎጂዎች ገንዘብ የሚላክበትና የአገልግሎት ክፍያው የሚቀንስበት አሠራር ውጤታማ ከሆነ፣ ይህንን መሞከሩ ጥሩ ነው፡፡
ከብሔራዊ ባንክ የተገኘው መረጃ ደግሞ ከውጭ ወደ አገር የሚገባውን ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ለማድረግ የአገልግሎት ወጪን የሚቀንሱ አሠራሮችን ለመዘርጋት የሚያስችል ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ከሆነ ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ሊቀንስ ይችላል የሚል እምነት አለ፡፡