Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቂ አቅርቦት የሚፈታው የዋጋ ንረት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅርብ ከምናስታውሳቸው የጤና ቀውስ መካከል አንዱ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ ቀን በተለየ የምናስታውሰው የመጀመርያው የኮቪድ-19 ተጠቂ በኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ሪፖርት የተደረገበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ዜና እንደተሰማ የነበረው መደናገጥና ከቫይረሱ ለመጠበቅ የነበረው ወኔ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ቫይረሱን ለመከላከል ይረዳሉ የተባሉ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ የነበረው ብርቱ ፍላጎትና ጥረትም የዋዛ አልነበረም፡፡ በጋራም ሆነ በግል ይደረጉ የነበሩ ጥንቃቄዎች ዛሬ እየታዩ ነው ማለት ግን አይቻልም፡፡ ሆኖም የቫይረሱ ሥርጭት ከቀደመው በበሳ መልኩ ዛሬም በከፋ ሁኔታ እየታየና አሥጊ ስለመሆኑም ይፋ እየተደረገ ነው፡፡

ቫይረሱ ኢትዮጵያ ውስጥ መታየቱ ከተሰማበት ዕለት አንስቶ ቫይረሱን ለመከላከል ያግዛሉ ከተባሉት ውስጥ አንዱ የሆነውን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ዋጋና አሁናዊ ሁኔታን ከአገራችን የግብይት ሥርዓት ጋር በማያያዝ አንድ ነገር ለማለት ወደድኩ፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ የቫይረሱ ተጠቂ ተገኘ በተባለበት ወቅት ማስክ በአንዴ እስከ 250 እና 300 ብር ዋጋ ተጠይቆበታል፡፡ ይህ የቆየ ታሪክ ሳይሆን ከወራት በፊት የሆነ በመሆኑ የሚዘነጋ አይደለም፡፡  

በወቅቱ በነበረው ድንጋጤ ለተወሰኑ ሳምንታት የማስክ ገበያ ደርቶ አንድ ማስክ ያለ ዋጋው 250 ብር ድረስ መሸጡም አጀብ አሰኝቷል፡፡ ቀስ በቀስም ዋጋው እየወረደ ረዘም ላለ ጊዜ ደግሞ ከ30 እስከ 50 ብር ከዚያም አሥርና 15 ብር ስንገዛ ከርመናል፡፡  ይህ ግን ትክክለኛ የማስክ ዋጋ አልነበረም፡፡ በእርግጥ በቂ የሆነ ምርት ስላልነበር የዋጋ ንረቱ እጥረት የፈጠረው ነው ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ እጥረት አለ ተብሎ ግን ከአንድ ማስክ ይተረፍ የነበረው ገንዘብ በመቶኛ ሲሰላ የትየለሌ እንደነበር መረዳት እንችላለን፡፡

ይህንን ጉዳይ ወደ ኋላ መለስ ብዬ እንዳስታውስና አሁን ያለውን ገበያ እንድንመለከት የወደድኩት የኢትዮጵያና የግብይት ሥርዓት መላ የሌለውና በሌላ በኩል ደግሞ በቂ ምርት ከተመረተ ገበያ እንዴት እንደሚያረጋጋ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡

ከወራት በፊት በሚስጥር ጭምር አንድ ማስክ 50 ብር እና ከዚያም በላይ ሲሸጡ የነበሩ ፋርማሲዎች ሳይቀሩ ዛሬ የአንድ ማስክ የመሸጫ ዋጋቸው ከአምስት እስከ ሰባት ብር ወርዷል፡፡ በዚህም ዋጋ ሸጠው የትርፍ ህዳጋቸው ከእጥፍ በላይ እንደሆነ የጅምላ መሸጫ ዋጋውን ላወቀ ነገሩ በደንብ ይረዳዋል፡፡ ስለዚህ ያለአግባብ በነበረ ጭማሪ ሕዝቡ ሲጎዳ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ዋናው ነገር አሁን የማስክ ዋጋ በዚህን  ያህል ደረጃ የመውረዱ ምክንያት በቂ የማስክ አቅርቦት እንዲኖር መደረጉ ነው፡፡ የማስክ ማምረት የሚችሉ ተቋማት ማምረት በመቻላቸውና አቅርቦቱ በጨመሩ ዋጋው ሊቀንስ መቻሉ አያጠራጥርም፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ከዚህ በኋላ ሁሉም በየአቅሙ ማስክ እየገዛ በመጠቀም የሚፈለገውን ጥንቃቄ ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በማስክ ላይ የነበረው የዋጋ ለውጥ በግብይት ሥርዓት ውስጥ የአቅርቦት ዕድገት ዋጋ እንዲረጋጋ ወይም እንዲቀንስ በማድረግ ያለውን አበርክቶ በደንብ ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በእጥረት ስም ያልተገባ ዋጋ በመስጠት የትርፍ ህዳግን እጅግ በተጋነነ ሁኔታ በማስፋት ይፈጸም የነበረውን ክፉ ተግባር ያጋልጣል፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም ኪስን ለመሙላት ያለንን ፍላጎት ያሳበቀብን ድርጊት ሆኖም ይሰማኛል፡፡

ቁም ነገሩ ግን ልክ እንደ ማስክ ዋጋ ሁሉ በሸመታ ውስጥ እየከፋ የመጣውን የሸቀጦች የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር አሁንም አቅርቦትን ማሳደግ ወሳኝ ነው፡፡ በተለይ መሠረታዊ ምርቶች በበቂ እንዲመረቱና እንዲቀርቡ በማድረግ ከተሠራ ውጤት ሊመጣ የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው፡፡

ክፋቱ ግን አሁን ላይ መሠረታዊ ምርቶች ጣራ ነክተዋል፡፡ ምክንያታዊ ያልሆኑ ጭማሪዎች በብዙ ምርቶች ላይ እየታየ ነው፡፡ አንዳንድ ምርቶች ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት እንዲሁ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ከፍ እያለ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ  ጭማሪ ሊያሳዩ ቢችሉ አሁን እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበት ግን ያሳስባል፡፡ ግብይት ውስጥ ረዥም እጅ ያላቸው ደላሎች ዛሬም ዋጋ ሰቃይ ገበያ መሪ ናቸው፡፡

ስለዚህ ቢያንስ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ላይ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አላስፈላጊ የግብይት ሰንሰለቶችን በአግባቡ መቆጣጠርንም ይጠይቃል፡፡ ጊዜያዊ የእሳት ማጥፋት ሥራዎች ላይ ከማተኮር ወጥተን ዘለቄታን ያገናዘበ መፍትሔ ማበጀት ተገቢ ነው፡፡ በቅርቡ የዋጋ ጭማሪ ከታየባቸው መሠረታዊ ከሚባሉ ምግብ ነክ ምርቶች መካከል አንዱ የሆነው የምግብ ዘይት ላይ እየተሠራ ያለውን ሥራ በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ ለምግብ ዘይት የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ የዋዛ አይደለም፡፡ ይህንን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ ይረዳሉ የተባሉ ትላልቅ የዘይት ፋብሪካዎች ወደ ማምረት እየገቡ ሲሆን፣ ሌሎችም በተለያየ ሒደት ላይ እንደሚገኙ መሰማቱ ደግሞ ደግ የምንለው ዜና ነው፡፡ አሁን እየተሰማ እንዳለው ፋብሪካዎቹ የማምረት አቅም ከራስ አልፎ ለውጭ ገበያ ምርቱን ለማቅረብ የሚያስችል ነው፡፡ ደግሞም የእያንዳንዱን ፋብሪካ የማመረት አቅም ካየን በእርግጥም ከፍላጎት በላይ ሊመረት የሚችል መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርጋል፡፡

ይህ ከሆነ ደግሞ ለምግብ ዘይት መቀነስ ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ይሆናል የሚለው ታሳቢ ይደረጋል፡፡ ለጊዜው ለውጭ ገበያ የምንለውን ትተን የአገር ውስጥ ፍላጎት ለመሸፈን የሚያስችል ደረጃ የምንደርስ ከሆነ፣ ዛሬ ላይ ተጋኖ የወጣውን የዘይት ዋጋ መቀነስ ይቻላል ማለት ነው፡፡

ምክንያቱም ፍላጎቱን የሚመጥን ምርት ከተመረተ ልክ እንደ ማስኩ የምግብ ዘይትም ገበያውን ባገናዘበ መልኩ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሌላ ሥሌት አያስፈልገውም በቂ ምርት ማምረት ከተቻለ ገበያ ይረጋጋል፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡

በአገር ውስጥ መመረቱ አንዱ ጠቀሜታም ይኸው ስለሆነ በዚሁ ሥሌት የዘይት ገበያ ይረጋጋል ብሎ ማሰብ ትክክል ነው፡፡ ችግሩ ግን እነዚህ ዘይት አምራቾች አሁን ያለውን ገበያ አስልተው እኛም በዚሁ ዋጋችንን ተክለን እንሸጣለን ካሉ ነው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ የገበያ ተመንን መሠረት አድርጎ የተረፈ ህዳግን መጥኖ የማቅረብ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ያኔ የነዚህ ማምረቻዎች መገንባት እውነተኛ ትርጉም ይኖረዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን እነዚህ የዘይት ማምረቻዎች ጥቅማቸው ታውቆ ወደ ሥራ ገብተው በአቅማቸው ልክ እንዲያመርቱ ድጋፍና ዕገዛ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በተቆራረጠ የኃይል አቅርቦት የሚፈለገውን ምርት ላያመርቱ ይችላሉና እንዲህ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ይህንን ሰበብ አድርጎ ያልተገባ ዋጋ ይዞ ገበያ ላይ ለመቅረብ እንዳይሞከር ያደርጋልና መንግሥትም የራሱን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል፡፡

በአጠቃላይ በሌሎች መሠረታዊ በሚባሉ ምርቶች ላይም ተመሳሳይ ዕርምጃ በመውሰድ ዳገት እየሆነ ያለውን የዋጋ ንረት ከዚህም በላይ እንዳይሆን መግታት ይቻላል፡፡ በተለይ እጥረት የሚታይባቸውና የዋጋ ንረት በተደጋጋሚ የሚስተዋልባቸው መሠረታዊ ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የግብይት ሥርዓቱን ለማስተካከል በተግባር የሚታይ ሥራ መሠራት አለበት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች