ኦሊምፒክ ኮሚቴ የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል
ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅት የተያዙ ብሔራዊ አትሌቶች ባለፈው ቅዳሜና እሑድ የመጀመርያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከኅዳር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በየርቀቱ በርካታ አትሌቶችን ሆቴል በማስገባት ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ለስምንት ወራት ያህል ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የመጀመርያው የሥልጠና ምዕራፍ መጠናቀቁን ተከትሎ ጥር 8 እና 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም በሁለቱም ፆታ ከ800 ሜትር እስከ 10,000 ሜትር በተደረገው ማጣሪያ ከ96 አትሌቶች 62 ተለይተው ለቀጣይ ዝግጅት ተይዘዋል፡፡ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በዕለቱ አሸናፊ ሆነው ላጠናቀቁ አትሌቶች እንደየደረጃቸው እስከ አሥር ሺሕ ብር ማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል፡፡
ከመካከለኛና እስከ ረዥም ርቀት በተደረገው የመጀመርያ ዙር ማጣሪያ፣ በ800 ሜትር 22 አትሌቶች ለውድድር የቀረቡ ሲሆን፣ በሁለቱም ፆታ አምስት አምስት አትሌቶች ተለይተዋል፡፡ በዚሁ መሠረት በሴቶች ድርቤ ወልተጂ፣ ሒሩት መሸሻ፣ ማህሌት ሙሉጌታ፣ ነፃነት ደስታና ነፃነት ዓለሙ ለሚቀጥለው የዝግጅት ምዕራፍ ተይዘዋል፡፡ በወንዶች ደግሞ አዲሱ ግርማ፣ ዳንኤል ወልዴ፣ ቶሎሳ በደና፣ ኡመር ኦማናና ጡሪ ምርኮና ተመርጠዋል፡፡
በ1,500 ሜትር ቀደም ሲል በሁለቱም ፆታ ከተያዙት 15 አትሌቶች መካከል በሴቶች ጉዳፍ ፀጋዬ፣ ለምለም ኃይሉ፣ ቅድስት ከተማ፣ ታዱ ተሾመና አዳነች አምበሴ ተመርጠዋል፡፡ በወንዶች ደግሞ ታደሰ ለሚ፣ ከበደ እንዳለ፣ ሳሙኤል አባተ፣ መልኬነህ አዘዘና መልካሙ ዘገዬ ናቸው፡፡
በ3000 ሜትር መሰናክል በአጠቃላይ በሁለቱም ፆታ ለውድድር ከቀረቡት 18 አትሌቶች መካከል በሴቶች አገሬ በላቸው፣ ብርቱካን አዳሙ፣ ወይንሸት አንሳ፣ ሲምቦ ዓለማየሁና ዘርፌ ወንድማገኝ ሲሆኑ፣ በወንዶች ታደሰ ታከለ፣ ጌትነት ዋለ፣ ጫላ ባዬ፣ አብርሃም ስሜና ተስፋዬ ድሪባ ሆነዋል፡፡
በ5000 ሜትር ቀደም ሲል በሁለቱም ፆታ ከተያዙት 14 አትሌቶች መካከል በወንዶች ንብረት መላክ፣ ያሲን ሐጅ፣ ጌታቸው መርሻ፣ ሙክታ እንድሪስና ጫላ ከተማ ሲሆኑ፣ በሴቶች ፋንቱ ወርቁ፣ እጅጋየሁ፣ መስከረም ማሞ፣ ይታይሽ መኮንንና ሥራነሽ ይርጋ ሆነዋል፡፡
በ10,000 ሜትር በአጠቃላይ በማጣሪያው በሁለቱም ፆታ ለማጣሪያ ከቀረቡት 15 አትሌቶች ሰለሞን ባረጋ (የአገር ውስጥ ክብረ ወሰን በማሻሻል)፣ አንዳምላክ በልሁ፣ ጉዬ አዶላ፣ ሚልኬሳ መንገሻና ታምራት ቶላ ተመርጠዋል፡፡ በሴቶች ደግሞ የዓለምዘርፍ የኋላው፣ ፀሐይ ገመቹ፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣ መድህን ገብረሥላሴና አስናቀች አወቀ ሆነዋል፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና የውድድር ዳይሬክተር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ማጣሪያ የመጨረሻ እንዳልሆነ እንዲያውም በቀጣይ ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዝያ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሻሉ አትሌቶች ከተገኙ ለቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ዝግጅት እንዲካተቱ ይደረጋል፡፡ ከሔንግሎው የመጨረሻ ማጣሪያ በፊት ሌሎች ተጨማሪ አትሌቶች ማጣሪያዎችን እንዲያደርጉ ተጨማሪ የውድድር ዕድል የሚመቻች ስለመሆኑ ጭምር ተናግረዋል፡፡