ሙዳይ የበጎ አድራጎት ማኅበር (ሙዳይ) በመንግሥት በኩል ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱና ቋሚ የቦታ ይዞታ ባለመኖሩ ምክንያት ትልቁ ችግር ውስጥ መግባቱን አስታወቀ፡፡
በኪራይ አገልግሎት የሚሰጥበትን ቦታ በአምስት ወር ውስጥ እንዲለቅ በመጠየቁ እየደገፋቸው ያሉ ወገኖች ለአደጋ እንደሚዳረጉ ገልጿል፡፡
ሙዳይ ጥር 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ላይ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የቀድሞው አዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ለማኅበሩ አገልግሎት የሚውል 5,000 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጥ ቢወሰንም እስካሁን ድረስ በመጓተቱ ምክንያት ማኅበሩ ላይ ችግር መውደቁንም አመልክቷል፡፡
የሙዳይ የበጎ አድራጎት ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ እንደገለጹት፣ በተደጋጋሚ የተወሰነውን ቦታ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም አስተዳደሩ ትኩረት ባለመስጠቱ ተፈጻሚ አልሆነም፡፡ በአሁኑ ወቅት ማኅበሩ ለ21 ዓመታት ይኖሩበት ከነበረው ሥፍራ ልቀቁ መባላቸው ትልቅ ችግር ውስጥ እንደከተታቸው አስረድተዋል፡፡
ማኅበሩ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሕፃናትና ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ወጣቶችን ከጎዳና ተዳዳሪነትና ከሴተኛ አዳሪነት ሕይወት በማላቀቅ በራሳቸው እንዲቆሙ ማድረጉን ወ/ሮ ሙዳይ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ማኅበሩ አገልግሎት የሚሰጥበትን ቦታ ያከራዩት አካላት ለሌላ ሥራ ቦታውን በመፈለጋቸው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ እንዲለቁ ትዕዛዝ እንደደረሳቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
የቦታ ይዞታውን በተመለከተ የተለያዩ የመንግሥት ተቋሞች ጋር ቢሄዱም መፍትሔ እንዳልተሰጣቸው የገለጹት ወ/ሮ ሙዳይ፣ ማኅበሩ በዚሁ ከቀጠለ በውስጡ ያሉት ተረጂዎችም ሆኑ ማኅበሩ ተበታትነው እንደሚቀር ተናግረዋል፡፡
የሙዳይ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ታደለ አየለ፣ ማኅበሩ በኪራይ ምክንያት መቸገሩንና ድጋፍ እንደሚፈልግ ለቀድሞው ከንቲባ ድሪባ ኩማ ማሳወቃቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከንቲባውም 5,000 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲፈቀድለት መመርያ ቢሰጡም ተፈጻሚ ሳይሆን ከሥልጣናቸው ተነስተዋል፡፡
የአዲስ አበባ መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ለማኅበሩ ቦታ እንዲሰጠው ለየካ ክፍለ ከተማ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ያገኘው ምላሽ ከአያት መኖሪያ መንገድ ጀርባ 3,200 ካሬ ሜትር ብቻ እንደሚሰጥ ማስታወቁን አቶ ታደለ ገልጸዋል፡፡
ዓምና በታኅሣሥ ወር የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ይወስንበት የተባለው ጉዳይ በተለያዩ ምክንያቶች መፍትሔ አለማግኘቱን የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው፣ ማኅበሩ የሚያርፍበት ቦታን ካላገኘ ድጋፍ የሚሰጣቸው ወገኖች ስለሚበተኑና ለከፋ ችግር ስለሚጋለጡ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኘው ከያኒ ተስፋዬ ገብረሃና በሙዳይ ማኅበር የተያዙ ሕፃናትና ወጣቶች ተመልሰው ጎዳና ላይ እንዳይወድቁ ኅብረተሰቡ የሚችለውን እገዛ እንዲያደርግ የተማፅኖ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሙዳይ በጎ አድራጎት ከሁለት አሠርታ በፊት በ1992 ዓ.ም. የተመሠረተ ማኅበር ነው፡፡