Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

አሁን ያለው ትውልድ ከያ ትውልድ እንዲማር

‹‹ያ ትውልድ ተቋም›› የተመሠረተው ሚያዝያ 23 ቀን 2004 ዓ.ም በሰሜን አሜሪካ ዳላስ ነው፡፡ በ1969 ዓ.ም. የዓለም ሠራተኞች ቀን (ሜይዴይ) ክብረ በዓልን በሰላማዊ ሠልፍ ለማክበር የወጡ ወጣቶች ላይ ደርግ ያደረሰው ፍጅት ለተቋሙ መመሥረት ምክንያት ነው፡፡ ተቋሙ የነበረውን ፍጅትና የተሰዉት እነማን እንደሆኑ መረጃ የማሰባሰብና የማደራጀት ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ድረ ገጽ በመክፈት በተለይም ከ1969 እስከ 1971 ዓ.ም. በደርግ ነፃ ዕርምጃና ቀይ ሽብር ሰለባ የሆኑን ሰማዕታት ስምና ምሥል በአማርኛና እንግሊዝኛ  መግለጫዎች አካቷል፡፡ አቶ ነሲቡ ስብሐት የ‹‹ያ ትውልድ ተቋም›› ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ስለተቋሙ ዓላማ፣ ራዕይና ተልዕኮ እንዲሁም ባለፉት ሰባት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ያ ትውልድ ተቋም›› የተመሠረተበት ዓላማ ምንድነው?

አቶ ነሲቡ፡- ‹‹ያ ትውልድ ተቋም›› ዓላማ ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን ይዟል፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም የያ ትውልድ የዲሞክራሲና የፍትሕ ትግል ታሪክ ማሰባሰብ የመጀመርያ ዓላማ ሲሆን፣ ለያ ትውልድ ሰማዕታት መታሰቢያ ቦታዎችን መሰየምና ሐውልት ማቆም ሁለተኛ ዓላማው ነው፡፡ በሦስተኛነት ተቋሙ በስፋት መሥራት የሚያስበው በትግሉ የተጎዱ ወገኖችንና ቤተሰቦቻቸውን በተለያየ መልኩ መርዳትና ማገዝ ናቸው፡፡ የያ ትውልድ ታሪክ መረጃ ማሰባሰብና ለትውልድ ማስተላለፍ ጠቀሜታው ከትምህርት ሰጪነቱ በተጨማሪ በኢትዮጵያ በደርግ አገዛዝ የደረሰው አንድ ትውልድ የማጥፋት ዕርምጃ እንዳይደገም ልብ እንድንል ‹‹ያ ትውልድ›› ቃሉ ይጋብዘናል፡፡

ሪፖርተር፡- በጊዜው የተሰዉትን ሰማዕታት መረጃ በምን መልኩ አሰባሰባችሁ?

አቶ ነሲቡ፡- በተለያዩ የኢትዮጵያ የክልል ከተሞች በጊዜው መስዋዕት የሆኑ ሰዎች ቤተሰቦች መረጃዎችን እናገኛለን፡፡ ሰዎችን በመጠየቅ መረጃዎችን የምናደራጅ ሲሆን፣ መጀመርያ ላይ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ሥራዎቻችንን ሲያዩ ‹የኔም ወንድም፣ ቤተሰብ፣ እንደዚህ ሆኗል› እያሉ መረጃዎችን በፎቶ በማስደገፍ ይሰጡናል፡፡ በዚህ መንገድ ከተለያዩ ግለሰቦች፣ ከመገናኛ አውታሮች፣ ከመጽሐፍ፣ ከድረ ገጽና ከተለያዩ ድርጅቶች መረጃዎች ሰብስበናል፡፡ እነዚህን መረጃዎች መጽሐፍ ለመጻፍ፣ ጥናት ለማድረግ፣ ቴአትርና ፊልም ለመሥራት ለሚፈልጉ በትክክለኛው መንገድ ተደራሽ እንዲሆኑ ማስቻል  ፍላጎታችን ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ‹‹ያ ትውልድ ተቋም›› ለተሰዉ ሰማዕታት በምን መልኩ ነው መታሰቢያ የሚቆምላቸው?

አቶ ነሲቡ፡- መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች በስማቸው እንዲሰየሙ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ችግር የገጠማቸው በዚያ ጊዜ መስዋዕት የሆኑ ቤተሰቦችን በተለያየ መልኩ ማገዝና መርዳትም ከዚሁ የሚካተት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ተቋሙ መረጃዎችን ከማሰባሰብ በዘለለ የፖለቲካ ተሳትፎ አለው?

አቶ ነሲቡ፡- ‹‹ያ ትውልድ ተቋም›› የትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት ከመወገን ነፃ የሆነ ሲሆን፣ ዋና ዓላማው በ‹‹ያ ትውልድ›› ከደረሰው ፍጅት የአሁን ወጣቶች፣ መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲማሩበትና ቆም ብለው እንዲያስቡበት የሚያግዝ ነው፡፡ በሌላ በኩል በሰማዕቱ ስም ችግኝ መትከልና በጎ ተግባሮችን በማከናወን እነሱን ማሰብና ለመዘከር ታልሟል፡፡   

ሪፖርተር፡- ድረ ገጹ ምን ምን አካቷል?

አቶ ነሲቡ፡- በጊዜው ስለነበረው አገዛዝ፣ ስለቀይ ሽብር ሰማዕታት፣ የቀይ ሽብር ተሳታፊዎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የብዙኃን ድርጅቶችና ወጣቶች የያዘ ነው፡፡ በድረ ገጹ ሁሉም በተቻለው መጠን መረጃዎችን ለማካተት እየተሞከረ ይገኛል፡፡ በዚህም የዚያን ጊዜ መስዋዕት የሆኑትም በጊዜው ዕርምጃውን በዋናነት ሲመሩ የነበሩት እንዲሁ ተካቷል፡፡ በተቻለ መጠን በወቅቱ የነበረውን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አመለካከቶች የሚያንፀባርቁ መረጃዎች ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል መስዋዕት የሆኑ ሰማዕታት የት አካባቢ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸውና በማን እንደተወሰደባቸው የሚገልጹ መረጃዎች በድረ ገጹ ለማካተት ተጥሯል፡፡ ይህም አጥኚዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ፊልም ሠሪዎችና በጊዜው ስለነበረው ሁኔታ ማወቅ የሚፈልጉ አካላት በቀላሉ እንዲያገኙት የተሰናዳ ነው፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ 4,000 የሚሆኑ ሰማዕታት መረጃዎች በተለያየ መልኩ ተሰባስቧል፡፡ ከዚህ በኋላ ሌሎችም ሰማዕታት ሊኖሩ ስለማይችሉ በየጊዜው በሚገኘው መረጃ መሠረት ገቢ ይደረጋሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- በውሸት ትርክት ምክንያት መረጃዎችን የመጠራጠር ሁኔታ አለ፡፡ በ‹‹ያ ትውልድ ተቋም›› የሚሰባሰቡ መረጃዎች ምን ያህል እውነታ አላቸው? ምን ያህልስ ሚዛናዊ ነው?

አቶ ነሲቡ፡- በጊዜው በኢትዮጵያ ክፍላተ አገር የተፈጸሙ ግድያዎችን ሁሉ የሚገልጹ መረጃዎች ናቸው፡፡ ይህም አንዱ አካባቢ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ የተፈጸመ አይደለም፡፡ በጊዜው ሁሉም ብሔረሰቦች ላይ የደረሰ በመሆኑ መረጃዎችን ስንሰበስብ ጉዳት የደረሰበት (ሰማዕት) ብቻ መሆኑን አረጋግጠን ነው፡፡ ይህም አሁን ያለው ትውልድ ፍትሐዊ መረጃዎችን እንዲያገኝ ያግዛል፡፡ በጊዜው የነበሩት ዕርምጃዎች ጎራ የለዩ ሳይሆኑ የሚነሳውን ርዕዮተ ዓለም በመቃወም ምክንያት የመጡ በመሆናቸው ቀለምና ብሔር አልነበራቸውም፡፡ እኛም መረጃዎች ስናሰባስብ በጊዜው በነበረው ፍጅት ጉዳት የደረሰባቸው ወይም መስዋዕት ከሆኑ ቤተሰቦቻቸው መረጃውን ይዘን ነው፡፡ በዚህም አሁን ያለው ትልቅ ከነበረው ያልተገባ ዕልቂት መማር እንዲችልና ለታሪክም በትክክለኛው መንገድ የተሰበሰቡ መረጃዎችን በቀላሉ እንዲያገኝ እናደርጋለን፡፡  

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ዓይነት ሥራዎችን ትሠራላችሁ?

አቶ ነሲቡ፡- በቀጣይ አሁን ያገኘናቸውን መረጃዎች ማጠናቀርና የቀሩ መረጃዎችን ከተለያዩ ቦታዎች ማሰባሰብ ነው፡፡ አባላትን በማብዛትና በማጠናከር መረጃ ከመለዋወጥ በተጨማሪ ለችግር የተጋለጡ የሰማዕታት ቤተሰቦችን እንዲታገዙ ማድረግና አሁን ያለው ትውልድ ከ‹‹ያ ትውልድ›› እንዲማር ማድረግ ቀጣይ ራዕያችን ናቸው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...

‹‹በአሁኑ ሰዓት እየፈተነን ያለው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው›› አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን፣ አይሲዳ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

አይሲዳ አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት በኤችአይቪ ሥርጭት ቁጥጥር ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ አዋቅሮ በተለይ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ...