Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አማራ ባንክ የምሥረታ ጉባዔውን ለማካሄድ በቂ ውክልና አገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛውን የተከፈለ ካፒታልና የባለአክሲዮኖች ቁጥር ይዞ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ የምሥረታ ጉባዔውን ለማካሄድ የሚያስችለውን የምልዓተ ጉባዔ ውክልና ማሟላት እንደቻለ ታወቀ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ አማራ ባንክ የአክሲዮን ሽያጩን በጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ የባንኩን ምሥረታ ዕውን ለማድረግ የሚያስችለውን ካፒታል ማሰባሰብ የቻለ ቢሆንም፣ የምሥረታ ጉባዔውን በውክልና ለማካሄድ በመገደዱ በዚሁ መሠረት ለመሥራች አባላቱ ባለአክሲዮኖች ውክልና እንዲሰጡ ባደረገው ጥሪ በመጀመርያው ዙር በቂ የውክልና ቁጥር ሳያገኝ መቅረቱ ይታወሳል፡፡

የውክልና አሰጣጡን በ15 ቀናት ባራዘመበት ወቅት ግን የምሥረታ ጉባዔውን ለማካሄድ የሚያስችለውን ውክልና ባለአክሲዮኖች ሊሰጡ በመቻላቸው እስከ የካቲት 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የመሥራች ጉባዔውን ያካሂዳል ተበሎ እንደሚጠበቅ እኚሁ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ከኅዳር 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለአክሲዮኖች ውክልና እንዲሰጡ በተላለፈው ጥሪ መሠረት፣ በአንድ ወር ውስጥ ውክልና የሰጡት ባለአክሲዮኖች ቁጥር 75 ሺሕ ብቻ ነበር፡፡ ይህም ከ185 ሺሕ ባለአክሲዮኖች አንፃር ውክልናው 41 በመቶ ብቻ በመሆኑ፣ የሚፈለገውን የ51 በመቶ የምልዓተ ጉባዔ ውክልና ለማስገኘት አላስቻለም ነበር፡፡

ባንኩ ከምሥረታ ጉባዔው በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዋናነት ቴክኖሎጂን መሠረት አድርጎ ኢንዱስትሪውን ይቀላቀላል ተብሎ የሚጠበቀው አማራ ባንክ፣ የአክሲዮን ሽያጩን የጀመረው ነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባንክ ለመመሥረት የሚያስችለውን ካፒታል ማሰባሰብ ችሏል፡፡

ከባለ አክሲዮኖች ብዛት አንፃር በቶሎ ወደ ምሥረታ ባለመግባቱ ጥያቄ ቢነሳበትም፣ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ ከ185 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን በመያዝ የመጀመርያው የሚሆነው አማራ ባንክ፣ ያሰባሰበው፣ የተከፈለና የተፈረመ ካፒታሉ በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡

እስካሁን ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከሰበሰበው የተከፈለ ካፒታል ሌላ 8.1 ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል የያዘና ከአክሲዮን ሽያጩ አገልግሎት ክፍያ ደግሞ 402 ሚሊዮን ብር ማሰባብ የቻለ ነው፡፡

አሁን በተገኘው የውክልና ቀመር መሠረት ምሥረታውን ለማካሄድ ውክልና የሰጡት ባለአክሲዮኖች ከ51 በመቶ በላይ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ምሥረታውን ለማካሄድ የሚገድበው ነገር አይኖርም፡፡

በኢንዱስትሪው ውስጥ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ይዞ የባንክ ምሥረታ ያካሄደ ባንክ የሌለ ሲሆን፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉ ባንኮች አብዛኛዎቹ ከ500 ሚሊዮን ብር በታች በሆነ የተከፈለ ካፒታል ወደ ሥራ የገቡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች