Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥትንም የተገዳደረው የዋጋ ግሽበት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ገበያዎች ላይ እየታየ ያለው የሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ሸማቾችን እየፈተነ ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሠረታዊ ከሚባሉ ምግብ ነክ ምርቶች ጀምሮ በሌሎች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ እጅግ የተጋነነ ሆኗል፡፡

ሰሞኑን ወርኃዊ አስቤዛ ለማድረግ ገበያ ወጥታ የነበረችው የቤት እመቤት ወ/ሮ አስናቁ ታፈሰ በአንዳንድ ምርቶች ላይ በአጭር ጊዜ ያየችው የዋጋ ጭማሪ እንዳስደነገጣት ትገልጻለች፡፡ ለመኖሪያዋ ቅርብ ወደ ሆነው ሳሪስ ገበያ የሸመተቻቸው ምግብ ነክ ምርቶች ከዚህ ቀደም ትገዛ ከነበረው ዋጋ በላይ ሆኖባታል፡፡ በዕለቱ ለመግዛት ገበያ ከወጣችባቸው ምርቶች መካከል በነበረው ዋጋ ያገኘችው ሽንኩርትና ቲማቲም ብቻ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ምግብ ነክ ምርቶች ዋጋቸው ስለመጨመሩ ትገልጻለች፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት አንዱን ኪሎ ዛላ በርበሬ በ135 ብር ገዝታ እንደነበር የምትገልጸው ወ/ሮ አስናቁ፣ አሁን እንደዓይነቱ 150 ብርና ከዚህ በላይ መድረሱን ታዝባለች፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ዋጋ ጋር ስታነፃፅረው ዋጋው በዕጥፍ ጨምሯል፡፡ ኪሎው 65 ብር የነበረውን ምሥር 72 ገዝታለች፡፡ የዋጋ ጭማሪ ከታየባቸው ምርቶች ውስጥ ፓስታ ተጠቃሽ ሲሆን፣ በካርቶን 375 ብር ሲገዛ የነበረውና ሃያ ፍሬ የሚይዘው እሽግ ፓስታ አሁን ላይ 425 ብር ገብቷል፡፡ ሌሎች የፓስታ ምርቶችም እንደየዓይነታቸው የዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል፡፡

ከሌሎች ምግብ ነክ ምርቶች በአንፃራዊነት ባለበት የቀጠለ ብላ የገለጸችው የአተር ክክ ሲሆን፣ ቀድመው ጭማሪ የተደረገባቸው ምርቶችም ቅናሽ አለማሳየታቸውን ትገልጻለች፡፡   

ከተለያዩ ገበያዎች ቅኝት መረዳት እንደሚቻለው የዋጋ ጭማሪው በምግብ ነክ ምርቶች ላይ ጎልቶ ቢታይም፣ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ብረታ ብረት፣ ሲሚንቶና የመሳሰሉ ምርቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው እጥረትም ያለባቸው ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡     

 ለአስቤዛ ወደ ገበያ የወጡ እንደ ወ/ሮ አስናቁ ያሉ ሸማቾች፣ አሁን ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ከዚህ ቀደም እንደሚታየው ዓይነት ሳይሆን፣ በጣም የተጋነነ ሆኖ እንዳገኙት ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ ምርቶች ጭማሪ መደረግ ያልነበረባቸው እንደሆኑ የሚገልጹም አሉ፡፡ ከሌሎች በተለየ ግን ከሰሞኑ የተጋነነ ዋጋ የታየበት የምግብ ዘይት ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት የዋጋ ቅናሽ አሳይቶ የነበረው የምግብ ዘይት ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ በአንድ ጊዜ የታየበት ጭማሪ ከፍተኛ ነው፡፡

አምስት ሌትር ፈሳሽ ዘይት እንደዓይነቱ/መለያው በችርቻሮ ከ300 ብር እስከ 320 ብር ሲሸጥ የነበረ ሲሆን፣ ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ ከ400 እስከ 450 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

የምግብ ዘይት ላይ እጥረት እንዳይፈጠርና ገበያውን ለማረጋጋት ተብሎ የሚድሮክ ኩባንያ አባል የሆነው ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት ፈሳሹ ባለ አምስት ሌትር ዘይት በ330 ብር፣ በኋላም 310 ብር እያቀረበ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ይህንን ዋጋ ለውጦ ከ360 በላይ አድርጓል፡፡ መሠረታዊ ከሚባሉ ምርቶች መካከል አንዱ የሆነውና መንግሥት ታክስ ቅናሽ ያደረገበት ምርት መሆኑ የሚነገርለት የምግብ ዘይት በአንዴ የዚህን ያህል ጭማሪ ማሳየቱ ሸማቹን ካስደነገጡና ካማረሩ ምርቶች መካከል አንዱ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በሸማቾች ማኅበር በኩል የሚሸጠው የፓልም ዘይት ዋጋም ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ጭማሪ እንደተደረገበት ሸማቾች እየገለጹ ነው፡፡ ሦስቱ ሌትር 171 ብር ይሸጥ የነበረው የፓልም ዘይት አሁን 202 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ 

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ደግሞ አሁን በገበያ ውስጥ እየታየ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ለማረጋጋት ወስጃቸዋለሁ ካላቸው ዕርምጃዎች ውስጥ አንዱ እንደ ዘይት ያሉ ምርቶች ላይ የተጣለውን ቀረጥ በከፍተኛ ሁኔታ ማውረዱ ነው፡፡

እንደ ምግብ ዘይት ያሉ ምርቶች ይጣልባቸው የነበረው የ40 በመቶ ቀረጥ ወደ አምስት በመቶ እንዲወርድ መደረጉንም አስታውቋል፡፡ ከዘይት ሌላ ስኳርና የሕፃናት ወተት በአምስት በመቶ ቀረጥ ብቻ እንዲገባ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል መመርያ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡

በዚህ መመርያ መሠረት ማንኛውም የውጭ ምንዛሪ ያለው በዳያስፖራ አካውንትም ሆነ በፍራንኮ ቫሉታ እነዚህን ምርቶች አምስት በመቶ ቀረጥ በመክፈል ብቻ ማስገባት ይቻላል፡፡ ስንዴና ሩዝ ደግሞ ከቀረጥ ነፃ የሚገባ ስለመሆኑም ይኼው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡    

በዓለም አቀፍ ዋጋ መሠረት አምስት ሌትር ዘይት ከ170 ብር እስከ 200 ብር ያወጣል በሚባልበት በዚህ ሰዓት፣ በአገር ውስጥ ገበያ እስከ 450 ብር ድረስ የሚሸጥበት ምክንያት ግልጽ አልሆነም፡፡ አሁን ባለው የዓለም ዝቅተኛው ዋጋ እስከነቀረጡ አምስት ሌትር ዘይት የሚፈጀው 178.50 ብር ነው፡፡ ከውጭ ገበያ በ200 ብር የተገዛ ደግሞ ቀረጡ አሥር ብር ነውና 210 ብር ነው፡፡

የአምስት ሌትር ዘይት ቀረጡ ወደ አምስት በመቶ ሳይወርድ፣ 200 ብር ከዓለም አቀፍ ገበያ ቢገዛና በ40 በመቶ ቀረጥ ታሳቢ ቢደረግ ትራንስፖርቱ ሳይታከል 280 ብር ይደርሳል፡፡

የግዥው ዋጋና ቀረጡ ታክሎ 178.50 ብር የፈጀ አምስት ሌትር ዘይት የትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎች ታክሎበት፣ እንዲሁም የትርፍ ህዳጉ ታሳቢ ተደርጎ ሲሸጥ 400 እስከ 450 ብር መጠየቁ ተጋኗል የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

እንደ ዘይት ሁሉ መንግሥት ታክስ ቅናሽ አድርጌባቸዋለሁ ያላቸው የስንዴና የሩዝ ምርቶችም ገበያውን አልለወጡትም፡፡ ታክስ ከተጣለባቸው ጊዜ በላይ ዋጋ ወጥቶላቸው እየተሸጡ ሲሆን፣ ስንዴን ግብዓት በማድረግ የሚመረቱ ፓስታና ማኮሮኒ ምርቶችም ዋጋቸው ከፍ ብሏል፡፡ ከታክስ ነፃ ይገባል የታባለው የሩዝ ምርትም ቢሆን ከቀደመው ዋጋ በላይ እየተሸጠ ነው፡፡

በመንግሥት የራሱን ገቢ አስቀርቶና ታክስ ቀንሶ እንዲገቡ የተፈቀዱ ምርቶች ሳይቀሩ ዋጋ ጭማሪ የታየባቸው መሆኑን በመገንዘብ፣ ያላግባብ ጭማሪ ያደረጉ ላይ ዕርምጃ ወስጃለሁ ቢልም ዕርምጃው ለውጥ አላመጣም፡፡

የምግብ ነክ ምርቶች ከ20 በመቶ በላይ ጭማሪ እየታየባቸው ስለመሆኑ በተከታታይ የወጡት የጥቅምትና የኅዳር ወር የብሔራዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል፡፡ የዋጋ ግሽበት ለዓመታት የቆየ፣ አሁንም እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ የሁኔታው አሳሳቢነትንም በመገንዘብ በመንግሥት ረገድ የተለያዩ ዕርምጃዎች እንዲወሰድ ያስገደደ ሆኗል፡፡

እንደ ንግድ ሚኒስቴር መረጃ፣ በገበያ ውስጥ እጥረት እንዳይፈጠር ተከታታይ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ በመሆኑ፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት የምርት እጥረት አለ ተብሎ አይታሰብም፡፡

እንዲያውም የአንበጣና የጎርፍ አደጋዎች ያሳረፉት ተፅዕኖ አለ ቢባል እንኳን፣ ከቀደመው ዓመት የተሻለ ምርት እንዳለም እየተጠቀሰ ነው፡፡ ይህም የዋጋ ጭማሪውን ምክንያታዊ አያደርገውም፡፡ በመንግሥት በኩል ዋጋን ለማረጋጋት በተጨባጭ ተሠርቷል የሚባለው ሌላው ሥራ ለአምራችና ለኅብረት ሥራ ማኅበራት 800 ሚሊዮን ብር ብድር ለመስጠትና የምርት አቅርቦትን ለማሳደግ በጀት ስለመያዙ ማስታወቁ ነው፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንዳሉትም፣ ይህ ብድር በዋናነት እያሻቀበ ያለውን የዋጋ ግሽበት መፍትሔ ለማበጀትና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ያለ ችግር ምርቶችን እንዲያቀርቡ ለማገዝ ታስቦ የተወሰደ ዕርምጃ ነው፡፡

መንግሥት ሌሎች ዕርምጃዎችንም እየወሰደ ሲሆን፣ የዋጋ ግሽበቱ አልተገታም፡፡ ባለሁለት አኃዝ ሆኖ የቀጠለውን የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት የተዋቀረው የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ በቅርቡ እንዳሳወቀውም፣ ለዓመታት አገሪቱን እየተፈታተናት የቆየውን የዋጋ ግሽበት ለማሻሻል የተለያዩ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆንም፣ ይህ ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ ሊፈታ የማይችል መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡

የዋጋ ግሽበት በመንግሥት ደረጃ ፈታኝ ስለመሆኑ ሌላው ማሳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ተጨማሪና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቀው አንዱ ችግር የዋጋ ግሽበት መሆኑን በቅርቡ መግለጻቸው ነው፡፡ የመንግሥታቸውን የ2013 በጀት ዓመት የመጀመርያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም በተመለከተ በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ፣ የዋጋ ግሽበትን ለማሻሻል አምና በርካታ ሥራ የተሠራና ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ ገልጸዋል፡፡

እንደ እርሳቸው እምነት፣ የገንዘብ ለውጡ የሚያመጣው አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁንም የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ ሰፊ ሥራ የሚጠይቅና የማክሮ ቡድኑ ራስ ምታት ነው፡፡  

ለኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ኢኮኖሚያዊና ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ምክንያቶች ተደበላልቀው የሚፈጥሩት መሆኑ ችግሩን የሚያከብድ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህንን ችግር መንግሥት በሚያወጣቸው ፖሊሲዎች ብቻ በአጭር ጊዜ ለማከም የማይቻል መሆኑን የማክሮ ኮሚቴ መጥቀሱም የችግሩን አሳሳቢነት የሚጠቁም ነው፡፡ የፕላንና ኢኮኖሚ ኮሚሽነሯም ችግሩን ለማቃለል የመዋቅር ለውጥ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

በአጭር ጊዜ የሚፈታ ያለመሆኑንም በመጥቀስ፣ ችግሩ መዋቅራዊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ሥራ እንደሚጠይቅ መግለጻቸውም የዋጋ ግሽበት በእርግጥ ከዚህም በኋላ የመንግሥት ፈተና ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን ያሳያል፡፡

የዋጋ ግሽበት አሁንም ሰፊ ሥራና ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከዚህ አኳያ የዋጋ ግሽበቱ ገፊ ምንያቶች ምንድናቸው? የሚለውን መዘርዘር በጥልቀት መለየት አንዱ ሥራ ይሆናል ብለዋል፡፡

ችግሩ የማሳሰቡን ያህል ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ስለመኖራቸውና ተጨማሪ ምርት የሚገኝበት አሠራር በመከተል ውጤት የታየባቸው ስለመሆኑ መንግሥት ይገልጻል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ የግብርና ምርት የራሱ ፈተና ቢኖረውም ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ለመኖራቸው አንዱ ማሳያ ብለው የጠቀሱት፣ በመስኖ፣ በኩታ ገጠምና በቴክኖሎጂ ምርት ማሳደግ አንዱ የመፍትሔው አካል በመሆኑ በዚሁ አኳያ እየተሠራ መገኘቱ ነው፡፡

ነገር ግን ምርታማነትን ብቻ ማሳደግ በቂ ያለመሆኑንና የንግድ ሥርዓቱን ማዘመን እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡ የንግድ ሥርዓቱ ከፍተኛ ውስንነት ያለበት እንደሆነ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ወጣ ስትሉ ምርት አለ፡፡ እዚህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት አለ፡፡ ይህንን እንዴት እናገናኛለን የሚለውን ከንግድ ሥርዓቱ በተጨማሪ ሎጂስቲክስ ማዘመን ይፈልጋል፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ለዚህም የመሠረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛውን ሚና የሚይዝ ይሆናል፡፡ ፍላጎትና አቅርቦትን ማጣጣምም እንዲሁ፡፡  

መንግሥት ዋጋን ለማረጋጋት የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ባይኖሩ ኖሮ፣ ከዚህም በላይ የዋጋ ግሽበት ሊከሰት ይችል እንደነበር የሚጠቁሙ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ግን፣ አሁንም መንግሥት በጊዜያዊነት በተለይ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ላይ እጁን በማስገባት ማስተካከል ግድ ይለዋል፣ ገበያውንም ሥርዓት ማስያዝ አለበት ይላሉ፡፡

ይህ ግን ዘላቂ መፍትሔ ያለመሆኑን በመጥቀስ ማክሮ ኢኮኖሚው ላይ አሁንም ብዙ ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡ መንግሥት ታክስ እየቀነሰ የሚያስገባው ምርት ዋጋው እየጨመረ መምጣቱ የግብይት ሥርዓቱ ችግር መሆኑን፣ እየጨመረ ያለው የውጭ ምንዛሪም የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንዳለው ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች