Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበእነ አቶ ጃዋር ላይ ከተመሠረቱት አሥር ክሶች ውስጥ አምስቱ በፍርድ ቤት ተሰረዙ

በእነ አቶ ጃዋር ላይ ከተመሠረቱት አሥር ክሶች ውስጥ አምስቱ በፍርድ ቤት ተሰረዙ

ቀን:

የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ቀጠሮ ተሰጠ

ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ በሚገኙት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ (24 ግለሰቦች) ላይ ተመሥርተው ከነበሩት አሥር ክሶች ውስጥ አምስቱ በፍርድ ቤት ተሰረዙ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥትና የሽብር ወንጀሎች ማስቻያ አንደኛ ወንጀል ችሎት፣ ክሶቹ እንዲሰረዙ ያደረገው ዓርብ ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ቀደም ባለው ችሎት ክሶቹን አሻሽሎ እንዲያቀርብ የተሰጠውን ትዕዛዝ ተግባራዊ ባለማድረጉ ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ጊዜ ተከሳሾች ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ በክሱ ተጠቅሶ የነበረው ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የሚለው ሐረግ ግለሰብ ይሁን ወይም ቡድን ግልጽ እንዲያደርግ የነበረ ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግም ‹‹ቡድን ነው›› በማለት አሻሽሎ አቅርቧል፡፡ ዓቃቤ ሕግ አቶ ሃምዛ አዳነ የተባለው ተከሳሽ ቅስቀሳ ያደረገበትን የሚዲያ ስም እንዲጠቅስ በታዘዘው መሠረት፣ ሚዲያው ኦኤምኤንና በራሱ (በተከሳሹ) ፌስቡክ መሆኑን በመጥቀስ አሻሽሎ ቀርቧል፡፡

በአቶ ጃዋር ላይ ብቻ ተመሥርቶ የነበረው የሽብር ወንጀል ክስ በአዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 6 (2) መሠረት ‹‹መሰናዳት›› በሚል ማሻሻሉን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ከአምስተኛ እስከ አሥረኛ ያሉትን ክሶች ግን አለማሻሻሉን አስታውቋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ከጠቀሳቸው ማለትም የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥር አዋጅ ቁጥር 117/2012 አንቀጽ 4 (1) እና 22 (3) ድንጋጌዎች የተሻለ አንቀጽ መጥቀስ ስላልቻለ ባለበት እንዲቀጥል ለፍርድ ቤቱ ሲያሳውቅ፣ ፍርድ ቤቱ ለ20 ደቂቃዎች ረፍት ወስዶ በጽሕፈት ቤት ከተነጋገረ በኋላ፣ ከአምስት እስከ አሥር ያሉትን ክሶች እንዲሰረዙ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

ተከሳሾቹም የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ሲጠይቅ፣ የተከሳሾች ጠበቆች ደንበኞቻቸውን ያገኛቸው በዕለቱ መሆኑን ገልጸው፣ ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ አጭር ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም በመፍቀድ ለጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቀጠሮውን ሰጥቶ እንደጨረሰ አቶ ጃዋር ባቀረበው አቤቱታ፣ የተከሰሱት በማያስከስስና ወንጀል ባልሆነ ጉዳይ መሆኑን ገልጾ፣ በዋናነት ግን በምርጫ እንዳይሳተፉ ተፈልጎ መሆኑን ተናግሯል፡፡ የጦር መሣሪያን በሚመለከትም መንግሥት ፈቅዶ ፌዴራል ፖሊስ የሰጣቸው እንጂ ሕገወጥ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡ ለአገር ደኅንነት ሲባል በምርጫ መሳተፍ እንዳለባቸውና የቀረውም ክስ ቢሆን ምንም ጭብጥ የሌለው መሆኑን ገልጿል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...