መቀመጫውን በጀርመን ያደረገው ሮክስቶን ሪል ስቴት ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ በአንድ ቢሊዮን ብር ዘመናዊና ኢትዮጵያዊ ውበትን የተላበሱ የመኖሪያ አፓርትመንቶች ልገነባ ነው ሲል አስታወቀ፡፡ ለሕንፃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ሐሙስ ጥር 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ተቀምጧል፡፡
ኩባንያው በኢትዮጵያ የመጀመርያው የሆነውንና 21 ወለሎች ያሉት የመኖሪያ አፓርትመንት ግንባታ ከሦስት ዓመት ባነስ ጊዜ እንደሚያጠናቅቅ፣ የግንባታውን የመሠረት ድንጋይ ሲግናል መኮንኖች መኖሪያ አካባቢ ሲያስቀምጥ ተገልጿል፡፡
ወደፊት ለመካከለኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚመጥኑ የመኖሪያ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገነባ መሆኑን፣ የሮክስቶን ኩባንያ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዲትሪሽ ሮግ ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ ዲዛይንና ሥነ ሕንፃ በአውሮፓውያን አርክቴክቶች እንደሚመራ፣ የግንባታ ሒደቱም ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡
ኩባንያው ‹‹ከፍታ›› በተሰኘው የአፓርትመንት ግንባታ ዓለም አቀፍ ዕውቀቱንና ያካበተውን ልምድ ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የሚያካፍልበት እንደሚሆንም፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለዋል።
ኩባንያው በኢትዮጵያ ውስጥ በዘላቂነት ለመሥራት የመጣ መሆኑን፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና የውጭ ምንዛሪ አጥረትን ለመቋቋም የሚያስችል ዓለም አቀፋዊ አቅም አለው ብለዋል፡፡
ለአዲስ አበባ ከተማ አንድ ተጨማሪ ውበት ይጨምርላታል የተባለው የአፓርታማ ሕንፃ፣ ሁሉንም ዓይነት አገልግሎቶች በአንድ አድርጎ ይይዛል ተብሏል። የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የውበት ሳሎን፣ ሱቆችና የመሳሰሉትን ማካተቱ ተጠቁሟል፡፡
ሕንፃው ሲጠናቀቅ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ነዋሪዎችን ፍላጎት ያማከሉ 100 የመኖሪያ ቤቶች ይኖሩታል ተብሏል።
የሮክስቶን ኩባንያ በቤት ግንባታ ዘርፍ ከተሰማራባቸው አገሮች ጀርመን፣ ስፔንና ፖርቱጋል እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡
ኩባንያው ከሁለት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል፡፡