Friday, July 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ 1.5 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግሪን አግሮ ሶሉውሽን ከተባለ ኩባንያ ጋር፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 1.5 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ፡፡

አዲሱ ‹‹ለእርሻ›› መተግበሪያ ከሲቢኢ ብር ጋር በመቀናጀት ለአርሶ አደሮች ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ፀረ ተባይ፣ ፀረ አረምና መሰል ግብዓቶችን በቀላል የክፍያ ሥርዓት ለማከናወን የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ስምምነቱ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በግሪን አግሮ ሶሉውሽን ኩባንያ መካከል ዓርብ ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ልደታ በሚገኘው የንግድ ባንክ ዛግዌ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተፈረመ ሲሆን፣ ግሪን አግሮ ሶሉውሽን ያቀረበው ‹‹ለእርሻ›› የተሰኘው መተግበሪያ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ የሚሆነው 85 በሚሆን የግብርና ባለሙያ ወኪሎች አማካይነት መሆኑ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ ሚሊዮን እንደገለጹት መተግበሪያው ግብይቱን ከማቀላጠፍ ባለፈ፣ የሲቢኢ ብር አገልግሎትን በመጠቀም የግብርና ግብዓቶችን መግዛት የሚያስችልና እግረ መንገዱን ባንኩ የሚሰጣቸውን የተለያዩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም አርሶ አደሮቹ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ድረስ መሄድ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ሥፍራ ሆነው የክፍያ አገልግሎት በማግኘት፣ ጊዜና ጉልበታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማገዝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

መተግበሪያውን ለሚጠቀሙ ወኪሎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሲቢኢ ብር አገልግሎት መጠቀም እንደሚያስችል የገለጹት አቶ ዮሐንስ፣ ለአካባቢው ኅብረተሰብ አገልግሎቱን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል፡፡

የግሪን አግሮ ሶሉውሽን ኩባንያ መሥራች አቶ አብርሃም እንድሪያስ በበኩላቸው፣ አገልግሎቱን እስከ 2017 ዓ.ም. ድረስ 1.5 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡  

አንድ አርሶ አደር በትራንስፖርት ተጉዞ ግዥ ለመፈጸም 17 በመቶ ወጪ እንደሚያወጣ የገለጹት አቶ አብርሃም፣ በመተግበሪያው ለመጠቀም የሚከፈለው ደግሞ ስምንት በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የክፍያ አፈጻጸሙን በተመለከተ አርሶ አደሮቹ የፈለጉትን የግብርና ምርት በወኪሎቻቸው አማካይነት ከደረሳቸው በኋላ፣ ክፍያው ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

የ‹‹ለእርሻ›› መተግበሪያ በአማርኛ፣ በኦሮሚኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን፣ የድምፅ፣ የምሥልና የአጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ እንዲሁም የጥሪ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል መሆኑን የኩባንያው መሥራች ተናግረዋል፡፡

መተግበሪያው በአርሲና በምዕራብ አርሲ ዞኖች በአሥር ወረዳዎች ውስጥ የሚተገበር መሆኑን፣ አሁን ከአሥሩ በሁለቱ ወረዳዎች ተግራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በባሌ፣ በምሥራቅ ጎጃምና በሰሜን ሸዋ በስፋት ለመሥራት ጥናት እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አብርሃም፣ በ2014 ዓ.ም. ሦስቱ ዞኖች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን አህመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በዲጂታል ዘርፍ የሚደረገው እንቅስቃሴ በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥልና አርሶ አደሮችም በቴክኖሎጂ በታገዘ አሠራር ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 78 ዓመታት ውስጥ ከ27.5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ፣ አሁን የተደረገው ስምምነት ደንበኞችን ከማብዛትና ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች