በናይል ሳት ይተላለፉ የነበሩ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቻናሎች ወደ አዲሱ ኢትዮሳት የተደረገው የግዳጅ ሽግግር የዲሽና ተዛማጅ ዕቃዎች ዋጋ እያሻቀቡ መሆኑንና ተቃሚዎችን ለወጪ መዳረጉ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ዘርፍ ማኅበር ከኤስኢኤስ (SES) ሳተላይት ጋር ባደረጉት ስምምነት መሠረት፣ ኢትዮሳት የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች የሚያስተላልፉበት ሳተላይት እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል፡፡ የሳተላይት ለውጡ ለዲሽ ቴክኒሻኖች የሥራ ዕድል ቢፈጥርም፣ አገልግሎቱ የሚተላለፍባቸው የኤችዲ (HD) መቀበያዎች፣ ሳህኖችና ሌሎች ተዛማጅ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማጋጠሙን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች አስታውቀዋል፡፡
አቶ ዮናታን መገርሳ በቄራ አካባቢ በዲሽ ገጠማ ሥራ ላይ የተሰማራ ሲሆን፣ የአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ወደ ኢትዮሳት መግባት ከጀመሩበት ታኅሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጾ፣ ነገር ግን የኤችዲ መቀበያዎች ዋጋ ቀድሞ ከነበረበት 800 ብር አሁን የ200 ብር ጭማሪ፣ እንዲሁም በሳህኖች ላይ በተመሳሳይ የ200 ብር ጭማሪ መደረጉን ገልጿል፡፡
በአንዋር መስጊድ አካባቢ የኤሌክትሮኒክስ ሱቅ ባለቤት የሆነው አቶ ፉአድ አህመድ እንደሚለው፣ ቀደም ብሎ ከውጪ ምንዛሪ ጋር በተገናኘ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ዋጋ ጨምሯል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ በዲሽና ተዛማጅ ዕቃዎች ላይ ፍላጎት በመጨመሩ፣ እስከ 200 ብር የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ እንዳለ ገልጿል፡፡
በአዲሱ ሳተላይት ኤስዲ (SD) ጥራት አለው በሚባለው የመቀበያ ዓይነት የሚተላለፉት ቻናሎች በቁጥር 14 ብቻ የሚደርሱ በመሆናቸው፣ በርካታ የሳተላይት ቻናሎች ለማግኘት ኤችዲ (HD) ሪሲቨር እንደሚያስፈልግ የሚገልጸው አቶ ዮናታን፣ በዚህም ሳቢያ የመቀበያና የዲሽ ሳህን ፍላጎት እንደጨመረ አስረድቷል፡፡
ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር የኢትዮሳት መምጣት ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ከዚህ በፊት የተገለጸ ሲሆን፣ ሽግግሩን መሠረት በማድረግ ቁጥራቸው 20 ሺሕ የሚደርሱ ቴክኒሻኖችን በማሠልጠን ለሥራ ማሰማራቱን መግለጹ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ዘርፍ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ እንደሻው ወልደ ሚካኤል፣ ስለሳተላይት ሽግግሩ እንዲሁም አገልግሎቱ እንዴት በቀጣይ እንደሚሠራ እንዲያስረዱ ሪፖርተር ለማነጋገር የተደረገው ጥረት የእጅ ስልክ ባለማንሳታቸውና ለጽሑፍ መልዕክትም ምላሽ ባለመስጠታቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡