የአፍሪካ እግር ኳስ ኮፌዴሬሽን (ካፍ) በአፍሪካ የውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ለማበረታት በሚል ያዘጋጀው የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) በካሜሮን አስተናጋጅነት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ካፍ ውድድሩን በመሐል ዋና ዳኝነትና ረዳት ዳኝነት እንዲመሩ ከመረጣቸው 47 የእግር ኳስ ዳኞች ውስጥ በዋና ዳኝነት ኢትዮጵያዊቷ ሊዲያ ታፈሰ ብቸኛዋ እንስት ሆናለች፡፡
ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ቅዳሜ ምሽት ጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በናሚቢያና በታንዛኒያ መካከል የተደረገውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት አጫውታለች፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ጨምሮ የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ያጫወተችው ሊዲያ፣ አፍሪካ ካፈራቻቸው እንስት የእግር ኳስ ዳኞች ውስጥ የመሐል ዋና ዳኛ በመሆን ቀዳሚዋ ሆናለች፡፡
እንደ ሊዲያ ሁሉ የዓለም ዋንጫን ጨምሮ የተለያዩ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች በመምራት የሚታወቀው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማም በቅዳሜ ምሽቱ ጨዋታ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ጨዋታ ሲመራ ታይቷል፡፡