Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ያገናዘበው የአዋሽ ኢንሹራንስ ስምምነት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ተደራሽነት እጅግ ዝቅተኛ ከሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ከጠቅላላ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ድርሻው ከሦስት በመቶ በታች ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉትም፣ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ወቅታዊ አቋም በንፅፅር ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሲታይ፣ በሁሉም መመዘኛዎች ዝቅተኛ ነው፡፡

አብዛኞቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በውስን አገልግሎት ብቻ የሚንቀሳቀሱ፣ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ያገናዘበ አገልግሎት የሌላቸውና በቴክኖሎጂ ያልተደገፉ በመሆናቸው ኢኮኖሚያዊ አበርክቷቸው እጅግ ዝቅተኛ ሆኗል፡፡

በተለይ እንደ ባንክ ካሉ የፋይናንስ ዘርፍ ጋር በንፅፅር ሲቀመጡም ተደራሽነታቸውም ሆነ የአገልግሎት ስፋታቸው አነስተኛ ሆኖ መቆየቱ እያደገ ከመጣው የአገር ኢኮኖሚ ጋር የተናበበ አገልግሎት ለመስጠት እንዳላስቻላቸውም የዘርፉ ባለሙያዎች ያመለክታሉ፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙትም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጥቅል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የመድን ሽፋናቸው ከሞተር ወይም ከተሽከርካሪ የመድን ሽፋን ጋር የተያያዘ ሆኖ ለዓመታት መዝለቁ ብዙ የመድን ሽፋን ሊሰጥባቸው የሚችሉ አገልግሎቶችን አለመሥራታቸውን ያመለክታል፡፡

ይህ ኢንዱስትሪ አሁን ካለበት አነስተኛ የሚባል አስተዋጽኦ ተላቆ ሽፋኑን ለማስፋት እየተደረገ ያለው ጥረት እምብዛም በሆነበት ወቅት፣ አዋሽ ኢንሹራንስ ለኩባንያውም ሆነ ለአጠቃላይ ለኢንዱስትሪው ዕድገት ይበጃል ያለውን ስትራቴጂ ለመቅረፅ ዲሎይት ከተባለው ዓለም አቀፍ አማካሪ ኩባንያ ጋር ስምምነት ማድረጉን አስታውቋል፡፡

አዋሽ ኢንሹራንስ የኩባንያውን የአሥር ዓመት ስትራቴጂ ዕቅድ፣ ዲሎይት ዓለም አቀፍ አማካሪ ኩባንያ እንዲቀርፅለት ሐሙስ ጥር 13 ቀን 2013 ዓ.ም.  ስምምነት አድርጓል፡፡ በዘርፉ ልምድ ያላቸውን ኩባንያዎች በማወዳደር ዲሎይትን እንደተመረጠም አስታውቋል፡፡ ለኩባንያውም ለኢንዱስትሪውም ይበጃል የተባለውን ስትራቴጂ ዕቅድ ሥራ በይፋ ማስጀመሩንም በዕለቱ ገልጿል፡፡  

‹‹ትራንስፎርሚንግ አዋሽ ኢንሹራንስ ራዕይ 2030›› የሚል ፕሮጀክት በመቅርፅ የስትራቴጂክ ማማከር አገልግሎት ለመስጠት የተመረጠው ዲሎይት ኮንሰልቲንግ፣ የአሥር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱን በሦስት ወራት ውስጥ የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ ስለዕቅዱ አፈጻጸምም የአንድ ዓመት ድጋፍ የሚሰጥ ይሆናል፡፡  

እስካሁን ስትራቴጂክ ዕቅድ በመቅርፅና በመተግበር ባንኮች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በኢንሹራንስ ኩባንያ ደረጃ ስትራቴጂውን በውጭ ኩባንያ በማሠራት ወደ ትግበራ ለመግባት እየተሠራ መሆኑን የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጉዲሳ ለገሠ አመልክተዋል፡፡ ከዚህ ስምምነት አገርን የሚጠቅም ሥራ ይሠራል ብለው እንደሚጠብቁም አክለዋል፡፡

ኩባንያቸው የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ዘርፍ የሚለወጥበትን መንገድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲህ ያለውን ስምምነት ስለማድረጉም ጠቅሰዋል፡፡

በአማካሪ ድርጅቱ በኩል ከፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ ከሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ በኩባንያው በኩል የሚሰጥ የአገልግሎት ይዘትና የአሠራር ሒደትን መፈተሽ፣ ክፍተቶችን መለየትና በአገልግሎት፣ ይዘትና አሠራር ሒደት ላይ ማሻሻያዎችን ማቅረብ ይገኙበታል፡፡

ለአሥር ዓመት የስትራቴጂ ሰነድ ማዘጋጀትና የአሥር ዓመት አፈጻጸም ፍኖተ ካርታ ማውጣት የሚካተት ሲሆን፣ አማካሪ ድርጅቱ የስትራቴጂ ክትትልና ግምገማ ድጋፍን ለኩባንያው መስጠት ይጠበቅበታል፡፡

አዋሽ ኢንሹራንስ ከዲሎይት አማካሪ ድርጅት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት፣ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የኩባንያውን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል የላቀ ተወዳዳሪ ኩባንያ ለመሆን ያለውን ፍላጎት በሥራ ላይ እንዲያውልም ይጠበቃል ተብሏል፡፡

በተለይም በንግድ ዘርፍ ውስጥ ያሉትን አዳዲስ ለውጦች ከግምት በማስገባት የኩባያውን ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ የስትራቴጂ ግብዓቶች ከፕሮጀክቱ እንደሚገኙም ታምኗል፡፡ ኩባንያው የቀረፀው የራዕይ 2030 ፕሮጀክት የተሳካ እንዲሆን ከዚህ ስምምነት ብዙ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

አቶ ጉዲሳ እንደገለጹትም፣ በስምምነቱ መሠረት የሚተገበረው የስትራቴጂክ ዕቅድ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ክፍተት በመመልከትና ወደፊት የኩባንያው አካሄድ ምን መሆን እንደሚኖርበት በማጥናት የተሻለ አሠራርን ይፈጥራል፡፡

ስትራቴጂያቸውን አስጠንተው ወደ ሥራ የገቡ ባንኮች ለውጥ አምጥተዋል ያሉት አቶ ጉዲሳ፣ ‹‹በኢንሹራንስ ዘርፍ ብዙ ያልተሠሩ ሥራዎች ስላሉ እኛም የኩባንያውን ስትራቴጂ ቀርፀን መተግበር ውጤታማ እንሆናልን፤›› ብለዋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅዱ ሲተገበር አዋሽ ኢንሹራንስን በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚሆን ያመለከቱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህንንም ለማድረግ የዲሎይት ልምድ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ቀረፃው አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ያለበትን ደረጃና በአጠቃላይም የአገሪቱን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በመፈተሽና በመተንበይ ኢንዱስትሪው ውስጥ ውስን የሆኑትን የመድን ሽፋን ዓይነቶች ለማብዛትና አዳዲስ ገበያዎችን ለመፍጠር ያስችላል፡፡

የኢንሹራንስ ተደራሽነቱ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ይህንን ክፍተት ለይቶ ለአዋሽ ኢንሹራንስ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ለኢንዱትሪው ሊያገለግል የሚችል ቴክኖሎጂ ይቀረፃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ጉዲሳ ገልጸዋል፡፡

ከዲሎይት ጋር ከስምምነቱ በፊት በነበረ ምክክር የዲሎይት ፍላጎት የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያን መለወጥ ብቻ ሳይሆን የቁጥጥር ሥርዓቱን መቀየርንም ግምት ውስጥ ያስገባ ነው ተብሏል፡፡

18ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2012 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን 11.6 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚሆነው ከሕይወት ኢንሹራንስ የተሰባሰበ ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላላ ከተሰበሰበው ዓረቦን የሕይወት ኢንሹራንስ ድርሻ አምስት በመቶ አካባቢ እንደሚሆን ያሳያል፡፡ እንዲህ ያለውን የዘርፉን ክፍተት ለመሙላት በስትራቴጂካዊ ዕቅድ መመራት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኗል፡፡    

አዋሽ ኢንሹራንስ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ17ቱ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በቀዳሚነት ከተመሠረቱት አንዱና 26 ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡

1.2 ቢሊዮን ብር የተፈቀደና ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ያለው ነው፡፡ በተጠናቀቀው የ2012 የሒሳብ ዓመት ከ893 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን የሰበሰበ መሆኑና ከታክስ በፊት ከ221 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡ ይታወቃል፡፡ የኩባንያው የሀብት መጠን ሰኔ 2012 መጨረሻ ላይ 2.9 ቢሊዮን መድረሱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች