በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ አበርክቶ ካላቸው የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ማይክሮ ፋይናንሶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ 43 ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ወስደው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ 39 በኢትዮጵያ ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማኅበር የታቀፉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ከበደ ይገልጻሉ፡፡
ብዙውን ጊዜ የማኅበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የፋይናንስ ተቋማት ልማትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ልማቱን ለማገዝ ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ይንቀሳቀሳሉ፡፡
በቀደመ መልኩ የተለመደው የባንክ ዘርፍ አገልግሎት፣ ለገጠሩም ሆነ ለከተማው ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ባለመሆኑ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ለእነዚህ ተደራሽነት ለመሆንና ችግሩን ለመቅረፍ ወደ ሥራ ከገቡ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት አነስተኛ ይዘት ያላቸው የፋይናንስ ድጋፎችን በብድር፣ በቁጠባና በአነስተኛ መድን መልኮች ያቀርባሉ፡፡ ብዙዎቹ የማይክሮ ፋይናንስ ደንበኞች አነስተኛ ገቢ ያላቸው ገበሬዎች፣ ከብት አርቢዎች፣ ሴቶችና ማይክሮ ኢንተርፕራይዞች ናቸው፡፡
እስከ ሰኔ 2011 ዓ.ም. ድረስ አጠቃላይ ተበዳሪዎች ቁጥር አምስት ሚሊዮን ሲሆን፣ የባንክ ተበዳሪዎች ቁጥር ደግሞ 280 ሺሕ ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነት ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ነው፡፡
የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት የ2012 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም ሲታይም፣ ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 59.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ለብድር ያዋሉት ደግሞ 41.3 ቢሊዮን ብር መድረሱን ያመለክታል፡፡ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በአምስት በመቶ ማሳደጋቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ እዚህ ደረጃ የደረሱ ቢሆንም፣ በቴክኖሎጂ ያልተደገፉ ሆነው ቆይተዋል፡፡
ተቋማቱ በሁሉም ረገድ ዕድገት እያስመዘገቡ ቢሆንም፣ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንፃር ያለባቸውን ክፍተት በጥናት ጭምር በመገለጹ፣ ተቋማቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስተሳሰር አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ጥር 13 ቀን 2013 ዓ.ም. የዚሁ አካል የሆነው 25 ማይክሮ ፋይናንሶች በኮር ባንኪንግ የማስተሳሰሩ ሥራ ተጠናቆ በይፋ ወደ ትግበራ መገባቱ ተገልጿል፡፡
የማክሮ ፋይናንስ ተቋማትን ለማዘመን ይቻል ዘንድ ወደ ሥራ የገባው ኢቲ-ኢንክሉሲቭ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማኅበር፣ ከዚሁ የኮር ባንኪንግ ትስስሩ ጋር በመሆን ተጨማሪ ሥራዎችን ለመሥራት መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
እስካሁንም በኢቲ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማኅበር በኩል የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ አክሲዮን ኩባንያው ክልልን መሠረት ባደረጉ አምስት ጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ተመሥርቶ በአሁኑ ወቅት በ30 የፋይናንስ ተቋማትና ግለሰቦች ባለቤትነት ይዞታ ሥር የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡
ኢቲ ብቸኛ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማኅበር ኤም ብር የተሰኘውን የመጀመርያው ውሁድ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ ግብይቶች የጋራ መገበያያ መተግበሪያ አገልግሎት አቅራቢ ሆኗል፡፡ የሞባይል መተግበሪያን በመጠቀም የገንዘብ ዝውውርን፣ ክፍያን፣ ቁጠባንና የጥሬ ገንዘብ ወጪዎችን በክልል ዋና ዋና ከተሞችና በአዲስ አበባ ለማከናወን ያስችላል፡፡
ኢቲ ከአምስት ዓመት በፊት በ2015 ዓ.ም. የገንዘብ ዝውውሩ ከሃምሳ ሺሕ ብር ያልበለጠ የነበረ ቢሆንም፣ በ2020 መጨረሻ ላይ 1.43 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የግብይት መጠኑ በገንዘብም ሆነ በሚያንቀሳቅሰው የገንዘብ መጠን ዕድገት አሳይቶ በ2015 ዓ.ም. ከነበረው 14.4 ሚሊዮን ብር 14.7 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የግብይቱ መጠንም በተመሳሳዩ ወቅት ከነበረው 38.7 ሚሊዮን 1.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሞባይልና ወኪል ባንኪንግ አገልግሎቶችን እንዲሁም ኤምአይኤስ (ኮር ባንኪግ ሲስተም) አገልግሎቶችን በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ለ25 ጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የማስፋፋት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትን ወደ ቀጣዩ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ ውጤታማ መሆኑ ታምኖበት ወደ ትግበራ መገባቱም ታውቋል፡፡
ይህ በማክሮ ፋይናንስ ተቋማቱ ጥምረት የተቋቋመው አክሲዮን ኩባንያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አገልግሎቶቻቸውን እንዲሰጡ የሚያስችላቸው ሲሆን፣ ይህም ተደራሽነታቸውን፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸውንና በአጠቃላይ ዕድገታቸውን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየተሰጠ ያለው ቅርንጫፎች በመክፈት ነው ያሉት አቶ ተሾመ፣ ወደፊት ግን የኮር ባንኪንግ አገልግሎቶችን ጨምሮ የአገልግሎት አሰጣጥ አማራጮችን እየሰፋ እደሚሄድ፣ ቅርንጫፎችን እየከፈተ ሳይሆን በኤጀንት ባንኪንግ፣ በሞባይል ባንኪንግ፣ በኢንተርኔት ባንኪንግ ኤትኤምና በመሳሰሉ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች ሥራው ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ ትልቁ ሞተር ስለመሆናቸው የጠቀሱት አቶ ተሾመ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራም የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የተጀመሩ ቢዝነሶችን ለማስፋት አዲስ ለሚጀምሩም ሙሉ የመነሻ ካፒታል ለመስጠት የሚመረጡትና ያሉትም አማራጮች እነዚህ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት በመሆናቸው፣ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ቀጣይ ሥራዎችን ለማከናወን የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑም ታውቋል፡፡