Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከብዝበዛ አላቁን!

እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ጉልህ ችግሮች ተብለው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ውስጥ የመኖሪያ ቤት አንዱ ነው፡፡ አብዛኛው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የራሴ የሚለው መኖሪያ ቤት የለውም፡፡ በአቅሙ ተከራይቶ ለመኖርም በቂ አቅርቦት የለም፡፡ ቤት ተከራይቶ ለመኖር ቢሻም አሁን ያለውን የቤት ኪራይ ዋጋ ተቋቁሞ ለመጓዝ እጅግ ከባድ እየሆነበት ነው፡፡

ቤት ገንብቶ ለመኖር የሚያስችል አቅም ቢኖር እንኳን፣ ምቹ ሁኔታ ያለመኖሩና በዚያው ልክ ፍላጎቱ እያደገ መቀጠሉ ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ይበጃሉ የተባሉ የቤት ግንባታ ፕሮግራሞች በተግባር የማዋል ሥራ ስለመኖሩ ባይካድም፣ በአግባቡ ባለመተግበሩ ችግሩን ሊፈታው አልቻለም፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ለዓመታት የተከማቸውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል እንደ መፍትሔ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች ውስጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ  ፕሮጀክቶች በቀዳሚነት ቢጠቀሱም በአግባቡ አልተሠራባቸውም፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች ካለው እጅግ የሰፋ ፍላጎት አንፃር ችግሩን ለማቃለል አበርክቷቸው የጎላ ቢሆንም፣ በአተገባበር ደረጃ የታየባቸው ግድፈት ዘላቂ መፍትሔ እንዳይሆኑ አድርጓል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ካለው የመኖሪያ ቤት እጥረት አንፃር ከኪራይ ዋጋ ጋር ተያይዞ እየታየ ያለው ችግርን መፍታት ግን ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ ቤት ሠርቶ ለመኖር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ከጠበበ ቢያንስ መንግሥት የኪራይ ዋጋን ለምን አይቆጣጠርልንም እስከማለት እየተደረሰ ነው፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክቶች በአግባቡ ተተግብረው ቢሆን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ንረትን ሊያረግቡ ይችሉ ነበር፡፡ በአግባቡ እንዲተላለፉ አለመደረጋቸውና በተዝረከረከ የግንባታ ማኔጅመንት በመመራታቸው ለቤት ችግር የሚመጥን መፍትሔ እንዳይሆኑ አድርጓል፡፡

ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር ከግለሰብና ተጠቃሚዎች ባሻገር፣ ለአገር ሀብት ብክነትም ሆኗል፡፡ በፖለቲካው ተጠልፎ ዜጎች ቆጥበው ቤት ለማግኘት የሚያስችላቸውን ተስፋ ሁሉ ያጨለመ መሆኑም በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡

በኮንዶሚኒየም ዙሪያ የተፈጸሙ አሳዛኝ ድርጊቶች በርካታ ቢሆኑም፣ እሱን ለጊዜው እንተወውና አሁን በአዲስ አበባ ከተማ የምናየው የመኖሪያ ቤቶች የኪራይ ዋጋ ጉዳይ ግን የበለጠ አሳሳቢ መሆኑን ተረድቶ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል፡፡ የራሴ የሚሉት ቤት የሌላቸው ዜጎች የቤት ኪራይ ዋጋ ወገባቸውን እያጎበጠው ነው፡፡ ሠርተው ለመኖሪያ ቤት ኪራይ እየከፈሉ ነው፡፡

የኑሮ ውድነቱ አንዱ መገለጫም ይኼው እንደተፈለገ የሚቆለለው የቤት ኪራይ ዋጋ ነው፡፡ ውድነቱ የብዙዎች ምሬት ከሆነ የከረመ ሲሆን፣ አሁን ላይ ደግሞ እየባሰበት መምጣቱን ተረድቶ ሃይ የሚል ያለመኖሩ አከራዮች እንዳሻቸው እንዲሆኑ እያደረገ ነው፡፡

መንግሥት የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለማቃለል የሚያግዙ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በአግባቡ እንዲገነቡና እንዲተላለፉ አለማድረጉና አሁን ላይ ደግሞ ጭራሽ ግንባታዎቹን እንደማያካሂድ መወሰኑ ችግሩን ያባብሰዋል፡፡ ያላግባብ እያደገ የመጣው የቤት ኪራይ ዋጋን ያለመቆጣጠሩ ደግሞ ድርብ ተወቃሽ ያደርገዋል፡፡

በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የቤት ኪራይ ዋጋን የሚወስኑት ደላሎች መሆናቸውም የችግሩ አካል ነው፡፡ ተከራዮች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዲንከራተቱ፣ አከራዮችን ጭምር በመጠምዘዝ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ደላሎች ስለመሆናቸው ሲታሰብ፣ በዚህች አገር ኢኮኖሚ ውስጥ የደላሎች እጅ ረዝሞ እስከመቼ ይዘለቃል? የሚለውን ጥያቄ ደጋግመን እንድናነሳ ያደርገናል፡፡  

የራሳቸው መኖሪያ ቤት እያላቸው የቀበሌና የጋራ መኖሪያ ቤት ባለቤት የሆኑ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦችን ሃይ ማለት አለመቻሉም የችግሩ አንድ ገጽታ ነው፡፡ ዜጎች ንብረት አፍርተው ተጠቃሚ የመሆን መብታቸው የተጠበቀ ስለመሆኑ እርግጥ የመሆኑን ያህል፣ አገልግሎታቸው በአግባቡ እንዲሆንም ይጠበቃል፡፡ አቅም ኖሯቸው ቤት ገንብተው ችግሩን በማቃለላቸው ማመስገንም ተገቢ ነው፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው ባልተገባ የቤት ኪራይ ዋጋ እንዲበዘበዙና ደላሎች እንደፈለጋቸው ይፈንጩበት ማለት ግን አግባብ አይሆንም፡፡

በዚህ ጉዳይ በብርቱ ሊታወስ የሚገባው የመኖሪያ ቤት ዋጋ እየናረ መምጣት ቀውስ ሊሆን እንደሚችል ታምኖ ሲሠራበት እንደነበር ነው፡፡ ይህም መንግሥት የመኖሪያ ቤቶች ዋጋ ራሱን የቻለ ተመን ኖሮት እንዲስተናገድ የሚያስችል ሕግ  ማርቀቅና ችግሩን ለማቃለል ያለመ ነበር፡፡

ይህ ረቂቅ ሕግ ግን ሕግ ሆኖ ሳይወጣ ለዓመታት አቧራ እንዲጠጣ የተደረገበት ምክንያት ግራ ያጋባል፡፡ ረቂቅ ሕጉ በተለይ በአከራይና ተከራይ መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት ሁሉ ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑ ረቂቁ በቀረበበት ወቅት መገለጹም ይታወሳል፡፡ የቤት ኪራይ ዋጋ በዘፈቀደ እንዳይሆንና ገበያን ያገናዘበ ሆኖ እንዲሠራበት የሚያስችልም ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ቤት ገንብቶ ማከራየት ሕጋዊ ሥራ ሆኖ እንዲቀጥልና ሌሎችም እንዲበረታቱበት በማድረግ ረገድ ያግዛል ቢባልም ረቂቁ የውኃ ሽታ ሆኗል፡፡  

ለዋጋ ግሽበት አንዱ መንስዔ ሆኖ የቆየውን የቤት ኪራይ ዋጋ ማረጋጋት ችግሩን ለመፍታት ያግዛል፡፡ የተጋነነ የኪራይ ዋጋ የሚጠየቀው በመኖሪያ ቤቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በንግድ ቤቶችም ነው፡፡ ገበያውን የማይመጥን ዋጋ በመቆለልና ይህንንም በማራገብ ተመከራይቶ መስራት የሚፈልገውን አምክኗል፡፡ የንግድ ቤት ኪራይ ዋጋ ከፍተኛ መሆኑም ሸመታው ላይ ዋጋን ማናሩ አይካድም፡፡ ስለዚህ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ የሚያስችሉ የተፈተሹ አሠራሮችን ከመተግበር ባሻገር፣ የኪራይ ዋጋን መቆጣጠር ተገቢ ነው፡፡  ምክንያቱም ኢኮኖሚው ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ ቀላል አይደለምና፡፡፡

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋን የተመለከተው ረቂቅ ሕግ በቶሎ መውጣቱ አንድ መፍትሔ ይሆናል፡፡ ለምን እንዲዘገይ እንደተፈለገም ልናውቅ ይገባል፡፡ በቶሎ ሕጉ እንዲወጣ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡

የግሉ ዘርፍ በዚህ ሊኖረው የሚችለው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፣ በአብዛኛው ብዙኃንን ሊደርሱ በማይችሉ ቅንጡ ቤቶች ግንባታ ላይ ብቻ ማተኮራቸው አንድ ችግር ነው፡፡ ሆኖም አሁንም ወጪ ቆጣቢ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት መፍትሔ አካል ሊሆን ይችላል፡፡

ለዚህ አሳሳቢ ችግር የተሻሉ አማራጮችን ለመተግበር የመንግሥትም ድርሻ ወሳኝ ነው፡፡ ይህ እኛ ተከራዮችን ካላስፈለጊ ብዝበዛ ነፃ ያወጣናል፡፡ ከብዝበዛ አላቁን!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት