የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች የመረጧቸውን የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቶች እንዲቀይሩ፣ ማክሰኞ ጥር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡
በዚህም መሠረት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ የመረጠው ምልክት ከዚህ በፊት በነበረ ምርጫ ሌላ ፓርቲ ሲጠቀምበት የነበረ በመሆኑና ፓርቲው የቀድሞ ምልክቱን ለመጠቀም በመጠየቁ፣ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የመረጠው ምልክት ከዚህ በፊት በነበረ ምርጫ ሌላ ፓርቲ ሲጠቀምበት የነበረ በመሆኑና ፓርቲው የቀድሞ ምልክቱን ለመጠቀም በመጠየቁ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የመረጠው ምልክት ከዚህ በፊት በነበረ ምርጫ ሌላ ፓርቲ ሲጠቀምበት የነበረ በመሆኑና ፓርቲው የቀድሞ ምልክቱን ለመጠቀም በመጠየቁ፣ የምዕራብ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከሌላ ፓርቲ ምልክት ጋር ምልክቱ የተቀራረበ በመሆኑ፣ እንዲሁም የአርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከሌላ ፓርቲ ምልክት ጋር ምልክቱ የተቀራረበ በመሆኑ ነው እንዲቀይሩ በምርጫ ቦርድ ማሳሰቢያ የተሰጣቸው፡፡
ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የፓርቲዎች የምርጫ ምልክት መረጣ እየተከናወነ እንደሆነ አስታውሶ፣ በዚህም መሠረት እስካሁን ድረስ 45 ያህል ፓርቲዎች ምልክቶቻቸውን ያስገቡ መሆናቸውን በመጠቆም፣ የተጠቀሱት ፓርቲዎች የመረጧቸውን ምልክቶች ቀይረው እንዲያቀርቡ ጥሪ ማድረጉን አስታውቋል።
‹‹የምርጫ ምልክቶቻችሁን ያላስገባችሁ፣ እንድትቀይሩ የተገለጸላችሁ ወይም መቀየር የምትፈልጉ እስከ ጥር 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ እንድታጠናቅቁ ቦርዱ እያሳሰበ፣ የፀደቁ ምልክቶችንና የፓርቲዎችን ዝርዝር ሒደቱ ሲጠናቀቅ ይፋ ይደረጋል፤›› ሲል ምርጫ ቦርዱ አክሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሕጋዊ ኃላፊነት በተሰጠው አካል ምልክቱን እንዲመርጥ ጥያቄ ቀርቦለት፣ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የምርጫ ምልክት ማስገባታቸውን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ጥር 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ለምርጫ ምልክትነት ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ ምልክቶችን በማዘጋጀት የፓርቲ ተወካዮች ከተዘጋጁት ምልክቶች ሊወክለኝ ይችላል የሚሉትን እንደሚመርጡ፣ የመረጡት ምልክት በፓርቲያቸው የተያዘ መሆኑን እንዲያስመዘግቡ፣ ፓርቲዎች ያስመዘገቡት ምልክት ከሚመረጡ ምልክቶች ዝርዝር ውስጥ እንደሚወጣ፣ በቦርዱ ከተዘጋጀው ምልክት ውስጥ የሚፈልጉትን ምልክት ያላገኙ ወይም የራሳቸውን ምልክት ማስመዝገብ የሚፈልጉ ፓርቲዎች ያወጣቸውን መሥፈርቶች ማሟላት እንዳለባቸው ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
መጪው አገር አቀፍ ምርጫ ለፌዴራልና ለክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች፣ እንዲሁም ለአዲስ አበባና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ለማካሄድ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው።