የተሳታፊ አትሌቶች ቁጥር ቀንሷል
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወቅቱን ጠብቆ ሳይካሄድ የቆየው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ እሑድ ጥር 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ሱልልታ ከተማ ላይ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከሥልጠና ማዕከላትና ከክለቦች የተውጣጡ ከ600 በላይ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ላለፉት ዓመታት በዋናነት የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶችን በብዛት ሲሳተፉበት የቆየው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ፣ ዘንድሮ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የአገር ውስጥ አትሌቶች ብቻ የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡ እንደ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ፣ የተሳታፊ አትሌቶች ቁጥር ምን ያህል ነው የሚለው በውል አልታወቀም፡፡ ይሁንና ከአንድ ክልል በስተቀር ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከክለቦችና ከሥልጠና ማዕከላት የተውጣጡ በሁለቱም ጾታ ከ600 በላይ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የፌዴሬሽኑ የውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ ያስረዳሉ፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ውድድሩን አስመልክቶ ሐሙስ ጥር 20 ቀን መግለጫ እንደሚሰጥ ያስረዱት አቶ አስፋው፣ በዚህ ውድድር የሚሳተፉ አትሌቶች እስከ ቅዳሜ ጥር 22 ቀን ድረስ ከ48 እስከ 72 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ የኮቪድ ምርመራ በማድረግ ለፌዴሬሽኑ ሪፖርት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭን ጨምሮ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለሚያዘጋጃቸው የአገር ውስጥ ውድድሮች ዝግጅት የሚያደርጉ አትሌቶች መቀነሱን የሚናገሩ አሉ፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ አትሌቶች፣ ወረርሽኙን ተከትሎ የሚደመጠው ወሬ በተለይም ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ብዙዎቹ ተስፋ እንዲቆርጡ እያደረጋቸው ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳሉ፡፡
አንድ አትሌት ለአንድ ውድድር ቢያንስ ከሁለትና ከሦስት ወር በላይ ዝግጅት እንደሚያደርግ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ሁሉ ልፋትና ድካም በኋላ ነው ዕድል የቀናው አሸናፊ የሚሆነው፡፡ የቀረው ነገ ሌላ ቀን ነው በሚል ተስፋ ሰንቆ ወደ አሰልቺውና አድካሚው ዝግጅት ይመለሳል፡፡ አሁን ላይ ግን ወረርሽኙ ሁሉንም ነገር እያበላሸው ይመስላል፡፡ ችግሩ በተለይም ወቅታዊ ለሆነው አትሌቲክስ ክፉ ዕጣ ፈንታ ነው፡፡
‹‹የአንድ አትሌት ትልቁ ስኬት በሁለት ዓመት አልያም በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና ኦሊምፒክ ላይ መሳተፍ ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ትልልቅ መድረኮች መሳተፍ ውጤት ባይመጣም ለአንድ አትሌት ትልቅ ስኬት ቢሆንም፣ አሁን የምንሰማውም ሆነ ዓለም እየተጋፈጠችው ያለው ጉዳይ ለእነዚህ ሁሉ ተግዳሮት ሆኗል፤›› የሚሉት እነዚህ አትሌቶች ለጃንሜዳው ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ዝግጅት መዳከም በምክንያትነት ይነሳሉ፡፡