Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዓለምሶማሊያ ከምርጫ አስቀድሞ የገጠማት ግጭት

  ሶማሊያ ከምርጫ አስቀድሞ የገጠማት ግጭት

  ቀን:

  በሶማሊያ ውጥረት ነግሷል፡፡ የተንኮታኮተው የፖለቲካ ሥርዓቷም ከወር በኋላ ሊደረግ የታሰበውን ምርጫ ከወዲሁ እየፈተነው ነው፡፡ የአሜሪካ ጦር ከሶማሊያ መውጣትም የአገሬው ሚሊሻዎች ዳግም እንዲያንሰራሩ ያስችላል የሚል ሥጋት አንግሷል፡፡ ታዛቢዎች ደግሞ፣ ለሦስት አሠርታት የዘለቀው የእርስ በርስ ግጭት ረገብ ብሎ አገሪቱ ወደ ሰላም ማቅናት ስትጀምር የአሜሪካ ጦር መውጣቱ የመልሶ መረጋጋቱን አደጋ ላይ ጥሎታል ብለዋል፡፡

  ከዓምና ለዘንድሮ የተራዘመውና ከወር በኋላ ይደረጋል የተባለው ምርጫም፣  ብጥብጥ ሊያስነሳ ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ምርጫው መደረግ የነበረበት ዓምና ቢሆንም፣ በጎሳ የተደራጁ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ምርጫው ሊጭበረበር ይችላል በሚል ከምርጫ ራሳቸውን በማግለላቸው ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡

  የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ የቀድሞው ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሁሴን ሼኪ ዓሊ ‹‹ምርጫው ዳግም በታቀደለት ጊዜ ካልተካሄደ ወደ ጥፋት የመቀየር ዕድል አለው፡፡ ሁሉም ኅብረተሰብ የሶማሊያ ዴሞክራሲ አደጋ ውስጥ እንዳለ ያውቃል፣ ይህንን ማስተካከል አለብን፤›› ሲሉም ለቀጣዩ ወር የታቀደው ምርጫ እንዲካሄድ መክረዋል፡፡

  ሶማሊያ ከምርጫ አስቀድሞ የገጠማት ግጭት

   

  ሶማሊያ ምርጫውን ለማካሄድ ስትዘጋጅ ከጁባላንድ ክልላዊ ጦር የገጠመችው ጦርነት ግን ሌላ ችግር አስከትሏል፡፡

  በደቡብ ሶማሊያ የፌዴራል ክልል የሆነችው ጁባላንድ ወታደሮች በቡሎ ሃዎ ከተማ ጦርነት መክፈታቸውን የሶማሊያ ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን፣ ጦርነቱን የደገፈችው ኬንያ ናት ሲልም ወቅሷል፡፡

  ከኬንያ የምትዋሰነው ጁባላንድ ወታደሮች ከሶማሊያ መከላከያ ጋር ከፍተኛ ውጊያ ማድረጋቸውን የዘገበው አልጀዚራ፣ ከሁለቱም ወገን ‹‹አሸንፌያለሁ›› የሚል መግለጫ መሰጠቱንም አክሏል፡፡

  የሶማሊያ መንግሥት በኬንያ የሚደገፉ ሸማቂዎች ጦርነት ከፈቱብን ቢልም፣ የጁባላንድ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ሞሐሙድ ሰኢድ ኦዳን፣ ምርጫውን ለማካሄድ አስቀድሞ የሶማሊያ መንግሥት ያሰፈራቸው ወታደሮች ጥቃት ፈጽመዋል ብለዋል፡፡

  ማዕከላዊ መንግሥት በከተማዋ ባሰፈራቸው ወታደሮች ጥቃት መፈጸሙን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንት ሞሐመድ፣ ክልላዊ መንግሥታቸው የማዕከላዊ መንግሥት ወታደሮች በከተማው መስፈራቸውንም እንደማይደግፍ አስታውቀዋል፡፡

  ሁለቱም ወገኖች አሸንፈናል ቢሉም ጦርነቱ በመቀጠሉ የአካባቢው ነዋሪዎች መሰደድ መጀመራቸውን አልጀዚራ አስፍሯል፡፡

  የሶማሊያ ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ከተማዋን መቆጣጠሩን ሲያሳውቅ፣ ስለደረሰው ጉዳት ያነሳው ነገር የለም፡፡

  የሶማሊያ መንግሥት ‹‹የአገሪቱን አንድነት፣ ሉዓላዊነትና መረጋጋት ለመጠበቅ›› በማለት ከኬንያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካቋረጠ በኋላ ‹‹ኬንያ አሸባሪዎችን እየረዳች ነው፤›› ሲል መኮነን ጀምሯል፡፡ አሁን የተደረገውን ጦርነትም የኬንያ እጅ አለበት ብሏል፡፡

  የፖለቲካ ተንታኞች ግን፣ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ማዕከላዊ ወታደሮችን ወደ ጁባላንድ በመላክና ውጥረት በመፍጠር ለሁለተኛ ጊዜ እንዲመረጡ ቀልብ ለመሳብ ያደረጉት ነው ይሏቸዋል፡፡

  ባለፈው መስከረም ላይ፣ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ጁባላንድ ከሚገኝበት የጌዶ ግዛት ማለትም አሁን ጦርነቱ በተቀሰቀሰበት ቡሎ ሃዎ ከተማ ጦራቸውን ለማስወጣት ተስማምተው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ይህ ጦር በቡሎ ሃዎ የሰፈረውም ዓምና ነበር፡፡

  ፕሬዚዳንት አብዱላሂ በጁባላንድ ፕሬዚዳንት አህመድ ሞዶቤ የተሾመውን የጌዶ ኮሚሽነር በሌላ መተካታቸውም የክልሉን አስተዳደር አስቀይሞ ነበር፡፡

  ጁባላንድ የኪስማዩ ወደብ ከተማ ስትሆን፣ የኬንያ ጦር የአፍሪካ ኅብረት ጥምር ጦር አካል ሆኖ የሰፈረበት ነው፡፡ የጁባላንድ መካከለኛው አካባቢም አሁንም ድረስ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አለው በሚባለው አልሸባብ ታጣቂ ቡድን ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ነው፡፡

  በሶማሊያ ከምርጫ በፊት የተደቀነ ሥጋት

   ሶማሊያ በሰላም ለመኖርም ሆነ ላለመኖር አሁን ወሳኝ ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡ በመሆኑም ከወር በኋላ የሚደረገውን ምርጫ በሰላም ማጠናቀቅ ላይ ሊሠራ እንደሚገባ ዓለም አቀፍ ተቋማት መክረዋል፡፡

  የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል የሶማሊያ ፖለቲከኞች ውይይት እንዲያደርጉ ጥሪ በማቅረብ ‹‹ማንኛውም ግጭት ተቀባይነት የለውም›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

  በሶማሊያ በጎሳ መሪ መከፋፈሏ ብቻ ሳይሆን ዛሬም የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን መኖሩ ሥጋት ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት እንደተጠናከረ የሚነገርለት ቡድኑ፣ አሁንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግብር እንደሚሰበስብ ቢቢሲ የፕሬዚዳንት አብዱላሂ የቀድሞ አማካሪን ጠቅሶ አስፍሯል፡፡

  ‹‹አልሸባብን ማፍያ ነው›› ብሎ ማናናቅ ተገቢ እንዳልሆነ፣ የተጠናከረ ስትራቴጂክ ራዕይ ያለው፣ በምክንያት የተደራጀ ቡድን መሆኑም፣ ነገር ግን አልሸባብን እንደሌለ መቁጠርና ራስን መደለል እንደማይገባም ዓምና በሞቃዲሾ በታጣቂዎች የጋየው ኤሊት ሆቴል ባለቤት አብዱላሂ ኖር ተናግረዋል፡፡

  በሶማሊያ ያለው መሠረታዊ ችግር እዚህም እዚያም የሚነሱ ግጭቶች ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ አለማግኘታቸው ነው፡፡ ሶማሊያ ምን ዓይነት አገር መሆን እንዳለባት የሚያንፀባርቁ የተለያዩ አመለካከቶችም አሉ፡፡ እነዚህን ልዩነቶች የሚያጎሉ አሊያም ለራሳቸው ፍላጎት ማስፈጸሚያ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም አሉ፡፡ ሆኖም አገሪቱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ለውጥ አስመዝግባለች ሲሉ በሶማሊያ የእንግሊዝ አምባሳደር ቤን ሬንደር ተናግረዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...