Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሕዝቡ እንዲሳተፍበት የሚጠበቀው ጤና መድን

ሕዝቡ እንዲሳተፍበት የሚጠበቀው ጤና መድን

ቀን:

የጤና መድን አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ ክፍያ ግለሰቦች ወይም ቤተሰቦች የጤና መታወክ ባጋጠማቸው ጊዜ በነፃ ሕክምና ማግኘት የሚያስችል ስልት ነው፡፡ አነስተኛ የቅድመ ክፍያ ስልት መዋጮን በአንድ ቋት በማጠራቀምና የተሻለ የገንዘብ አቅም በመፍጠር ለሕዝቡ ፍትሐዊ፣ ጥራት ያለውና ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያገኝም ያስችላል፡፡ በገንዘብ ዕጦት ምክንያት በቂ ሕክምና ያለማግኘት ሥጋትንም ያስወግዳል፡፡

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዓይነት የጤና መድን ሥርዓቶችን ተግባራዊ ለማድረግ መሥራት ከጀመረች ከአምስት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ አንደኛው ማኅበራዊ የጤና መድኅን (ማጤመ) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን (ማአጤመ) ነው፡፡ የመጀመርያው ሥርዓት በመደበኛ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማሩትን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ በበርካታ የአውሮፓ፣ እስያና አፍሪካ አገሮች እየተተገበረ ያለ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በተግባር ላይ ለማዋል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ ናቸው፡፡ ሁለተኛው የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ሥርዓት ግን፣ በከተማና በገጠር መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሰማርቶ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል በተለይም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ሆኖ እየተተገበረ ነው፡፡  

አቶ ዘመድኩን አበበ የኢትዮጵያ የጤና መድኅን ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽንና ሞቢላይዜሽን ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ፣ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሚገኙ 13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ የተጀመረው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ከሙከራ የተገኘውንም ልምድ በመቀመር ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን እንቅስቃሴ በሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በሚገኙ 827 ወረዳዎች ተጀምሮ፣ 771 ወረዳዎች ቅድመ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ለአባላቶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው የሕክምና አገልግሎት መስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በእነዚህም ወረዳዎች የሚኖሩ 6.9 ሚሊዮን አባወራ/እማወራዎች በአባልነት የተመዘገቡ ሲሆን፣ በእነርሱ ሥር የሚገኙ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ጨምሮ ከ35 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎች በጤና መድኅን ሥርዓቱ እንደታቀፉ ተናግረዋል፡፡

በጤና መድኅን ሥርዓት የታቀፉት ዜጎች አሁን ካለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ፣ ከዚህም ግንዛቤ በመነሳት የተጠቃሚዎችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ቀጣይነት ያለውና የተጠናከረ ሥራ መከናወን እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያወጣችው የጤና መድኅን ሥርዓት ማንኛውም የጤና መድኅን አባልና ቤተሰብ በጥቅም ማዕቀፍ የተካተቱትን 37 ዓይነት የተመላላሽ፣ የተኝቶና የቀዶ ጥገና ሕክምናዎችን እንዲሁም የኤምአርአይ እና የሲቲ ስካን፣ የኢኮካርዲዮግራፊ፣ የላቦራቶሪ ምርመራዎች፣ ዲያግኖስቲክስና የመድኃኒት አገልግሎቶች የማግኘት መብት እንዳላቸው አቶ ዘመድኩን ተናግረዋል፡፡

ሕሙማን በማንኛውም የመንግሥት ሕክምና ተቋም በተመላላሽ፣ የተኝቶ ሕክምና ከማድረግ በተጨማሪ ቀላልና ከፍተኛ ቀዶ ሕክምናዎችን፣ ስፔሻላይዝድ ቀዶ ሕክምና ለምሳሌ የልብ፣ የነርቭ፣ የአንጎል ቀዶ ሕክምናና ሌሎች አገልግሎቶችን ሆኖም ሕክምና አገልግሎት የማይሰጥባቸው አሉ፡፡ ከእነዚህም የወርቅ ጥርስ ማስተከልና የውበት መጠበቂያዎች እንደሚገኙበት ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን የታቀፉት አባላት በዝርዝር የተጠቀሱትን የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙት በዓመት አንድ ጊዜ በሚያዋጡት መዋጮ ነው፡፡ አከፋፈሉ የኅብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ የተከተለ፣ የየአካባቢያቸውን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥና የአየር ንብረቱን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡

የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን የአባልነት ምዝገባና የነባር አባላት የዕድሳት ጊዜ በየዓመቱ ጥር ላይ እንደሚከናወን አቶ ዘመድኩን ገልጸው፣ በዚህም መሠረት ጥር የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ወር ተብሎ እንደተሰየመ አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አባላት ምዝገባና የነባር አባላት የዕድሳት ጊዜ ጥር ወር መጨረሻ ላይ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚቀርቡ የምዝገባ ጥያቄዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡

በየዓመቱ ግለሰቦች የሚያደርጉትን መዋጮ እንደየአካባቢው የሚወሰነው ኅብረተሰቡ ተሰብስቦ ነው፡፡ እስካሁን ያለው ልምድ የሚያሳየውም ዝቅተኛው 240 ብር በዓመት ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 550 ብር ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...