Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ትልምና ጉዞው

በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ በአፋር ክልል መዲና የሚገኘው ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከተመሠረተ ከአሥራ ሁለት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በሦስት ፋኩልቲዎች 12 የትምህርት ክፍሎች 1,867 ተማሪዎችን በመቀበል የማስተማር ተግባሩን የጀመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በሰባት ኮሌጆችና አንድ ትምህርት ቤት፣ 41 የትምህርት ክፍሎች (ዲፓርትመንት) በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት ከ10,000 በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ዩኒቨርሲቲው በቅርብ ከጀመራቸው አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች መካከል የአፋር ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ፣ አግሪ ቢዝነስ፣ ኬሚካል ኢንጂነሪንግ (የስኳር ቴክኖሎጂ) ይገኙበታል፡፡ በተመሳሳይም ዩኒቨርሲቲው የዓረቢኛ ቋንቋ፣ የባቡር ኦፕሬሽን አስተዳደርና የወደብ አገልግሎት አስተዳደር ትምህርት ለመክፈት እየተዘጋጀ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ ያለው ተግባርና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አቡበከር ያሲን ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ታምራት ጌታቸው እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት ጊዜያት በዩኒቨርሲቲዎች ሁከት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችሁ እንዴት አሳለፈው?

አቶ አቡበከር፡- በዩኒቨርሲቲያችን ከብጥብጡ በፊትም ሆነ በኋላ ችግር ሳይፈጠር ነው ያለፈው፡፡ ግጭትም ተከስቶ አያውቅም፡፡ ይህም ሰላማዊ ዩኒቨርሲቲ እንዲባል አስችሎታል፡፡ ይህም ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን የኅብረተሰቡ ባህልና እሴት፣ ተማሪዎቻችን እርስ በርስ ያለው ግንኙነት ጤናማ መሆኑ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ ባለመኖሩ፣ የተማሪዎች ኅብረት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያለው መሆኑ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ማንኛውም ተማሪ ያለውን ቅሬታ ለአስተዳደሩ የማቅረብ ሙሉ መብት ከመኖሩ ባለፈ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ዳጉ የሚባለው የመረጃ ሥርዓት ችግሮች እንዳይፈጠሩ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮቪድ-19 የተባለው ወረርሽኝ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ ይታወቃል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ይህንን ችግር እንዴት ተወጣው? በዚህስ ላይ ለማኅበረሰቡ የሰጠው ምን አገልግሎት አለ?

አቶ አቡበከር፡- እንደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በዚህም ትልቅ ችግር መፈጠሩ ይታወሳል፡፡ ዛሬም ያለ ቢሆንም በወቅቱ ተማሪዎችን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን ወደ ማኅበረሰቡ በማድረግም የማስተማርና የማስገንዘቢያ ሥራ ከማከናወኑም ባለፈ፣ ኮቪድን ለመከላከል የተለዩ ፈጠራዎችን በማከናወን፣ ሳኒታይዘር በማምረት፣ ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያ በመሥራት የኮቪድ-19 ሙቀት መለኪያን ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ከዩኒቨርሲቲው ራቅ ላሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች አቅርቧል፡፡ የመከላከሉን ሥራ ተማሪዎች እስኪመለሱ ድረስ እየሠራ የቆየ ሲሆን ይህንኑ ዝግጅት ሰፋ በማድረግ የኮቪድ መከላከል በሚፈቅደው ፕሮቶኮል መሠረት የተማሪዎች ማደሪያ፣ የመማሪያና የመመገቢያ ክፍሎችን እንዲሁም ቤተ መጻሕፍትን ሰፋ አድርጎ በማዘጋጀት ተማሪዎች ተቀብለን እያስተማርን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በአሁን ወቅት ምን ያህል ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል?

አቶ አቡበከር፡- ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በአሁን ወቅት ከአሥር ሺሕ በላይ ተማሪዎች፣ ከ41 ዲፓርትመንት፣ ሰባት ፋክልቲ፣ አንድ ትምህርት ቤት ያለው ሲሆን ከአንድ ሺሕ በላይ መምህራንና 1,400 በላይ የአስተዳደር ሠራተኛ አሉት፡፡

ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ትልልቅ ግንባታዎችን ማካሄድ ጀምሯል፡፡  እነዚህ ግንባታዎቹ ምንድን ናቸው?

አቶ አቡበከር፡- ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ጀምሮ ግንባታም ሆነ ማስፋፊያ ሳያደርግ ነው የቆየው፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ዕድገትና ምርምር፣ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ላይ ክፍተት ፈጥሮ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲው ግንባታ ባለመካሄዱ ችግር ውስጥ ያስገባው የሠራተኞች ፍልሰት ነበር፡፡ ይህም ከእሱ እኩል ከተቋቋሙት ዩኒቨርሲቲዎች ወደኋላ እንዲቀርም አድርጎታል፡፡ እነዚህንና ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች በዩኒቨርሲቲውና በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ የተለያዩ ግንባታዎች እያተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የአካባቢውን የአየር ንብረት ያገናዘቡ ግንባታዎች ሲሆኑ በአንድ ጊዜ ሦስት ሺሕ ተማሪዎችን የሚያስተናግድ ዲጂታል ላይብረሪ፣ እያንዳንዳቸው ባለ ሦስት መኝታ ቤት የመምህራን መኖሪያዎች፣ ከተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና የማደሪያ ክፍሎች ትላልቅ የመመገቢያ አዳራሾች የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና ሌሎችም በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡-  እስከ ዛሬ ግንባታ ያልተካሄደው ለምንድነው?

አቶ አቡበከር፡- ግንባታ እስከዛሬ የዘገየበት ምክንያት ትምህርት ሚኒስቴር የሚመድበው በጀት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲንና ሰመራን ዩኒቨርሲቲ እኩል ባህሪ በመስጠት የሚመድበው በጀት ሊያሠራ ባለመቻሉ አንዱና ትልቁ ምክንያት ነው፡፡ ከ11 ዓመት ጭቅጭቅ በኋላ ለአካባቢው የሚስማሙ ግንባታዎች እንዲከናወኑ በመፈቀዱና ገንዘቡም በመገኘቱ ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ግንባታውም ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ የሚጠናቀቅ ሲሆን ከ17 ሺሕ በላይ ተማሪዎች በመቀበል ከፍተኛ የውጭ ተመራማሪዎችን በመሳብ ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲውን የሚገዳደረው ምንድነው?

አቶ አቡበከር፡- ዩኒቨርሲቲው የሚገኘው ታዳጊ ክልል ውስጥ በመሆኑ ብዙ ጫና አለበት፡፡ የክልሉ ጫና ሁሉ እኛን ይመለከታል፡፡ ተፅዕኖ የሚያሳድረው አንደኛው የመሠረት ልማት ያለመስፋፋት፣ እንደ ልቡ ተንቀሳቅሶ ቶሎ ኅብረተሰቡ ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን ለማውጣት ያገደው በመሆኑ ለኅብረተሰቡ ሩቅ ሆነናል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በረሃ ላይ በመሆኑ ወጪውም ከፍተኛ ነው፡፡ ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ የገንዘብ ዝውውሩ ደካማ ነው፡፡ ሌላው አንዳንድ የክልሉ ቢሮዎች ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተቀራርቦ ከመሥራት ይልቅ ከዩኒቨርሲቲው  ብቻ መጠበቅና እንደ አንድ የዕርዳታ ድርጅት አድርጎ መመልከት ይንፀባረቃል፡፡ ያሉበትን እነዚህን ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ በተለይ ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኅብረተሰብ ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ አቡበከር፡- ዩኒቨርሲቲው እንደ ዕድል ሆኖ በርካታ ሥራዎችን በሚፈልግ ክልል ውስጥ የተቋቋመ በመሆኑ በርካታ ምርምሮችን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በብዙ ምክንያቶች ግን እየተመራመረ አይደለም፡፡ በትንሹም ቢሆን ግን በሁሉም ዘርፎች ምርምሮችን እያካሄደ ይገኛል፡፡ አብዛኛው ማኅበረሰብ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ነው የሚኖረው፡፡ ለምሳሌ በእንስሳት ሀብቱ ላይ ለሚከሰተው በሽታ መድኃኒት ለመሥራት ለእንስሳቱ የቅርብ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ አብሮ መዞርን ይጠይቃል፡፡ ወይም እንስሳቱን አንድ ቦታ በማቆየት ምግባቸውን፣ መጠለያቸውን ውኃቸውን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው አካባቢው በረሃማ በመሆኑ ከፍተኛ የውኃ ችግር አለ፡፡ ይህንን ለመቅረፍ የተለያዩ ምርምሮች ቢሠሩም ቆፍሮ ለማውጣት ግን ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ይጠይቃሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዓመት ለማኅበረሰብ አገልግሎት ያለው በጀት ከአምስት ሚሊዮን ብር አይበልጥም፡፡ በዚህም ግን በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች የአካባቢ ጥበቃን በአብዛኛው የተራቆቱ መሬቶችን በማልማት በረሃማነትን እየቀነሱ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ አትክልትና ፍራ ፍሬዎች በምርምር በማውጣት ኅብረተሰቡ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ በዚህም ከ1,200 በላይ አባወራዎች ተጠቃሚ ናቸው፡፡

በማኅበረሰብ ድጋፍ በኩል በአካባቢው ላሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አስተማሪን ከመመደብ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ ለተለያዩ በክልሉ ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ሥልጠና ይሰጣል፡፡ በሽታዎች ሲከሰቱ ቡድን በማዋቀር የሕክምና ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ለምሳሌም በቅርቡ በእንስሳት ላይ ተከስቶ የነበረውን በሽታ ከስድስት ወረዳዎች በላይ በመድረስ ከ25 ሺሕ በላይ በግ፣ ፍየል፣ እንዲሁም ግመሎችን ክትባት በመስጠት ለማዳን ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ወደፊት ምን አስቧል?

አቶ አቡበከር፡- ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው ወደ ዓረቡ ዓለም መውጫ ላይ ነው፡፡ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድን የሚያገናኝ በመሆኑ አገራችን የሚገባትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማግኘት እንደ ድልድይ ለመሆን ያስባል፡፡ ሌላው ዩኒቨርሲቲው በክልሉ የሚደረገውን ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት፣ በምርምር ውጤት፣ የተማሪ ቅበላን አቅም በማሳደግ በቀጣናው ያለውን ድርሻ በማሳደግ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ተመራጭ ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች