Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርፖለቲካዊ (ቤተ ነጋሲ) ጋብቻ

ፖለቲካዊ (ቤተ ነጋሲ) ጋብቻ

ቀን:

በዕዝራ ኃይለ ማርያም መኮንን

አፄ ምኒልክ በ1900 .ም. ሚኒስትሮችን ሲሾሙ ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስን የንግድና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አደረጓቸው፡፡ እቴጌ ጣይቱ አፄ ምኒልክ በሕመም ላይ ሳሉ በአፄ ምኒልክ ስም አድራጊ ፈጣሪ ስለነበሩ ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስን ተጣሏቸው፣ ለመውደቅም ተቃረቡ፡፡ ነጋ ድራስም የእቴጌይቱን ወንድም ልጅ ወ/ሮ የተመኙ አሉላን አግብተው እንደ ገና ተነሱ፡፡

አፄ ምኒልክ ልጅ ኢያሱን አልጋ ወራሽ፣ ራስ ቢትወደድ ተሰማን ደግሞ የልጅ ኢያሱ ሞግዚት አደረጉ፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ሥልጣን ሲዳከምና የመንግሥቱን ሥራ ሞግዚቱ መሥራት ሲጀምሩ በነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ ላይ ተቀናቃኝ ተነስቶባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ተሻሩ፡፡ እሳቸው ግን ወዲያው የእቴጌ ጣይቱን ወንድም ልጅ ወ/ሮ የተመኝን ፈቱና የራስ ቢትወደድ ተሰማን ልጅ ወ/ሮ ላቀችን አግብተውም ቀኞቻቸውን አሳፈሩ፡፡ ቢትወደድ ተሰማ አርፈው ሥልጣኑን ልጅ ኢያሱ ጠቅልለው ሲይዙ አሁንም ሥልጣናቸው አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ ወ/ሮ ላቀችን ፈተው የልጅ ኢያሱን ታላቅ እህት ወ/ሮ ስዒን ሚካኤልን ኅዳር 6 ቀን 1907 .ም. አገቡ፡፡ በዚህ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት ተጨምሮላቸው ቢትወደድ ተባሉ፡፡ በኢትዮጵያም ለመጀመርያ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ ‹‹የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ›› በተባለው መጽሐፍ ላይ ገልጸዋል፡፡

በጋብቻ ኃይልን ማደራጀትና መተሳሰር በመላው ዓለም ይሠራበት የነበረ ነው፡፡ ጋብቻ ትውልድን ከማስቀጠያነቱም በላይ የፖለቲካ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በጉልታዊ ሥርዓት ትውልድና ጋብቻ መንግሥታዊ ሥልጣንን ለመመሥረት፣ ኃይለኛውን ለማለዘብና የራስ ወገን ለማድረግ መሠረት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ አዳጊዎች በመስዋዕትነት ሲዳሩ ሲኳሉ ኖረዋል፡፡

ይህ መጣጥፍ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበረውን ፖለቲካዊ ወይም ቤተ ነጋሲ ጋብቻ ከፖለቲካ ጋር ያለውን መስተጋብር ይመለከታል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ በ1848 .ም. ሸዋን ካስገበሩ በኋላ ምኒልክን በምርኮ ወስደዋቸው መቅደላ አምባ ላይ በቁም እስር ለአሥር ዓመት ኖረዋል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ልጃቸውን አልጣሽን ቢድሩላቸውም ምኒልክ ትተዋት ሰኔ 24 ቀን 1858 .ም. ከመቅደላ አምባ አምልጠው ሸዋ ገብተው ነገሡ፡፡ ምኒልክ አባ ማስያስያች ሴትከሚሏቸው በዕድሜ የብዙ ታላቃቸው ከሆኑት፣ የመርሐ ቤቴ ባላባት ወ/ሮ ባፈና ፍቅር ተነደፉ፡፡

ወይዘሮዋ ከተለያዩ ባሎች ስምንት ልጆች የወለዱ፣ መልከ መልካም፣ ብልህና ዘማዊ ነበሩ፡፡ የምኒልክ ሕጋዊ ሚስት ሆነው ልጅ ይወልዱላቸው ዘንድ ምኒልክን እንዲያግቧቧቸው አቡነ ማስያስን ማስቸገራቸው አልቀረም፡፡ ምኒልክ ከባፈና ጋር የጀመሩት ፍቅር በአባ ማስያስ፣ በመኳንንትና በመሳፍንት ዘንድ አልተወደደም፡፡ ይልቁንም ምኒልክን ለማጥፋት ባፈና ሴራ ማድረጋቸውን መኳንንቱና መሳፍንቱ በመጠቆም ከእሳቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ስለመከሯቸው የፍቅር ግንኙነታቸውን እንዳቋረጡ ‹‹እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ›› መጽሐፍ ላይ ተመልክቷል፡፡

ከመቅደላ አምባ አምልጠው ንጉሥ ምኒልክ ዘንድ የመጡት ወንድማማቾቹ አሉላና ወሌብጡል ስለእህታቸው ጣይቱ ብጡል ብልህነትና አስተዋይነት ለምኒልክ ይነግሯቸዋል፡፡ ከምኒልክ በአራት ዓመት የሚበልጡት ጣይቱ ሸዋ እንዲመጡ ተደርጎ ሚያዝያ 25 ቀን 1875 .ም. በአንኮበር መድሐኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከምኒልክ ጋር በቅዱስ ቁርባን ተጋቡ፡፡ እቴጌ ጣይቱ መሃን ሲሆኑ፣ እቴጌ ጣይቱ በብርታታቸው ቃላቸው የሚደመጥና ነገራቸው የሚሰማ በሰላሙም ሆነ በጦርነት ጊዜ ለምኒልክ ቀኝ እጅ፣ ለዙፋናቸው ግርማ ሞገስና ለመንግሥታቸውም አዕማድ ነበሩ፡፡ ዘመዶቻቸውን ከታላላቅ የምኒልክ ባለ ሥልጣናት ጋር በማጋባት ኃይላቸውን አጠናክረዋል፡፡

የወንድማቸው ልጅ የሆኑትን ራስ ጉግሳ ወሌ ከዘውዲቱ ምኒልክ፣ የወንድማቸው የልጅ ልጅ የሆነችውን አስቴር መንገሻን ከልጅ ኢያሱ ጋር፣ የሸዋው ታዋቂ መስፍን ታዬ ጉልላቴን (በዘ ልማዳዊ የትውልድ ሐረግ መሠረት ታዬ ጉልላቴ ለዘውዱ ወራሽነት ከአቤቶ ኢያሱ ቀጥሎ ከማንም ይበልጥ ብቃት ነበራቸው) ከአስቴር መንገሻ ታላቅ እህት ከአልማዝ መንገሻ ጋር አጋብተዋል፡፡

አፄ ምኒልክ በታመሙበት ጊዜ በምኒልክ ስም የመንግሥቱን ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡ ከአፄ ምኒልክ ባለ ሥልጣኖች ከግማሽ በላይ የነበሩት የእቴጌ ጣይቱ የሥጋ ዘመዶች እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ እቴጌ ጣይቱ በፖለቲካ ጋብቻ ወገን ማብዛታቸው በሌሎች ዘንድ ሥጋት መፍጠሩ አልቀረም፡፡ የሸዋ ባለ ሥልጣናት ተሰባስበው እቴጌ በመንግሥት ሥራ መግባታቸውን ትተው አፄ ምኒልክን እንዲያስታምሙ፣ ከዚህ በፊት ያደረጉትን ሹም ሽር እንዲያነሱና የመንግሥቱንም ሥልጣን ለራስ ቢትወደድ ተሰማ እንዲተውላቸው ተወሰነ፡፡ ጥር 1908 .ም. እንጦጦ በግዞት እንዲቆዩ ተወስኖ በግዞት ባሉበት የካቲት 4 ቀን 1910 .ም. አርፈዋል፡፡

ወ/ሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ራስ ሚካኤልን ከማግባታቸውና ኢያሱን ከመውለዳቸው በፊት የራስ ጎበና ዳጨን ልጅ ደጃዝማች ወዳጆ ጎበናን አግብተው ወሰን ሰገድ የተባለ ልጅ ወልደው ነበር፡፡ ወሰን ሰገድን ዳግማዊ ምኒልክ የዙፋናቸው ወራሽ ሊያደርጉት አስበው በቤተ መንግሥታቸው ውስጥ በእንክብካቤ እያሳደጉት ሳለ በአንዳንዶች አጻጻፍ በ18 በሌሎች ደግሞ በ20 ዓመቱ ሞቶ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መቀበሩን ታደለ ገድሌ (ዶ/ር) መዝሙረ ምኒልክ ዘዳግማዊ በሚለው መጽሐፉ ላይ ገልጿል፡፡ ኦሮሞው ወሰን ሰገድ በልጅነቱ ባይቀጭ ኖሮ የዳግማዊ ምኒልክን አልጋ በቀጥታ ወራሽ ይሆን ነበር፡፡

‹‹የንጉሥ ልጅ በአንቀልባና በማደጎ ይሄዳል››

አፄ ዮሐንስ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በነበሩበት ዘመን፣ ንጉሥ ምኒልክ በአፄ ዮሐንስ ስር ሸዋና ደቡብ ኢትዮጵያን ይገዙ ነበር፡፡ ‹‹አፄ ዮሐንስ ከእንግዲህ ወዲህ ለእኔም ያለኝ አንድ ወንድ ልጅ ብቻ ነው፡፡ ለንጉሥ ምኒልክም ያለቻቸው አንዲት ሴት ልጅ ብቻ ናትና የእኔ ወንድ ልጅ የንጉሥ ምኒልክን ሴት ልጅ ያገባ እንደሆነ እኛም ብንሞትና ብናልፍ የሁለታችንም ዘር በአልጋው እንዲቀመጥ ሴት ልጅዎን ለልጄ ይስጡልኝ፤›› ብለው ታላላቅ መኳንንትን ወደ ንጉሥ ምኒልክ ላኩ፡፡

ንጉሥ ምኒልክም ‹‹ልጅቱ የስድስት ዓመት ሕፃን ናት፣ አልደረሰችም እንጂ ምን ከፋኝ፣. . . ጃንሆይ ፈቃዳቸው ከሆነ፣ የእኔም ፈቃዴ ነው›› አሉ፡፡ አፄ ዮሐንስም ‹‹የንጉሥ ልጅ በአንቀልባና በማደጎ ይሄዳል (ሄዶ ይዳራል) ግድ የለም›› ብለው መለሱ፡፡ በዘመኑ የራስ አርዓያ ዕድሜ 12 ዓመት፣ የዘውዲቱ ደግሞ ስድስት ዓመት ነበር፡፡ ወ/ዘውዲቱና ራስ አርዓያ ጥቅምት 13 ቀን 1875 .ም. ወረኢሉ ላይ በታላቅ ሠርግ በተክሊልና በቁርባን ተጋቡ፡፡ ጋብቻቸው ለአምስት ዓመት ከሰባት ወር ፀንቶ ከቆየ በኋላ ራስ አርዓያ ሥላሴ ሰኔ 19 ቀን 1880 .ም. መቀሌ ላይ አረፉ፡፡

የሐዘኑ ወራት እንዳለፈ አፄ ዮሐንስና ንጉሥ ምኒልክ ለጦርነት ይገማመቱ ነበር፡፡ ወ/ሮ ዘውዲቱ በሁለቱ ንጉሦች መካከል የተነሳው ፀብ እየከረረ መሄዱን እንደሰሙ ‹‹ባሌ ራስ አርዓያ ባይሞቱ ኖሮ አባቴና ጃን ሆይ (አፄ ዮሐንስ) በታረቁ ነበር›› ብለው ተናገሩ፡፡ አፄ ዮሐንስም የወ/ሮ ዘውዲቱን አሳዛኝ ንግግር ሰምተው አልቅሰዋል፡፡ ከዚህ በኋላ አፄ ዮሐንስ ወ/ሮ ዘውዲቱን በመኳንንት አሳጅበው ወደ አባታቸው ንጉሥ ምኒልክ እንደሸኙዋቸው ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ›› አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነትበሚለው መጽሐፋቸው ጽፈዋል፡፡

/ሮ ዘውዲቱ ከመጀመርያ ባላቸው ሞት በኋላ ከደጃዝማች ጓንጉል ዘገየ አንዲት ሴት ልጅ ቢወልዱም በሁለት ዓመቷ ሞታለች፡፡ ቀጥሎም ለደጃዝማች ውቤ አጥናፍ ሰገድ ተድረው ለአራት ዓመት ከቆዩ በኋላ ተፋቱ፡፡ በ1893 .ም. የእቴጌ ጣይቱ ወንድም ልጅ የሆኑትን ደጃዝማች ጉግሳ ወሌን አገቡ፡፡

ዳግማዊ ምኒልክ በ1901 ዓ.ም. በታመሙ ጊዜ ከአባታቸው ጎን ሳይለዩ አስታመዋል፡፡ ልጅ ኢያሱ አክስታቸው ወ/ሮ ዘውዲቱን ከአባታቸው ልጅ ከራስ ገብረ ሕይወት ጋር ለማጋባት ቢጥሩም፣ ወ/ሮ ዘውዲቱ የቁርባን ባሌን ራስ ጉግሳ ወሌን ፈትቼ ሌላ አላገባም በማለታቸው ራስ ጉግሳን ከታሰሩበት ከአፍቀራ አስመጡላቸው፡፡ ልጅ ኢያሱ ዳግማዊ ምኒልክ ሲሞቱ የካቲት ወር 1908 ዓ.ም. ወ/ሮ ዘውዲቱን ከአዲስ አበባ ቤተ መንግሥት አስወጥተው ፋሌርስታቸው ላይ ከባለቤታቸው ከራስ ጉግሳ ጋር በግዞት እንዲቀመጡ አድርገዋል፡፡

በልጅ ኢያሱ አገዛዝ ያልተደሰቱ የዳግማዊ ምኒልክ ታላላቅ መሳፍንትና መኳንንት አድማ አደረጉ፡፡ አድማውም የልጅ ኢያሱን መናፍቅ ናት፣ ለቱርክ መንግሥት መወገናቸውንና የኢትዮጵያን መንግሥት ወደእስልምና ሊለውጡ ነው የሚል የነገረ ሃይማኖት ነቀፋ ነበር፡፡ አድማው ልጅ ኢያሱን ከሥልጣናቸው አንስቶ፣ በምትካቸው ወ/ሮ ዘውዲቱ ምኒልክን ንግሥተ ነገሥታት፣ ተፈሪ መኮንንን ደግሞ አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ አደረገ፡፡

ዘውዲቱ በአባታቸው ዙፋን ላይ ንግሥተ ነገሥታት ቢሆኑም፣ ራስ ጉግሳ እንዲርቁ ስለተፈለገ የቤጌ ምድር ገዥነት ሹመት ተሰጣቸውና ወደግዛት አገራቸው ሄዱ፡፡ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በባህሪያቸው ጭምት፣ መንፈሳዊ፣ ቅንና ሩሩ በመሆናቸው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በፆምና በፀሎት ነበር፡፡ ገና ከጅምሩ በአልጋ ወራሽ ተፈሪ ላይ ያቄሙት ራስ ጉግሳ ከአልጋ ወራሹ ጋር ያላቸው ቅራኔ ከዕለት ዕለት እየሰፋ መጣ፡፡

‹‹ንግሥት ዘውዲቱን ሥልጣን አልባ አድርገዋቸዋል፣ ተፈሪ መኮንን ካቶሊክ ሆነው ሃይማኖታቸውን ለውጠዋል፣ በአዲስ አበባ ውሻና አህያ ታረደ፣ በሥላሴ ቤተ ክርስቲያንም የውሻ መስዋዕት ተሰዋበት፤›› የሚል ወሬ ሰምተው ልባቸው በአልጋ ወራሹ ላይ ሸፈተ፡፡ ንግሥት ዘውዲቱ፣ ራስ ጉግሳን ከተፈሪ መኮንን ጋር አሸማግለው ጦርነቱን ለማስቀረት በብርቱ ቢደክሙም ስላልተሳካላቸው በተፈሪ መኮንንና በራስ ጉግሳ ወሌ መካከል መጋቢት 22 ቀን 1922 .ም. አንቺም በሚባል ቦታ ከባድ ጦርነት ተደረገ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያው የጦር አውሮፕላን ጦርነቱ ላይ ዋለ፡፡ ራስ ጉግሳ በጦርነቱ ሞቱ፡፡ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱም ራስ ጉግሳ በሞቱ በሁለተኛው ቀን ታመው ሞቱ፡፡

‹‹አንቺም ጦርነት››

ንግሥትን አስጨንቆ፣ የሚወዷቸውን ባለቤታቸውን በሞት ነጥቆ፣ የንግሥትን ሞት አፋጥኖ፣ ንጉሥ ተፈሪን ‹‹ሞሃ አንበሳ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› አሰኝቶ በተፈሪ መኮንን አሸናፊነት ተደመደመ፡፡

‹‹መለኩሴም ይኸን ማድረግ ይችላል ወይ››

የዳግማዊ ምኒልክ ቀኝ እጅ የሆኑት የሐረርጌ ገዥ ራስ መኮንን (የኃይለ ሥላሴ አባት) 14 ዓመት ዕድሜ ያላትን የራስ ወሌን (የእቴጌ ጣይቱ ወንድም) ልጅ ወ/ሮ ምንትዋብን በሠርግ አገቡ፡፡ ራስ መኮንን በዕድሜ ትልቅ ሰው ነበሩ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ራስ መኮንን ከወ/ሮ ምንትዋብ ጋር ተጠርተው አዲስ አበባ ሄዱ፡፡ ወ/ሮ ምንትዋብ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጃንሆይ ግቢ እንደሄዱ ቀሩ፡፡ እቴጌ ጣይቱ ‹‹የሚገባውን ሁሉ አላደረገላትም›› ብለው አፋቱዋቸው፡፡

ራስ መኮንንም በዚሁ ነገር ተቀይመው ከአፄ ምኒልክ ተሰናብተው ወደ ሐረር እንደተመለሱ ለአደን ኦጋዴን ጠረፍ ሄደው አንዲት ሴት አንበሳ ገድለው ደቦሎቿን (ልጆቿንም) ማርከው ወደ ሐረር ተመለሱ፡፡

አንበሳ በመግደላቸው፣ ለአፄ ምኒልክና ለእቴጌ ጣይቱየምስራችብለው መልዕክት ቢልኩ እቴጌ ጣይቱ ‹‹መለኩሴም ይኸን ማድረግ ይችላል ወይ›› ብለው የስድብ ቃል መለሱላቸው፡፡ ራስ መኮንን በእቴጌይቱ የንቀት ንግግር ተበሳጭተው በዚያ ሰሞን በግቢው ውስጥ ከመኳንንቶቻቸው ጋር ፉከራም ቀረርቶ እንደነበር ራስ እምሩከሰማሁትና ካየሁትመጽሐፍ ላይ ገልጸዋል፡፡

አወዛጋቢው ንጉሥና ጋብቻዎቻቸው

ልጅ ኢያሱ አባታቸው ንጉሥ ሚካኤልና እናታቸው ደግሞ የአፄ ምኒልክ ልጅ ወ/ሮ ሸዋረጋ ናቸው፡፡ የአፄ ምኒልክ አልጋ ወራሽ እንደተባሉ ሞግዚታቸውና እንደራሴያቸው በሆኑት በራስ ቢትወድደድ ተሰማ ግቢ ቤት ተሠርቶላቸው ይኖሩ ነበር፡፡ ራስ ቢትወደድ ተሰማ ሚያዝያ 03 ቀን 1903 .ም. በድንገተኛ ሕመም ሲሞቱ ልጅ ኢያሱ የ15 ዓመት ወጣት ቢሆኑም፣ ያለሞግዚት ኢትዮጵያን በግላቸው ያስተዳድሩ ጀመር፡፡

ልጅ ኢያሱ የመጀመርያ ሚስታቸው የአፄ ዮሐንስ የልጅ ልጅ ወ/ሮ ጽጌ ሮማን መንገሻን (በኋላ አስቴር መንገሻ የተባሉትን) ግንቦት 8 ቀን 1901 .ም. በተክሊል አግብተው በሠርግ ተዳሩ፡፡ በዚያን ጊዜ የልጅ ኢያሱ ዕድሜ 12 ዓመት ሲሆን፣ የሙሽራይቱ ደግሞ ስድስት ዓመት ነበር፡፡ ሙሽራዋ በአክስታቸው በወ/ሮ ገሰሰች ቤት በክብር ተቀመጡ፡፡

በኋላም ሞግዚታቸው ራስ ቢትወደድ ተሰማ የሥጋ ዘመዳቸውን ወ/ሮ አስካለ ጋረደውን ድረውላቸው አንድ ወንድ ልጅ ወልደው በሕፃንነቱ ሞቷል፡፡ ቀጥሎም የጎጃሙን የራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት ልጅ ወ/ሮ ሰብለ ወንጌልን፣ የተጉለ ቴውን የደጃዝማች አንዳርጌ ልጅ ወ/ሮ ትሰሜን፣ የጂማ የአባ ጅፋርን ልጅ አግብተዋል፡፡ ከወለጋ የደጃዝማች ጆቴ ቱሉን ልጅ ወ/ሮ አስካለን፣ ከጨኖ የነጋድራስ አቡበከርን ልጅ ሲያገቡ ከሐረር ደግሞ የልጆች እናትና የመሐመድ የሱፍ ሙዲር ሚስት የነበሩትን የአሚር አብዱላሂ (የሐረር አሚራዊ መንግሥት ገዥ የነበሩት) ልጅ ወ/ሮ አመቱላን ከትዳራቸው አፈናቅለው ሚስት አድርገዋቸዋል፡፡ የአዳል መኳንንት ልጅን፣ ከጥሙጋ ደግሞ የእነ ሷሌህን ልጅ፣ ከጂቡቲ ቅኝ ግዛት የሱልጣን አቡበከርን ልጅ አግብተዋል፡፡ ወ/ሮ ዳሼ የተባሉትን የደጃዝማች ገብረ እግዚአብሔርን ልጅ ማግባት ፈልገው ደጃዝማቹ የአፄ ምኒልክ የክርስትና ልጅ ስለሆኑ የመጽሐፍ ሕግ አይፈቅድም ተብሎ ጋብቻው ቀርቷል፡፡ በርካታ ዕቁባቶችም ነበሯቸው፡፡

ዓይንና ጥርስ እየገለጠ የሚያየው ፈረስና በቅሎ የሚገዛ ሰው ነው

በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ከአሥር ዓመታት በላይ በሩሲያና በአውሮፓ ተምረው ወደ አገራቸው የተመለሱት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት፣ ተክለ ማርያም የአፈ ንጉሥ ነሲቡ ሚስት የወ/ሮ ደስታ እህት ልጅን ሊያገቡ አሰቡ፡፡ ቤታቸው ደጋግመው በመሄድ ተለማመዱ፡፡ ከልጅቱ ጋር ለመተዋወቅ ወ/ሮ ደስታን ጠየቁዋቸው፡፡ ‹‹አልፈቀዱም፣ ነገሬን አጠየፉብኝ፡፡ እንደዚህ ያለ ፈሊጥ በአገራችን አልተለመደም፡፡ ፈረስና በቅሎ የሚገዛ ሰው ዓይንና ጥርስ እየገለጠ እያየ ይገዛል፡፡ ሚስት ለሚያጭ ሰው እንደዚህ ማድረግ አይፈቀድለትም ነውር ነው›› አሉ፡፡ ለማግባባት ቢሞክሩምተወው ይቅር፣ የዕድሏን አታጣምእንዳሏቸው ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያትኦቶ ባዮግራፊ (የሕይወቴ ታሪክ)” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ገልጸዋል፡፡

የአፄውና የእቴጌ 51 ዓመታት ትዳር

ወ/ሮ መነን ትዳራቸውን ፈተው ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን (አፄ ኃይለ ሥላሴ)ን እንዲያገቡ የተደረገው በአጎታቸው በልጅ ኢያሱ ትዕዛዝ ነው፡፡ ወ/ሮ መነን በአሥር ዓመታቸው ለደጃዝማች አሊ ተድረው ሁለት ልጆችን ወለዱ፡፡ ከዚያም ለደጃዝማች አመዴ አሊ ተድረው ሁለት ልጆችን ወልደዋል፡፡ በ1903 .ም. ሦስተኛ ባላቸውን ራስ ልዑል ሰገድ አጥናፍ ሰገድን አገቡ፡፡ ልጅ ኢያሱ በዚያኑ ዓመት፣ ወ/ሮ መነንን ከራስ ልዑል ሰገድ አፋ ተውለ ሐረርጌው ገዥ ለደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ዳሯቸው፡፡ ወ/ሮ መነንን በአጀብ ከአዲስ አበባ ወደ ሐረር የወሰዷቸው ራስ እምሩ እንደሚሉት ልጅ ኢያሱ አብረዋቸው ከሚኖሩት ራስ ልዑል ሰገድ በትዕዛዝ አፋተው በዕድሜ ስድስት ዓመት ከሚያንሷቸው ተፈሪ መኮንን ጋር አጋብተዋቸዋል፡፡

ኃይለ ሥላሴ ጭምት፣ ባህላቸውንና ሃይማኖትን አክባሪ ሲሆኑ፣ ከእቴጌ መነን ልዕልት ተናኘ ወርቅን፣ ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰንን፣ ልዕልት ዘነበ ወርቅን፣ ልዕልት ፀሐይን፣ ልዑል መኮንንና ልዑል ሳህለ ሥላሴን ወልደዋል፡፡ በርካታ የልጅ ልጆችንም አፍርተዋል፡፡ በ51 ዓመታት የትዳር ዘመናቸው ክፉና ደጉን ዓይተው እቴጌ መነን የካቲት 7 ቀን 1954 .ም. አርፈዋል፡፡

ራስ ተፈሪ መኮንን ከ1909 እስከ 1922 .ም. ድረስ በአልጋ ወራሽነትና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴነት፣ ከ1923 እስከ 1966 .ም. ድረስአፄ ኃይለ ሥላሴተብለው ንጉሠ ነገሥት ሆነው ኢትዮጵያን አስተዳድረዋል፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ የጀመሩትን ኢትዮጵያን የማዘመን ርዕይ ለማሳካት ደክመዋል፡፡ ዘመናዊ ትምህርት በማስፋፋት፣ ዘመናዊ አስተዳደር በመመሥረት፣ ኢትዮጵያን በመገንባትና አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ ብርቱ ትግል አድርገዋል፡፡ በመላው ዓለም ግርማ ሞገስ ያላቸው ንጉሠ ነገሥት ነበሩ፡፡

ታኅሳስ ግርግር

እየተባለ በሚጠራው በወንድማማቾቹ ብርጋዴየር ጄኔራል መንግሥቱና ገርማ ሜንዋይ በታኅሳስ 1953 .ም. በተሞከረው መፈንቅለ መንገሥት ዙፋናቸው ተነቃንቆ ለጥቂት ተርፈዋል፡፡ ዙፋኑ እንደእንግሊዝ ግርማ ሞገሳዊ ሆኖ እንዲቆይ፣ ኢትዮጵያ በሕዝብ በተመረጡ ዜጎች እንድትመራ ምክር ቢቀርብላቸውም አልተቀበሉም፡፡ የኢትዮጵያ የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት በ1966.ም. በፈነዳው የአብዮት ማዕበል ከሥልጣን ወረዱ፡፡ ቤተሰቦቻቸው፣ መኳንንትና መሳፍንት ተገደሉ፣ ታሰሩ፡፡ መጨረሻቸው አላማረም፡፡ በአገራችን ከፖለቲካ ጋር ጥብቅ ትስስር የነበረው የቤተ ነጋሲ ጋብቻ ከሥርዓቱ መውደቅ ጋር አብሮ መውደቁ ይታወቃል፡፡ መሳፍንቱን፣ መኳንንቱንና ጉልበተኞችን በመብላት የጀመረው የደርግ አብዮት ዕልፍ አዕላፍ ኢትዮጵያውያንን በጦርነትና በቀይ ሽብር በላ፡፡ አገሪቱንም ወደ ከፋ አዘቅት ጥሎ እሱም በተራው አለፈ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...