Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር‹‹ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ››

‹‹ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ››

ቀን:

በውብሸት ተክሌ

ትዝብት

ምንም እንኳን ጊዜው ቆየት ያለ ቢሆንም ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በየዓመቱ በሚከበረው የመከላከያ ቀን በአዳማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የዛሬውን በዓል ልዩ የሚያደርገው ሌተና ጄኔራል ባጫ ደበሌና ሌተና ጄኔራል አበባው ታደሰ መገኘታቸው ነው ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ይህን ይበሉ እንጂ፣ እሳቸው አባል የነበሩበትን የኢሕአዴግ ሠራዊት ስሙን ሳናውቅ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ አገር እንዳትሆንና ኤርትራም እንዳትገነጠል ለማዳን ሲል ደሙን የጨረሰውና አጥንቱን ያረገፈው የቢሹ ገብረ ተክሌና የክፈተው መርኔ ሠራዊት፣ የ56ቱን የሶማሌ ወረራ የገታው የአማን ሚካኤል አንዶም 3ኛ ክፍለ ጦርና በ69ኙ ጦርነት የሶማሌን ሰማይ ለወረሩት ለእነ ፋንታ በላይ፣ አምሐ ደስታ፣ ለገሰ ተፈራና በዛብህ ጴጥሮስን ለመሳሰሉ ጀግኖች ዕውቅና ያልሰጠ ንግግር ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በትናንቱ የባድመ ጦርነት በተደረገላቸው የድረሱልኝ ጥሪ የተሳተፉት ሚሊቴሪ ስትራቴጂስቶቹ ጄኔራል በኃይሉ ክንዴና ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተ ማርያም በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ጥሪ አልተደረገላቸውም፡፡ ጄኔራሎቹ በንጉሡ ዘመን የሐረር ጦር አካዴሚ ምሩቃን መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ቅደም ተከተላቸው በእስራኤልና በአሜሪካ በከፍተኛ ወታደራዊ ሳይንስ የሠለጠኑ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ አባዱላን ጨምሮ ባጫ ደበሌና ሌሎች ሦስት ጄኔራሎች የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት የነበሩ ሲሆን፣ በምርኮ ኢሕአዴግን የተቀላቀሉ ናቸው፡፡ ይህ እውነት በሠራዊቱም የሚታወቅ ሲሆን፣ እነሱም ያስተባብሉታል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ታዲያ ለጠላት እጃችንን አንሰጥም ብለው የራሳቸውን ጥይት የተጎነጩትና ባህር ውስጥ የሰመጡት የቴዎድሮስን የአደራ ልጆች ማን ያወድሳቸው? ብሎ መጠየቅ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል ከሚል ዜጋ የሚጠበቅ ነው፡፡ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ሠራዊት የመግፋት ወይም የማግለል ልክፍት የተዛመተው ለሻዕቢያ ወግነው ወደብ ያሳጡን ኃይሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ማፈርና መሸማቀቅ ሲገባቸው የአካዴሚክና የወታደራዊ ሳይንስ ልሂቃን (Intellect) የሆኑትን ጄኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች፣ የደርግ ወታደር እያሉ ማሽሟጠጥ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ይህን ይበሉ እንጂ ሦስት ብርጌድ ጦራቸውን ሳህል አውራጃ ከነበረው የሻዕቢያ ጦር ጋር በመቀላቀል የኢትዮጵያን ሠራዊት ከመውጋት የበለጠ አሳፋሪ ነገር የለም፡፡ እነዚህ በአንድ አካባቢ የበቀሉ አረሞች ለአንድነቱ ሲዋደቅ የኖረውን የቀድሞ ሠራዊት የማንቋሸሽም ሆነ የማኮሰስ ሞራል የላቸውም፡፡ እውነቱን ለመነጋገር ካሰብን በራሱ በሠራዊቱ መሪዎች ስህተትና ከዋናው የማዘዣ ማዕከል ሾልኮ በሚወጣ ወታደራዊ ሚስጥር በመታገዝ ወደ ሥልጣን የመጣው የባንዳ ስብስብ፣ የጦርነት መሐንዲሱ እኔ ነኝ ይበለን እንጂ ቀጥሎ የዘረዘርናቸውን ጀግኖች የሚተኩ አባላት የሉትም፡፡

የአየር ኃይሎቹ አብራሪዎች፡- ጄኔራል ሰለሞን በጋሻው፣ ጄኔራል ተስፉ ደስታ፣ ጄኔራል ንጉሤ አርጋው፣ ጄኔራል ገናናው መንግሥቱና ሻምበል ተሾመ ተንኮሉ፣ ወዘተ.፡፡

የአየር ወለዶቹ በራሪ ነብሮች፡- ድንበሩ በኩረን፣ ሕብስቱ አያሌው፣ ሙሉነህ ኃይሌ፣ ታደሰች ብርሃን፣ ታዬ ቶሳ፣ ወልዱ ባይከዳኝ፣ ገብረ ሕይወት ተፈሪንና ሰረቀ ብርሃን፣ ወዘተ.፡፡

የሠራዊቱ አዛዦች፡- ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ፣ ጄኔራል መስፍን ገብረ ቃል (ዶ/ር)፣ ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ፣ ጄኔራል አበሩ አበበ፣ ጄኔራል ቁምላቸው ደጀኔ፣ ጄኔራል አፈወርቅ ወልደ ሚካኤል፣ ጄኔራል ተስፋዬ ትርፌ ከእንግሊዝ ሳንድረስት ከንግሥቲቱ ሜዳሊያ በመሸለም የተመረቀ፣ ወዘተ.፡፡

በሲቪል አስተዳደር በኩል

የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የኤልኤልኤም (LLM) ምሩቁ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ፣ የኤርትራ ክፍለ አገር ዋና አስተዳዳሪ፡፡

የየል ዩኒቨርሲቲ የኤልኤልኤም (LLM) ምሩቁ ጎሹ ወልዴ፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የትምህርትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል፡፡ አምባሳደር፣ ኮሚሽነርና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወዘተ. የነበሩትም ሁለተኛ ዲግሪ (ማስትሬት) የነበራቸው ሲሆኑ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ሜዲካልና ሰርጂካል ዶክተሮችም ነበሩበት፡፡ በተለይ አሜሪካኖቹ ድምፅ አልባው አብራሪ ብለው በሚጠሯቸው ጄኔራል አምሐ ደስታ ይታዘዝ የነበረው የኢትየጵያ አየር ኃይል ዕውቀትና ተሞክሮ በሌላቸው በረኸኞች (በእነ አበበ ተክለ ሃይማኖት) እንዲበተን መደረጉን የምናስታውሰው በቁጭት ሲሆን፣ በዚሁ ሳቢያ ነበር አብራሪዎች ለእስርና ለስደት መዳረጋቸው የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በታሪክ ፊት የሚቆሙበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እርግጠኞች ነን፡፡ ‹‹አጣን እጎዳለሁ ብለው ወንዝ ውስጥ ወረወሩት›› እንዲሉ፣ ፓይለቶቹ በልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው ይሠራሉ፡፡

በግልጽ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ደርግ ከእነ ሠራዊቱ የወደቀው በውጊያ ብቃት ማነስ ሳይሆን ቀጥሎ በተዘረዘሩት አምስት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደነበረ ጥናቶች አመላክተዋል፡፡

 1. የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ያደረጉ ምርጥ ጄኔራሎች ያለ ፍርድ መገደል ለገንጣይና አስገንጣዮቹ ፈንጠዝያ ሲፈጥር ለወገን ጦር የሥነ ልቦና ስብራት ምክንያት ሆነ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከሠራዊቱ ጋር አብረው የኖሩት ጄኔራል ታሪኩ ላይኔና ኮሎኔል ውብሸት ማሞ በጦሩ ፊት በግፍ መገደልና የጄኔራል ከበደ ጋሼ ማዕረግ መገፈፍ ያስከተለው ቁጣ የጦሩን የውጊያ ፍላጎት ቀነሰ፡፡
 2. የሠራዊቱ አዛዦ የሚያወጡ የውጊያ ሥልት (Strategy) ወደ ተግባር ከመለወጡ በፊት፣ በጦሩ ውስጥ የነበሩ ባንዳዎች (የውስጥ አርበኞች) ለሕወሓት አሳልፈው በመስጠት ጦሩን ማስጨፍጨፍ ቻሉ፡፡
 3. የሕወሓት ሦስት ብርጌድ ጦር በሳህል አውራጃ ይንቀሳቀስ ከነበረው የሻዕቢያ ጦር ጎን በመሠለፍ የኢትዮጵያን ጦር በመውጋቱና ከመሀል አገር የሚላክ ስንቅና ትጥቅ እንዳይደርስ መንገድ በመዘጋቱ፣ በጦርነቱ ከደረሰበት ጉዳት ይልቅ ለረሃብና ለውኃ ጥም ተጋልጦ አለቀ፡፡
 4. ሕዝቡ በቀይ ሽብርና በብሔራዊ ውትድርና ልጆቹን እንዲያጣ በመደረጉ ከደርግ የማይሻል የለም በሚል የመረረ ጥላቻ የሕወሓትንና የሻዕቢያን ሠራዊት መንገድ እየመራ አራት ኪሎ እንዲገባ መፍቀዱ እንጂ፣ የዘመናት ብሶት የወለደው የተባለለት የኢሕአዴግ ሠራዊት አዲስ አበባን መቆጣጠር የቻለው በወታደራዊ የበላይነት አልነበረም፡፡
 5. የሠራዊቱ አዛዦች በኢሠፓ አስገንጣዮቹ ዕድል ሰጥቷል፡፡

እንደ አገር የሚታሰብ ከሆነ በ56ቱ እና በ69ኙ የሶማሌ ወረራ የላቀ ጀግንነት የፈጸሙ የአየርና የምድር ተዋጊዎችን ጨምሮ፣ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል በተደረገው ረዥም ጦርነት ከመማረክ ሞትን መርጠው የራሳቸውን ጥይት የተጎነጩት የቁርጥ ቀን ልጆች አስከሬናቸው በየጫካው ቀርቷል፡፡ ቤተሰባቸው ተበትኗል፡፡ ልጆቻቸው ትምህርት አቋርጠዋል፡፡ ይህን ሁሉ የሚያውቁ መሪዎቻችን እንዳላየና እንዳልሰማ ዝም ብለዋል፡፡ ከእነዚህ ይልቅ አንድ አርቲስት ሲሞት መንገድ ይሰየምለታል፡፡ ሐውልት ይቆምለታል፡፡ ለቤተሰቦቹና ለልጆቹ ሚሊዮን ብሮች ይፈሱለታል፡፡ አሁንም ወደ ቀድሞው ሠራዊት ልመለስና አገርና መንግሥት የሌሏቸው ይመስል በሻዕቢያ እስር ቤቶች ተጥለው የቀሩና እስካሁንም መጨረሻቸው ያልታወቀ ሦስት መኮንኖችና ጋዜጠኞችን መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡

 1. ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ፡- የኤርትራ አየር ኃይል አዛዥና የበዛብህ ጴጥሮስ የቀድሞ ጓደኛ የነበረው ሻለቃ ሀብተ ጽዮን የአይደር ትምህርት ቤት ሕፃናትን ከመጨፍጨፍ በኋላ አፀፋውን ለመመለስ አስመራ ገብቶ፣ የአየር ኃይሉን ሠፈር (Base) ከፊሉን አፈራርሶ በሰላም ተመልሶ የነበረ ቢሆንም በማግሥቱ ግዳጁን ሲወጣ በሚሳይል ተመቶ የወደቀ ፓይለት ነው፡፡ በወቅቱ ሻለቃ ሀብተ ጽዮን አግኝቶት ለምን እንደዚህ ታደርጋለህ? ብሎ በጠየቀው ጥያቄ አንተስ በአይደር ትምህርት ቤት ሕፃናት ላይ የፈጸምከው ጭፍጨፋ አይሰማህም ወይ? ብሎ መልሶለታል፡፡ በዛብህ ጴጥሮስ ቀደም ሲል በተመሳሳይ ሁኔታ በሻዕቢያ እጅ ወድቆ ሰባት ዓመታት ከታሰረ በኋላ በምሕረት የተለቀቀ ሲሆን፣ የ69ኙን የሶማሌ ወረራ ለመቀልበስ በጄኔራል ፋንታ በላይ የተመራውን የእነ ለገሰ ተፈራ፣ አምሐ ደስታና ኮሎኔል ባጫን ቡድን በመቀላቀል የሶማሌ ሚግ አውሮፕላኖች እርስ በርሳቸው እየተላተሙ እንዲጋዩ በማድረጉ የሚታወቅ፣ ከዚያም አልፎ ለበረራ የተወለደ የተባለለት ጀግና ነው፡፡ ዛሬ በሕይወት ይኖራል ተብሎ ባይገመትም የራሱ ቤትና መኪና እንኳን ያልነበረው፣ በከፈለው መስዋዕትነት በመንግሥት በቂ ዕውቅና ያላገኘ መሆኑ ደግሞ ለወዳጆቹ፣ ለቤተሰቡና ለሥራ ባልደረቦቹ ፀፀትና ቁጭት አስከትሏል፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአሜሪካ ባደረጉት ጉብኝት ስለዚህ ሰው በዳያስፖራው መጠየቃቸውን የሰማን ቢሆንም፣ እሳቸውንና ኢትዮጵያን እዚህ ስላደረሱ ዜጎች በተለይም ስለቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ክብርና ስለከፈለው መስዋዕትነት ሲናገሩ አልሰማንም፡፡ አሁንም ቢሆን ‹‹የፊተኞቹ የኋለኞች›› ይሆናሉ ካልተባለ በስተቀር በሠራዊቱ ውስጥ ስለተፈጠረው የታሪክ መዛባት ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
 2. ካፒቴን አብርሃም ስንቄ፡- ልክ እንደ በዛበህ ጴጥሮስ ኤርትራ ውስጥ ተመቶ ከወደቀ በኋለ በሻዕቢያ እጅ ገብቶ መከራና ሥቃይ ሲቀበል የቆየ ሰው ነው፡፡ ካፒቴን አብርሃም በእስር ላይ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን በሕይወት ስለመኖሩ መረጃ የለም፡፡ በተዋጊ ጄት አብራሪነቱ የአየር ኃይሉ ኩራት እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት የሥራ ባልደረቦቹ በሐዘን ስሜት ይገልጹታል፡፡
 3. ጄኔራል ገብረ መድኅን፡- (የአባታቸውን ስም የዘነጋሁት) ትውልደ ኤርትራዊ ይሁኑ እንጂ፣ በኢትዮጵያ ሠራዊት ውስጥ ካልተዘመረላቸው ጀግና ጄኔራሎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ኢትዮጵያን ለማፈራረስና ኢትዮጵያዊነትን ለማቆሸሽ ሲለፋ የቆየው ሕወሓት ወደ ሥልጣን እንደ መጣ ጄኔራሉን ለሻዕቢያ አሳልፎ ከሰጣቸው በኋላ በእስር ላይ እንደነበሩ ብናውቅም፣ በሕይወት መኖር አለመኖራቸውን የማወቅ ዕድል አልገጠመንም፡፡
 4. ጋዜጠኛ ሳራ መኮንን፡- ትውልደ ኤርትራዊ ስትሆን ኤትራ ውስጥ የተዋጣላት ጋዜጠኛ ነበረች፡፡ በኢትዮጵያዊነቷ በነበራት ጠንካራ አቋም ትታወቃለች፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣች በኋላ በሙያዋ በማገልገል ላይ እንዳለች የጄኔራል ገብረ መድኅን ዕጣ ፋንታ የገጠማት ሴት ነች፡፡ እሷም ሻዕቢያ ደብዛቸውን ካጠፋቸው ውስጥ ትጠቀሳለች፡፡ ከአንድ እስከ አራት ከተገለጹት በተጨማሪ በሻዕቢያ እስር ቤት የታጎሩ የሲቪልና ወታደራዊ የፖለቲካ ሠራተኞች የነበሩ ኢትዮጵያውያን የዜና ሽፋን እንኳን እንዳያገኙ ትልቁን ድርሻ የተወጣው በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው መለስ ዜናዊ ቢሆንም፣ በስሙ የገዘፈው በተግባሩ የኮሰሰው የዓለም ቀይ መስቀል ማኅበርም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በሆነ መንገድ ሰዎቹ የት እንዳሉና በሕይወት ከሌሉም የማሳወቅ ግዴታ ነበረበት፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ተቋም ረዥም ዕድሜ ቢኖረውም ዱቄትና ዘይት ከማደል በስተቀር በጦር ምርኮኝነትና በግፍ አገዛዝ ሥር የወደቁ ዜጎች አያያዝና መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው መሟላታቸውን እየተከታተለ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒትር ዓብይ (ዶ/ር) ጉብኝት ባደረጉባቸው አገሮች እስረኛ በማስፈታት ያሳዩትን ዲፕሎማሲያዊ ብቃት በኤርትራም ይደግሙታል ብለን ብንጠብቅም፣ የእሳቸው ዝምታ የሰዎቹን በሕይወት መኖር የማይታሰብ አድርጎታል፡፡

ቀደም ሲል ስለቀደመው የኢትዮጵያ ሠራዊት መበተን መሠረታዊ ምክንያቶችን ዘርዝሬያለሁ፡፡ ሆኖም አሸንፈን መጥተናል የሚሉን ከሆነ ያስገኙት ውጤት አገር ማስገንጠልና ወደብ ማሳጣት መሆኑን እየጎመዘዛቸውም ቢሆን ሊቀበሉት ይገባል፡፡ እነሱ ታገልን የሚሉት ፎቅ ሊደረድሩ፣ ቪ8 ሊያሽከረክሩና ልጆቻቸውን አውሮፓና አሜሪካ እየላኩ ለማስተማር እንጂ አንድም ጊዜ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻልና አገርን የማልማት አጀንዳ ኖሯቸው አያውቅም፡፡ ለዚህም ማሳያ በልማት ባንክ፣ በስኳር ኮርፖሬሽንና በሜቴክ የፈጸሙት መጠነ ሰፊ ዘረፋ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ለአገር ሉዓላዊነትና ለሕዝቦች አንድነት ተራራ ሲወጡና ቁልቁለት ሲወርዱ ጊዜያቸው ያለፈ ጄኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች፣ መኪናና ቤት ቀርቶ የጡረታ መብታቸው እንኳን አልተከበረላቸውም፡፡ ለዚህ የከፋ ኑሮ ተጋልጠው አውቶብስና ታክሲ ለመሳፈር ተራ ሲጠብቁ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ እርግጥ ነው የበላይ ዘለቀን ስቅለት የምናስታውስ ወገኖች ግፍና በደሉን ለምደነው ይሆናል፡፡ እሱ በተሰቀለባት ኢትዮጵያ ስንቱ ባንዳ ምድር ገነት ሆናው ይኖር እንደነበር የሩቅ ጊዜ ታሪክ አይደለም፡፡ በሌሎች አገሮች ለምሳሌ ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ ጃፓንና ሩሲያ፣ በአፍሪካም ጭምር አገራቸውን ነፃ ለማውጣትና ከወረራ ለመከላከል ሲታገሉ ሕይወታቸው ላለፈ ወታደሮች ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ ልጆቻቸው የእነሱን አርዓያ ተከትለው እንዲያድጉ የነፃ ትምህርት ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ በሕይወት የተረፉም በታላላቅ ወታደራዊ ሥነ ሥርዓቶች እየተገኙ ንግግር ያደርጋሉ፡፡ የአገር መሪዎችም ጉብኝት ባደረጉ ቁጥር የአበባ ጉንጉን ያስቀምጡላቸዋል፡፡

በእኛ አገር እነ መለስ ዜናዊ በወሰዱት የበቀል ዕርምጃ ጀግና ወታደሮች እንደ አሮጌ ዕቃ ተጥለዋል፡፡ ዓመታት ያስቆጠረ የጥላቻ ዘመቻ ሰለባ ሆነዋል፡፡ እነሱ በሻዕቢያ ጉያ ተወሽቀው አገር ማድማታቸው ሳይታወቃቸው፣ የቀድሞ ሠራዊት ስለአንድነትና ሉዓላዊነት የከፈለውን መስዋዕነት ያንቋሽሻሉ፡፡ የአገሬ ሰው ዳኝነት በተጓደለበት ቁጥር ‹‹ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሠራልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ›› እያለ ብሶቱን ሲያስተላልፍ ኖሯል፡፡ ዛሬም እያየን ያለነው ይህንኑ ነው፡፡ የእኛዎቹም ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት፣ ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በሚያገኙት መድረክና በሚፈጠረው አጋጣሚ ስለቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት መነሻና መድረሻ በውስጡም ስላለፉ ወታደራዊ ጠበብቶችና ስለብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮቻቸው ተነጋግረው አያውቁም፡፡ በግሌ የማዝነው አንድም ዩኒቨርሲቲ በሠራዊቱ ውስጥ ለሚታወቁ ወታደራዊ ምሁራን፣ ለአስገራሚዎቹ ተዋጊ ፓይለቶችና ወደር ላልተገኘላቸው አዋጊና ተዋጊ ጀግኖች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥተው ባለማወቃቸው ነው፡፡ ያም ሆኖ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ብዙ ስንጠብቅ ከወጣትነት እስከ አዛውንትነት ለአገር የተዋደቁ ጄኔራሎችን ረስተው ባጫ ደበሌን በቀድሞ ስሙ አትንኩኝን ያወደሱበት አግባብ፣ ሐዘናችንና አበረታው እንጂ ጉልበት አልሆነልንም፡፡ ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ  ጄኔራል ተስፋዬ ትርፌ፣ ጄኔራል አምሐ ደስታ፣ ኮሎኔል ሰረቀ ብርሃን፣ ኮሎኔል ካሳ ገብረ ማርያም፣ ጄኔራል ተሾመ ተሰማ፣ ጄኔራል በኃይሉ ክንዴና ሚኒስትር ፋንታ በላይን ያውቋቸዋል? እነሱም እኮ ያገለገሉት ኢትዮጵያን ነበር፡፡

ሁለተኛው ትዝብቴ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 346 ሚሊዮን ብር ወጭ ያደረገበትን የማስፋፊያ ተርሚናል በስካይ ላይት ሆቴል በመረቁበት ዕለት ያደረጉትን ንግግር በሚመለከት ነው፡፡ በዚሁ ንግግራቸው አየር መንገዱ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ያበቁት አቶ ግርማ ዋቄና አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ናቸው ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡ ሁለቱም ግለሰቦች ለአየር መንገድ ዕድገት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሠርተዋል፡፡ በተለይ አቶ ግርማ ዋቄ አየር መንገዱ በተመራጭነቱ እንዲቀጥል አሻራቸውን አኑረዋል፡፡ የሠራተኛውንም ደመወዝ በማሻሻልና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንዲከበሩለት በሠሩት ሥራ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቸራቸው ምሥጋና የሚያንሳቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይሆንም፡፡ ነገር ግን ለአየር መንገዱ ዕድገት በከፈሉት ዋጋ የምናስታውሳቸው የቀድሞ አመራሮች ይሸለማሉ ብለን ስንጠብቅ ስማቸው እንኳን ባለመነሳቱ በጣም አዝነናል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ባለታሪኮች እነማን ናቸው?

 1. የሥራና የመገናኛ ሚኒስትር የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፡- አየር መንገዱን ከአሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ አሁን ወደሚገኝበት ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ከማዛወር ጀምሮ፣ ቦይንግ አውሮፕላንን ለመጀመርያ ጊዜ ያስመጡ ሰው ናቸው፡፡ አውሮፕላኑን ገዝቶ ለማስመጣት ያቀረቡት የ45 ሚሊዮን ዶላር የብድር ጥያቄ በወቅቱ የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት ይልማ ደሬሳን ጨምሮ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ሳይቀበለው ቀረ፡፡ መንገሻ ሥዩም ሥራ ወዳድና የማሳመን ብቃት ስለነበራቸው ንጉሡ ፊት ቀርበው ካስፈቀዱ በኋላ፣ የነበራቸውን የረዥም ጊዜ ህልም ዕውን ለማድረግ የልዑካን ቡድናቸውን በመምራት አሜሪካ ሄደው ከውጭ ጉዳይ (State Department) ባለሥልጣናትና ከቦይንግ ኩባንያ አመራሮች ጋር በመደራደር የብድር ስምምነቱን በፊርማቸው አፀደቁ፡፡ የሰው ኃይል ሥልጠናን በሚመለከት በሁለተኛው ዙር ድርድር ስምምነት ላይ ስለደረሱ ስድስት ቴክኒሽያኖችን ጨምሮ ካፒቴን ዓለማየሁ አበበና ካፒቴን አዳሙ (የአባታቸውን ስም የዘነጋሁት) ሠልጥነው እንዲመለሱ በማድረግ ቦይንግ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ማንዣበብ ጀመረ፡፡
 2. ኮሎኔል ሥምረት መድኃኔ፡- የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የአየር መንገድ ዋና ሥራ አስኪያጅና በኋላም የሥራ ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል፡፡ የአየር መንገዱን መዳረሻ መስመሮች አስፋፍተዋል፡፡ ዘመናዊ የቴክኒክ ተቋም እንዲኖረው አሻራቸውን አኑረዋል፡፡ አፍሪካን በንግድና ቱሪዝም ለማስተሳሰርና የአቪየሽንን ዕድገት ለማፋጠን ያደረጉትን አስተዋጽኦ በማጉላት፣ በመላው ዓለም የሚሠራጩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ጽፈውላቸዋል፡፡ ስምረት መድኃኔ ወደ አየር መንገድ ከመምጣታቸው በፊት በኢትዮጵያ አየር ኃይል የኮሎኔልነት ማዕረግ የነበራቸው ታዋቂ ፓይለት ነበሩ፡፡
 3. ካፒቴን መሐመድ አህመድ፡- እንደ ኮሎኔል ስምረት መድኃኔ ሁሉ እሳቸውም በሥራ አስኪያጅነት ዘመናቸው አየር መንገዱ በሁለት እግሩ እንዲቆም ሙሉ ጊዜያቸውን ሰውተዋል፡፡ የማኔጅመንቱን ቡድን (Management Crew) በተዋጣላቸው ባለሙያዎች እንዲሞላ ከማድረግ ጀምሮ፣ የበረራ ደኅንነቱ ዘመናዊ ሥልጠና በወሰዱ አባላት እንዲጠናከር በማድረጋቸው በተደጋጋሚ ተሞክረው የነበሩ ጠለፋዎች እንዲመክኑ አስችለዋል፡፡ ካፒቴን መሐመድ ሥራቸውን ለቀው ከወጡ በኋላ አየር መንገዱ ገጥሞት የነበረውን ሁለንተናዊ ቀውስ እንዲያስተካክሉ በደርግ መንገሥት የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው በመምጣት፣ ወደነበረበት ከፍታ መመለስ የቻሉ በመሆናቸው ዛሬም ዘወትርም ልናስታውሳቸው ይገባል፡፡ አየር መንገዱ ተወልዶ እስካደገ ድረስ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ የቅርብ ክትትል ያደርጉበት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የመገደላቸው ገዳይ አነጋጋሪ ሆኖ የቀጠለው የሕግ ምሁሩ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ከእነ ዶ/ር ሎሬንሶ ታዕዛዝ ቀጥሎ ቀደምት (Senior) ዲፕሎማት እንደነበሩ፣ በተለይ በኤርትራ ጉዳይ በከፈሉት መስዋዕትነት በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ኅብረት ይታወሳሉ፡፡ በነበራቸው ከፍተኛ ዕውቀትና ተደማጭነት ሐውልት ባይቆምላቸውም መንገድ ባይሰየምላቸውም በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ዘለዓለም ሲታሰቡ ይኖራሉ፡፡

ትዝብት 3

ፕሬዚዳንቷን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት በታላቁ ቤተ መንግሥት በተደረገው የአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአሸኛኘት ሥነ ሥርዓት ላይ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ያደረጉትን ንግግር ሳደምጥ በጣም አፍሬአለሁ፡፡ በተለይ ሥጦታው (የወርቅ ሰንሰለቱ) የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት መሆኑንና የአፍሪካ መሪዎች ከአቶ ኃይለ ማርያም መማር ነበራቸው ሲሉ የገለጹበት መንገድ፣ የሚመሩትን ሕዝብ ሥነ ልቦና የማይመጥን ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡ በመሠረቱ ሕዝብና መንግሥት ሁለት ገዥና ተገዥ ወገኖች የሚፈጥሩት አስገዳጅ ግንኙነት እንጂ፣ የጋራ ፍላጎት ኖሯቸው አያውቅም፡፡ መንግሥት ፍርድ ቤቶችንና ፖሊስ በማቋቋም ከሳሽም ዳኛም ሆኖ ይመራል እንጂ፣ ሕዝብ መብቱና ነፃነቱ ተከብሮለት የኖረበት ጊዜ የለም፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ በአቶ ኃይለ ማርያም ፍቅር ወድቆ ስጦታ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ማለቱን አልሰማንም፡፡ በስሙ ከመጠቀም በስተቀር አንድም የሕዝብ ተወካይ በግብዣው ላይ አልተገኘም፡፡ ዜናውን ግን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀጥታ ሥርጭት ተከታትሏል፡፡ ጊዜ ሳይወስድ ሐዘኑንና መከፋቱን ገልጿል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የታላቁንና የባለራዕዩን መሪ “ሌጋሲ” አስቀጥላለሁ ብለው አዋጅ ካወጁበት ጊዜ አንስቶ፣ ከኢሕአዴግ ካድሬዎች በስተቀር ሕዝቡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር አይመለከታቸውም ነበር፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር አቶ ኃይለ ማርያም የሚያስተምሯቸው የአፍሪካ መሪዎች የትኞቹ መሆናቸውን አለማወቃችን ነው፡፡ መቸም የጋናውና ዴሞክራት፣ የሩዋንዳውን የለውጥ ሃዋሪያና የቦትስዋናውን የሰላም አምባሳደር ማስታወሳቸው ከሆነ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአፍ ወለምታ ሆኖባቸዋል ወይም ደግሞ መሪዎቹን መሳደብ ፈልገዋል ማለት ነው፡፡

እስቲ አቶ ኃይለ ማርያም ስድስት ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ ኢትዮጵያን ወዴት ወስደዋት እንደነበር እንመልከት፡፡

 1. ከለጋሽ አገሮች በብድርና በዕርዳታ የተገኘ ገንዘብ በዕቅድ በማይመራ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት ልማት ባንኩ አደጋ ላይ መውደቁን፣ ሁለቱ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት (አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ) ምክር ቢለግሷቸውም ዕርምጃ በመውሰድ ከመከላከል ይልቅ፣ ልማታዊ መንግሥታቸውን ለማዳከም የታሰበ እየመሰላቸው አሁን ለተሸከምነው 86 ቢሊዮን ዶላር ዕዳና 16.4 ቢሊዮን ዶላር የተበላሸ ብድር ኃላፊነቱን ከሚወስዱ ሹመኞቻቸው ውስጥ በመጀመርያው ተርታ ይሠለፋሉ፡፡
 2. ጫማ ጠራጊዎች አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ አሻራቸውን ያኖሩበት የዓባይ ግድብ (ህዳሴ የሚለውን አልጠቀምም) በሜቴክ ኮማንደሮች ሲመዘበርና 77 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎባቸዋል የሚባሉት የስኳር ፕሮጀክቶች ሥራቸው ቆሞ እያለ፣ እሳቸው ግን ሁለቱም ፕሮጀክቶች በተያዙላቸው ዕቅድ መሠረት እየተሠሩ መሆናቸውን ለፓርላማው ሪፖርት ማቅረባቸው እንዳለ ሆኖ፣ በተለይ ሜቴክ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ማሳካቱ የዕድገታችን አንዱ ማሳያ ነው ሲሉን ነበር፡፡ ለገንዘቡ ብክነት ፕሮጀክቶቹ ብቻ አልነበሩም፡፡ የጋምቤላ የእርሻ መሬትን እናለማለን ከሚሉት ውስጥ አብዛኞቹ ሌቦች ያለ ምንም የዕዳ ማስያዣ (Collateral) በቀበሌ መታወቂያ የተሰጣቸው ብድር ለግል መበልፀጊያ መዋሉን ለአቶ ኃይለ ማርያም ተከታታይ ሪፖርት ይደርሳቸው ነበር፡፡ አስገራሚው ነገር ባንኩ ሲመዘበር የቦርድ ሰብሳቢው ቁልፍ ከሚባሉት ሚኒስትሮች አንዱ የነበረ ሲሆን፣ በአንድ ትልቅ አገር አምባሳደር ሆኖም ሠርቷል፡፡ አሁን ደግሞ ጡረታ ከተባለ በኋላ የኢነርጂውንና የፋይናንስ ዘርፉን የሚቆጣጠር ተቋም የቦርድ ሰብሳቢ ሆኖ ይመራል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት የነበረው ግለሰብም በቦሌ በኩል ሲሸኝ አቶ ኃይለ ማርያም አያውቁም ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በዚያው ሰሞን ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ሲታገል የነበረውን አንዳርጋቸው ጽጌን ቻርተር አውሮፕላን አዘው ከየመን ለማስያዝ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡
 3. ማዕከላዊ በመባል የሚታወቀውን የሰው ልጆች መሰቃያ ቦታና በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የነበረውን ሁኔታ ለመመልከት የመጡትን የዓለም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዛይድራኢድ አል ሁሴን ወደ አካባቢው እንዳይሄዱ ከልክለዋቸዋል፡፡ ሒውማን ራይትስ ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የነበረውን ግድያ መፈናቀልና የንብረት ውድመት በማስመልከት የሚያወጡት መግለጫ ተራ አሉባልታ በማስመሰል፣ ለአገር ውስጥና ለውጥ የሚዲያ ተቋማት ማስተባበያ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ የኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ በነበሩ ጊዜም የፀጥታ ኃይሉ ዕርምጃ እንዲወስድ ባስተላለፉት ትዕዛዝ የብዙ ወጣቶች ሕይወት አልፏል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም በተከተሉት ብልሹ አሠራር የማይፀፀቱና ይቅርታም የመጠየቅ ፍላጎት እንደሌላቸው ጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ከግጭት ቀጣና (Conflict Zone) ጋዜጠኛ ቲም ሴባስቲያን (Tim Sebastian) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተረድተናል፡፡
 4. በፌዴራል መሥሪያ ቤቶችና ዜጋን ይፈጥራሉ ተብለው በሚገመቱ የዩኒቨርሲቲ አመራሮት በተፈጸመ መጠነ ሰፊ ሙስና ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ መባከኑን፣ ዋናው ኦዲተር ገመቹ ዱቢሳ ባለመሰልቸትና ተስፋ ባለመቁረጥ ለፓርላማው ያቀረቡት የኦዲት ሪፖርት ለአቶ ኃይለ ማርያም እንዲርሳቸው ቢደረግም የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለሙያ መኖርንና በራስ መተማመንን ላስተማሩን ገመቹ ዱቢሳ ረዥም ዕድሜና ሙሉ ጤንነትን እንመኛለን፡፡ እኚህ ሰው አይነኬ እየተባሉ ይጠሩ የነበሩትን ሁለት የመንግሥት ተቋማት ለመጀመርያ ጊዜ ኦዲት ለማድረግ የደፈሩ ጀግናችን ናቸው፡፡

በመጨረሻም አቶ ኃይለ ማርያም የማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በንጉሡና በደርግ ዘመን የዜጎች ማሰቃያ ስለነበር ወደ ሙዚየምነት ቀይረነዋል ካሉን ታዲያ፣ በእሳቸው ዘመን ማዕከላዊ ምን ሲሠራበት ነበር? ለመሆኑ ዜጎች ከአውሬ ጋር ሲታሰሩ፣ የዘር ፍሬያቸው ሲኮላሽ፣ ግብረሰዶም ሲፈጸምባቸውና ጥፍራቸው ሲነቀል አያውቁም ነበር እንዴ? አብዲ ኢሌ ሚሊዮን ሕዝብ ሲያፈናቅልና 200 ሰዎች በጉድጓድ ሲቀብር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ምን ዕርምጃ ወሰዱ? በአንድ ወቅት ወርቅ በሰፌድ እያበጠሩ መበልፀግ ይቻላል ያሉን አቶ ኃይለ ማርያም በመሪነታቸው ስላሳዩን ስንፈት ሕዝቡን በአደባባይ ይቅርታ ካልጠየቁ፣ በእጃቸው ያለውን ዕድል አሳልፈው እንደ ሰጡ መቆጠር አለባቸው፡፡ ነገ ሌላ ቀን ነውና፡፡

አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር

አክሊሉ ሀብተ ወልድን የሰጠኸን አንተ ነበርክና

ዛሬም ምትካቸውን መድብልን፡፡ አሜን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ አየር ወለድ ባልደረባ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...