Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ኮርኳሪ አይጥፋ!

ጉዞ ሊጀመር እየተሰናዳን፣ ‹‹የነዳጁን ዋጋ እኛ የምናንረው ይመስል ሰው በሙሉ እኛን ሊበላን ደርሷል…›› በማለት ቅሬታውን ለታክሲ ተሳፋሪዎች ያሰማው ወያላው ነው፡፡ ወያላው በሰው ሁኔታ የተማረረ ይመስላል፡፡ ሰው ደግሞ አሁን ያልተማረረበት ምንም ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ የታክሲ ታሪፍ ሳይጨምር የነዳጅ ዋጋ ጨመረ ሲባል፣ ከነዳጅ ጋር ግንኙነት ያላቸውም የሌላቸውም ዕቃዎች ዋጋ ከመጠን በላይ ስለሚጨምር ነው በሚለው ሐሳብ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ወያላው ብሶቱን መተንፈሱን ቀጥሏል፣ ‹‹እኔንማ ገና ሲያዩኝ ድሮ ስደባደብ የተፈነካከተውን፣ በጫትና በሲጋራ የጠቋቆረውን ፊቴንና የተነቃቀሉ ጥርሶቼን ሲያዩ ይደነግጣሉ፡፡ ፊቴ በየቦታው በመጎድጎዱ የነዳጅ ጉድጓድ ነው የሚመስላቸው፤›› በማለት የቀድሞ ታሪኩ ምን ይመስል እንደነበር በመጠኑም ቢሆን አካፈለን፡፡ ሾፌሩም የወያላውን ብሶት ሰምቶ ሲያበቃ፣ ‹‹ወንድሜ እንደዚህ የሚያደርግህ የነዳጅ መወደድ አይመስለኝም፡፡ ይልቁንስ እንዲህ የሚያብሰለስልህ የሱስህ ሰዓት ደርሶ ነው፡፡ ሰዓቱ ደርሷል፣ የሐራራ ዕድልህ ነው…›› አለው፡፡

ወያላውም መልስ አላጣም፣ ‹‹ዕድል ምናምን አትበለኝ፡፡ እንዲያውም፣

ዕድሌ ነው እንጂ መልኬ መቼ አነሰኝ፣

ብርቱካን ሲታደል ሎሚ የደረሰኝ፣

በሚለው ግጥም ላይ አለኝ ማሻሻያ፣

የተደበቀውን አጉልቶ ማሳያ፣

ፉንጋው መልኬ ነው እንጂ፣

ዕድል መቼ አነሰኝ፣

አፍንጫ ሲታደል ጆሮ እየደረሰኝ፤›› በማለት ግጥሙን አምበለበለው፡፡

ሾፌሩ በወያላው የቃላት አደራደር በጣም ተገርሞ፣ ‹‹ታዲያ እኔ ምን አልኩህ? አንተ እኮ ዕድልና ሱስ ነው እንጂ እዚህ የጣለህ ይኼኔ ከታዋቂዎቹ ገጣሚያን ተርታ በተሠለፍክ ነበር…›› አለው፡፡  ሾፌሩ ወሬውን በመቀጠል፣ ‹‹የት እንደሆነ ያነበብኳት አንድ ግጥም አለችኝ ላሰማህ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ወያላውም፣ ‹‹ኧረ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ አንዳንዴ እንኳን እንደዚህ ግጥምና መነባንብ እየሰማን አዕምሮአችንን እናድስ እንጂ፤›› ብሎ ጆሮዎቹን ቀጥ አደረጋቸው፡፡ ወያላና ሾፌር ታክሲ ውስጥ የግጥም ምሽት ያዘጋጁልን ይመስል የታክሲውን ዘፈን ማጫወቻ ዘጉት፡፡

ሾፌሩ ቀጠለ፣ ‹‹እኔ እተችሀለሁ አንተ ስማኝ ብቻ፣

ከንፈርህ ቅልብስ ነው እንደ ማር ስልቻ፤›› ብሎ ሳቁን ለቀቀው፡፡ ሾፌር ጠጅ ቤት ውስጥ ለታደመ አዝማሪ ያዝ እንግዲህ እያለ የሚገጥም ይመስላል፡፡

ይህንን የሰሙ ተሳፋሪዎች በጠቅላላ ወደ ወያላው ከንፈር አነጣጠሩ፡፡ ወያላው ይኼኔ  ለመልስ ቸኮለ፣ ‹‹እንደዚህ ብሎ የጻፈው ገጣሚ ማን ነበር?›› አለ፡፡ ሾፌሩም ከባድ የመልስ ምት እንደተዘጋጀለት ጠርጥሯል፣ ‹‹እንዴት?›› አለ፡፡ መልሱን ለመስማት እየጓጓ፡፡ ወያላው ወገቡን ይዞ ለሾፌሩ ግጥሙን ለቀቀበት፡፡

‹‹እንደ ሰማይ ጠርቶ ይታየኛል ሁሉም፣

ከላይ ፍፁም ውብ ነህ አላስተባብልም፣

ግን ቢያጠራጥረኝ እምነት ባልጥልበት፣

ጥያቄ አጫረብኝ የፀጉርህ መሠረት፤››

ወያላው ያልተጠበቀና በውብ ግጥም መልዕክት በማስተላለፉ ነው መሰል አንዳንዶች አጨበጨቡለት፡፡ የምሥጋና ቃላት ሊደረድሩለት የቃጣቸውም አልጠፉም፡፡ ‹‹በተለይም ጥያቄ አጫረብኝ የፀጉርህ መሠረት›› የሚለው ሐረግ በጣም የተራቀቀ ነው፡፡ ምክንያቱም ፀጉሩ ያረፈበት መሠረት ጭንቅላቱ ነው፡፡ ዋናው መልክ ሳይሆን ጭንቅላት ነው ብሎ ሾፌሩን ጭንቅላቱን መታው፡፡ ይህም ግጥም የገጣሚ ኑረዲን ኢሳ እንደሆነ የሚያውቁ አልጠፉም፡፡ ሆኖም ወያላው የተወሰነ ማሻሻያ አድርጎበታል፡፡ ታክሲ ውስጥ ምንጭ ሳይጠቀስ መጠነኛ ማሻሻያ አድርጎ በማቅረቡ አንድ ወጣት ተቸው፡፡ ‹ለምን አይዶል ላይ አትወዳደርም?› ያሉትም አልጠፉም፡፡ ሾፌሩ ግን፣ ‹‹አገባልኝ! አገባልኝ!›› ከማለት ውጪ ምንም መልስ አልሰጠውም፡፡ በነገራችን ላይ በዘፈን መተራረብ የአፍሪካውያን ባህል ነው፡፡ እንዲያውም የፈጠራ ችሎታቸውም የሚመዘንበት ነው፡፡ ሁለት ሰዎች ወደ መድረክ ይወጡና የሰውዬውን ሁኔታና ማንነት እየተመለከቱ በግጥምና በዜማ የሚተራረቡበት ጨዋታ አላቸው፡፡ ታዲያ ወያላና ሾፌሩ ወዲያው ያስታወሱን ይህንኑ ነው፡፡ በአገራችንም ቢሆን በግጥም፣ በአሽሙርና በአግቦ መተራረብ የነበረ ነው፡፡ በአዝማሪ አማካይነት በነገር የሚጎነታተሉ እንደነበሩ ይነገራል፡፡

ሾፌሩ ከወያላው ጋር መተራረቡ እንደማያዋጣው አውቆ ነው መሰል ጥያቄውን ቀየር አደረገው፡፡ ‹‹ለዚያች አይተህ ላፈቀርካት ልጅ ምን ብለህ ነበር ግጥም የጻፍክላት?›› አለው፡፡ ወያላው ትዝ አለው፡፡ ትንሽ ካሰላሰለ በኋላ፣

‹‹ሀብታም ሠፈር ሄጄ፣

ቆንጆ ልጅ ወድጄ፣

የልቤን ሳልነግራት ሄደች ወደ ዲሲ፣

እኔም ወደ ታክሲ፤››

በማለት የወደዳት ጉብል ወደ ዋሸንግተን ዲሲ መሄዷንና እሱም ወደዚህ ሥራ መግባቱን ተናገረ፡፡ ወያላው እንዲህ ቃላትን እያሳካ ግጥሞቹን ሲያነበንብ የተገረመበት አንድ ጎልማሳ፣ ‹‹ለምን ወያላ ሆንክ?›› አለው፡፡ ጉደኛው ወያላም፣ ‹‹እህል ውኃ… እህል ውኃ…›› እያለ የአስቴር አወቀ ዘፈን በሚገርም ቅላፄ ዘፈነለት፡፡

ሾፌሩ በጣም ተደስቶ ነበር የሚያዳምጠው፡፡ የእኛንም ጆሮ መያዙን አልተጠራጠረም፡፡ በአስገራሚ የግጥም መነባንቦቹና የአዘፋፈን ሥልቱ ጆሮአችንን ወጥሮ የያዘው ወያላ ንቁ ከመሆኑ የተነሳ እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በንቁ ዓይኖቹ ይከታተላል፡፡ በወያላው በፍጥነት የመግጠም ብቃት የተደነቀ አንድ ሰው፣ ‹‹ለመሆኑ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ጦርነት አንስተው ስለተደቆሱት ወፈፌዎች ምንም ግጥም አልጻፍክላቸውም?›› አለው፡፡ ወያላውም፣ ‹‹ጽፌያለሁ፡፡ ግጥሙ ግን ጥያቄ ነው…›› አለ፡፡ ይኼ ወያላ ሁለገብ ዕውቀት ሳይኖረው አይቀርም በማለት አጠገቤ የተቀመጡ ሁለት ሰዎች አንሾካሾኩ፡፡

‹‹እነሱ በተድላ ውስኪ እየተጎነጩ፣

ምስኪን ሕዝባቸውን ምነው ደም አራጩ?››

ጥያቄውን ያቀረበለት ሰውዬ በጣም አደነቀው፣ አሞካሸው፣ አበረታታው፡፡ ለሌሎችም ቢጤዎቻቸው ግጥም እንዲጽፍ ሐሳብ አቀበለው፡፡ አንዲት የወያላው ነገር ያስገረማት ኮረዳ፣ ‹‹ለመሆኑ ሰዎቹን በቅርብ ታውቃቸዋለህ? ሰዎቹ ውስኪ ሲጠጡ የት ነው ያየኸው?›› አለችው፣ የተናደደች ትመስላለች፡፡ ወያላው እየሳቀ፣ ‹‹እነሱን በቅርበት ብታውቂ ኖሮ እንዲህ አትይም ነበር፡፡ ሕዝባችንን በዘር ለመከፋፈል ሞክረው አልሳካ ሲላቸው ሲሳደቡ እኮ ሰክረው ነበር…›› ሲላት ተሳፋሪዎች በሙሉ በሳቅ አውካኩ፡፡

አንዲት ወጣት የወያላው ንግግር የተዋጠላት አትመስልም፡፡ ወያላውን ቁም ስቅሉን አሳየችው፡፡ ‹‹አራት ብር ክፈይ…›› ሲላት፣ ‹‹የመቶ ብር ዝርዝር አለህ?›› አለችው፡፡ በሁኔታዋ በጣም ስለተናደደ፣ ‹‹አዎ አለ…›› አላት፡፡ መቶ ብር መያዝ አለመያዟን ለማረጋገጥ የፈለገ ይመስላል፡፡ ይጠይቀኛል ብላ አላሰበችም ነበር፡፡ ‹‹መቶ ብሩን ግን ገና ከባንክ አላወጣሁትም…›› አለችው እንደ መሞላቀቅ እያለች፡፡ ቀጥላም፣ ‹‹ካላመንከኝ የባንክ ቡኬን ላሳይህ እችላለሁ…›› ብላ ሳቅ አለች፡፡ የሚወራውን ይሰማ የነበረው ሾፌር በወጣቷ ሁኔታ እየተገረመ፣ ‹‹ማነሽ በክሬዲት ካርድ አገልግሎት መስጠት አልጀመርንም…›› ሲላት፣ ‹‹ታዲያ ይኼ የራሳችሁ ኋላቀርነት ነዋ…›› ብላ መለሰችለት፡፡ ወያላው፣ ‹‹ማነሽ እሺ የባንክ ቡክሽን አሳይን…›› አላት፡፡ በጣም ተቆጣች፡፡ ‹‹ማነሽ ትለኛለህ እንዴ? እኔኮ እናትና አባቴ ያወጡልኝ መጠሪያ ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ማነሽማ ልትለኝ አይገባም…›› እያየች በቁጣ ተንቀጠቀጠች፡፡ ወያላው መልሶ፣ ‹‹ለነገሩ አንቺ እንኳን የባንክ ቡክ የፌስቡክ አካውንትም የለሽ…›› ብሎ ተሳለቀባት፡፡

‹‹ታዲያ ማን ብዬ ልጥራሽ? እሺ ሱናሚ ልበልሽ?›› አላት፡፡ ምን ለማለት እንደፈለገ የገባት አትመስልም፡፡ ‹‹ሶሎሜ አይደለሁም…›› ስትል ተሳፋሪዎች በሙሉ ሳቁባት፡፡ ሳትደርስ ነው መሰል፣ ‹‹ወራጅ!›› አለ ብላ ወርዳ ሄደች፡፡ ወያላው፣ ‹‹ዛሬ ደግሞ ምን ዓይነቷ ሱናሚ የሆነች ልጅ ናት ያጋጠመችን?›› አለ፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹አናወጠችን እኮ!›› አለ፡፡ በእርግጥም ለአጭር ጊዜም ቢሆን ታክሲዋን ለማናወጧ መስካሪ ቢባል ሁላችንም እጃችንን ማውጣታችንን አንጠራጠርም፡፡ የሆነው ሆነና ልጅት ያናደዳት ጦርነት አስነስተው የተደቆሱት ሰዎች ጉዳይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ያ ወሬ ከመነሳቱ በፊት ድምጿ አልተሰማም ነበር፡፡ አንዳንዴ እኮ ድምፃችን ጎልቶ የሚሰማን የሚኮረኩረን ነገር ሲኖር ነው፡፡ ባንናገር እንኳ ወይ እንስቃለን ካልሆነም በንዴት እንንተከተካለን፡፡ ኮርኳሪ አይጥፋ፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት