Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በትግራይ ባንኮችን ሙሉ ለሙሉ ሥራ የማስጀመር ሒደት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በትግራይ ክልል ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ከ600 በላይ የባንክ ቅርንጫፎች የአብዛኛዎቹ መቀሌ ላይ ሥራ ቢጀምሩም፣ ከመቀሌ ውጪ ያሉትን ግን በስፋት ሥራ ለማስጀመር አልተቻለም፡፡

በትግራይ ክልል ያሉ ባንኮችን ሥራ ለማስጀመርና በአጠቃላይ በክልሉ ያለውን የባንክ አገልግሎት በተመለከተ፣ ብሔራዊ ባንክና ባንኮች እየመከሩበት ነው፡፡ እስካሁን በተሰበሰበው መረጃ መሠረትም ሥራ የጀመሩት ቅርንጫፎች ቁጥር 161 ደርሰዋል፡፡ 440 ያህሉ ደግሞ ሥራ አልጀመሩም፡፡

አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ከተባሉት 161 የባንክ ቅርንጫፎች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የተከፈቱት በመቀሌ ነው፡፡ ይህም የአብዛኛዎቹ ባንኮች አገልግሎት በመቀሌና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች እንዲወሰን አድርጓል፡፡

መረጃዎች የሚያመለክቱት፣ ማይጨውና አላማጣን ጨምሮ ከመቀሌ ውጪ የባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጡባቸው ያሉ ከተሞች ቁጥር ከስድስት ያልዘለለ መሆኑን ነው፡፡

ሥራ ያልጀመሩትን ቅርንጫፎች ወደ ሥራ ለማስገባት ፍላጎት ያለ ቢሆንም፣ አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችሉ ሁኔታዎች እስኪመቻቹ መጠበቅ ግድ ሆኗል፡፡

ከመቀሌ ውጪ ያሉ የባንክ ቅርንጫፎችን ወደ ሥራ ለማስገባት አዳጋች ከሆኑባቸው ምክንያቶች አንዱ የኤሌክትክሪክና የኢንተርኔት አገልግሎት አለመጀመር ነው፡፡

ከዚህም ሌላ አንዳንድ ቅርንጫፎች ባሉባቸው አካባቢዎች የፀጥታ ችግር መኖሩ ሥራን ለማስጀመር አላስቻለም፡፡ ይህም ባንኮቹ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በነበራቸው ውይይት የተገለጸ ሲሆን፣ ክፍተቶቹ ከተቀረፉ አገልግሎቶቻቸውን እንደሚጀምሩ ታውቋል፡፡

በክልሉ የባንክ አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር ሌላ ፈተና የሆነው አንዳንድ የባንክ ቅርንጫፎች የሚገኙባቸው አካባቢዎች ቅርንጫፎቹ ስላሉበት ወቅታዊ ሁኔታ በቂ መረጃ የሌለ መሆኑ ነው፡፡

ከመቀሌ ውጪ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ያሉ አንዳንድ ቅርንጫፎች የሕግ ማስከበር ከተጀመረ በኋላም ሆነ በፊት ዘረፋ የተፈጸመባቸው በመሆኑ፣ በቅርንጫፎቹ ያለውን የገንዘብ መጠን እንኳን ለማወቅ አለመቻላቸው እንደተግዳሮት ታይቷል፡፡

በክልሉ ያሉ የባንክ ቅርንጫፎች መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ከሕግ ማስከበር ሥራው ጋር ተያይዞ የተዘረፉ ቅርንጫፎች በተመለከተ መረጃዎችን የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ቅርንጫፎችና ኤቲኤሞች ላይ ጉዳት በመድረሱ መረጃዎች ተሰባስበው መጠኑ ይገለጻልም ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ አገልግሎታቸውን እንዲያቆሙ ውሳኔ ከሰጠባቸው ምክንያቶች መካከል በአንዳንድ ቅርንጫፎች ላይ ተፈጸመ የተባለው ዘረፋ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

አንዳንድ የባንክ ኃላፊዎች፣ አሁንም አገልግሎት የጀመሩ ቅርንጫፎች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ እንዲቀጥሉ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና የፀጥታ ኃይሉ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የአገልግሎቱ መስተጓጎል በክልሉ የሚገኙ የባንክ ደንበኞችንም ሆነ ባንኮችን የጎዳ ሲሆን፣ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ላይም የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡

የሕግ ማስከበር ዘመቻው መጠናቀቅ ከተገለጸ በኋላ በመቀሌ ከተማ አገልግሎት በመጀመር ቀዳሚው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፣ የግል ባንኮችም በተወሰነ ቅርንጫፎቻቸው በተለያየ ጊዜ አገልግሎታቸውን ጀምረዋል፡፡

በመቀሌ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዳግም የተጀመረው የባንክ አገልግሎት ተቋርጦ የነበረውን የብር ኖት ቅያሪ እንዲቀጥል ያደረገ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወቅቱ ባወጣው መመርያ መሠረትም፣ በትግራይ ክልል ቅርንጫፎቻቸውን ሥራ ያስጀመሩ ባንኮች ለ14 ቀናት የብር ኖት ቅያሪ ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡  

ጥር 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጣው መመርያ ደግሞ፣ በትግራይ ክልል ዳግም የባንክ አገልግሎት ሲጀመር የቀጠለውና ከታኅሳስ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለ14 ቀናት የዘለቀው የብር ቅያሪ ቀነ ገደብ ተጠናቋል ብሏል፡፡

በመቀሌ የጊዜ ገደቡ የተጠናቀቀው የብር ኖት ቅያሪ ግን፣ ከመቀሌ ውጪ ባሉ ቅርንጫፎች የሚቀጥል መሆኑንና የጊዜ ገደቡ አሰጣጥም በከተሞች እንደሚወሰን ተነግሯል፡፡

‹‹በእስካሁኑ የክልሉ የብር ቅያሪ አፈጻጸም ግምገማ መሠረት የተራዘመው ጊዜ ለእያንዳንዱ የባንክ ቅርንጫፍ የተሰጠ መሆኑ ቀርቶ ለእያንዳንዱ የክልሉ ከተማ እንዲሆን ተደርጓል፤›› የሚለው የብሔራዊ ባንክ መግለጫ፣ ከጥር 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ አንድ ከተማ ቀድሞ አገልግሎት የሚጀምር የባንክ ቅርንጫፍ ሲኖር፣ በዚያ ከተማ የሚሰጠው የብር ቅያሪ የጊዜ ገደብ የሚሠላው ይኼው የባንክ ቅርንጫፍ ሥራ ከጀመረበት ቀን አንስቶ ለ14 ቀናት ብቻ ይሆናል ብሏል፡፡

ዘግይተው ሥራ የሚጀምሩ ሌሎች የባንክ ቅርንጫፎች በከተማው አሮጌ ብር መቀየር የሚችሉትም በዚሁ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ብቻ እንደሚሆን ጠቅሶ፣ መቀሌን ጨምሮ የብር ቀያሪ ከተጀመረ 14 ቀናት ባለፋቸው የትግራይ ከተሞች ሲሰጥ የነበረው የብር ቅያሪ አገልግሎት ከጥር 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መቋረጡን ገልጿል፡፡

በየትኛውም የክልሉ ከተሞች የሚገኙ ኅብረተሰቦች ይህን ተገንዝበው በተጠቀሱት 14 ቀናት ብቻ አገልግሎቱን እንዲያገኙ አሳስቧል፡፡

አንድ ባንክ በአንድ ከተማ የብር ቅያሪ ከጀመረ ከሰባተኛው ቀን በኋላ ሌላ ባንክ አገልግሎት ቢጀምር፣ የብር ቅያሪን የሚያደርገው በቀሪዎቹ ሰባት ቀናት ብቻ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ የባንክ ቅርንጫፍ ሥራ ሲጀምር፣ ሥራ ከጀመረበት ቀን አንስቶ ለ14 ቀናት የብር ቅያሪ ያደርጋል የሚል ሲሆን፣ ይህ አሁን ቀርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች