Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከእንስሳት ሀብት ጋር ያልተመጣጠነው የመድኃኒት አቅርቦት

ከእንስሳት ሀብት ጋር ያልተመጣጠነው የመድኃኒት አቅርቦት

ቀን:

በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ ኢትዮጵያ የመጀመርያ መሆኗ ይወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ካላት የእንስሳት ሀብት አኳያ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚል ዕርምጃ እንዳልተራመደች ይነገራል፡፡

በኢትዮጵያ በእንስሳት ዘርፍ የምግብ ፍላጎትን በማሟላት፣ በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የገቢ ምንጭና የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ አኳያ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና በተለያዩ መንገድ የግብርና ዘርፍን በመደገፍ ትልቅ ሚና እንዳለው ይታወቃል፡፡

በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት 19 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ከእንስሳት ሀብት መሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ከ16 እስከ 19 በመቶ የሚሆነው የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ትንሽ የማይባል ሚና እንዳለው ይወሳል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ የእንስሳት በሽታዎች መንሰራፋት፣ አጥጋቢ የሆነ የእንስሳት ዝርያዎች ማሻሻያ አለመኖር፣ የግብይይት ውስንነትና ለሌሎችም ችግሮች ለዘርፉ አለማደግ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡

በዋነኛነት የእንስሳት ሕክምና አናሳ መሆንና ሕክምናው በተፈለገው ልክ ያለማደግ የግልና የመንግሥት ዘርፎች ተናበው ያለመሥራትም ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ዮሐንስ ግርማ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፣ በኢትዮጵያ ከ61 ሚሊዮን በላይ የቀንድ ከብቶች፣ ከ30 ሚሊዮን በላይ በጎችና ፍየሎች፣ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ዶሮዎች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ግመል፣ አህያ፣ ፈረስ በቅሎና ሌሎችም የእንስሳት ሀብቶች በኢትዮጵያ አሉ፡፡

ይሁን እንጂ የእንስሳት ሀብትና በአገር ውስጥ ከሚገባው መድኃኒትና ከሌሎች አገልግሎት አንፃር ዘርፉን እየጎተተው እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በአማካሪው አገላለጽ፣ በእንስሳት ሀብት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥራቸውን ሊያመናምኑ የሚችሉ በሽታዎችን ለማጥፋት መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ እየጣረ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ካለው እምቅ ሀብትና አገር ውስጥ የሚገባው የሕክምናና መድኃኒቶች ብዛት ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡

ለወተት፣ ዕንቁላል፣ የሥጋ ተዋፅዖ፣ አደልቦ ለመሸጥና ለሌሎች ግልጋሎቶች የሚውሉት የእንስሳት ሀብቶች ለዘርፉ የሚቀርበው የመድኃኒት አቅርቦት ዝቅተኛ በመሆኑ ምርታማነታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ አልቀረም፡፡

በአጠቃላይ በዓለም ካለውና ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሀብት ዕርባታ ዕድገት አንፃር ያለው የመድኃኒት ዓይነቶችና ብዛት በጣም ዝቅተኛ ነው የሚሉት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ ከተወሰኑ መድኃኒቶች አኳያ የወተት ላሞች ላይ የሚከሰተው በሽታ የወተት ምርትን የሚቀንስ ሲሆን፣ ለዚህ በሽታ የሚሆነውን መድኃኒቶችን ለማግኘት የአርብቶ አደሮች ለማግኘት እንደሚቸገሩ ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል የእንስሳት መድኃኒት አስመጪዎችም ተፈላጊ የመድኃኒት ዓይነቶችን እንጂ የሚጠቅሙ መድኃኒቶችን አስገብተው ለአርብቶ አደሩ የማቅረብ ውስንነት እንዳለ ገልጸዋል፡፡

ብዛት ያላቸው እንደ ድንበር ዘለል በሽታዎች፣ ምርትና ምርታማነትን የሚቀንሱ መኖራቸውን የገለጹ ሲሆን፣ አሁን ላይ ለስድስት የበሽታ ዓይነቶችን ለእንስሳት ክትባት እየተሰጠ መሆኑንም ዶ/ር ዮሐንስ ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ለእንስሳት መድኃኒት ይገባሉ ተብለው የተመዘገቡ ከ400 ያላነሱ ቢሆንም 70 የሚሆኑ መድኃኒቶች ብቻ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንደ አማካሪው ታይታ፣ አገር ውስጥ የሚገቡት ጥቂት መድኃኒቶች መሆናቸው፣ ኅብረተሰቡም ስለ መድኃኒቶቹ ያለው ዕውቀት (ግንዛቤ) አናሳ በመሆኑ አስመጪዎችም ደፍረው መድኃኒቱን ለማምጣት ሥጋት ይሆንባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል አስመጪዎች እንደ ልብ የእንስሳት መድኃኒት ለማስመጣት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ መሆኑን ዶ/ር ዮሐንስ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የእንስሳት መድኃኒት፣ መኖ አስተዳደር ቁጥጥር ጥራትና ደረጃ ምዝገባ ፈቃድ ዳይሬክተር ሰለሞን ከበደ (ዶ/ር)፣ በዋናነት የእንስሳት መድኃኒቶችን ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ የሚፈቅደው ባለሥልጣኑ ነው፡፡

የመድኃኒት ፍላጎት የሚመጣው በአስመጪዎች ሲሆን ማምጣት የሚፈልጉትን መድኃኒት ካስመዘገቡ በኋላ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ፈቃድ ይሰጣል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት በሁሉም ዝርያ ከፍተኛ ቁጥር ሲሆን፣ አካባቢያዊ አየር ደግሞ ለተለያዩ በሽታዎች እንስሳትን እንደሚያጋልጣቸው ዶ/ር ሰለሞን ይናገራሉ፡፡

ካሉት የበሽታዎች ብዛትና ዓይነት አንፃር በቂ የሆነ መድኃኒት እየቀረበ ነው ለማለት አይቻልም የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ መድኃኒቶቹን የሚቀርቡት በግል አስመጪዎች በመሆኑ ተደራሽ ለማድረግ አልተቻለም፡፡

የግሉ ባለሀብት ደግሞ ትኩረት አድርጎ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባው ትርፋማ የሚያደርገው ላይ መሆኑ ሌላው ችግር መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡

በዚህም በጣም አስፈላጊ የሆኑና በዝቅተኛ ወጪ የሚፈልጉ መድኃኒቶች ሲገቡ አይስተዋሉም ሲሉ ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ለሰዎች ሕክምና የሚውሉ የመድኃኒት አቅርቦትን ብንመለከት የግል ባለ ሀብቶች የሚያስገቡትን መድኃኒቶች እንዳሉ ሆነው፣ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ አማካይነት ደግሞ ያለውን ክፍተት እንዲሞሉ ተደርገው በተለያዩ የጤና ተቋም ይሠራጫሉ፤›› ሲሉ ዶ/ር ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን በእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት በኩል የእንስሳት ግብዓት አቅርቦት ኮርፖሬሽን የሚባል ድርጅት ቢኖርም ክፍተቱን በሚሞላ መልኩ እየሠራ ነው ለማለት እንደማያስደፍር ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ፡፡

የብቃት ማረጋገጫ አውጥቶ መድኃኒት የማስመጣት ፈቃድ ያለው ኮርፖሬሽኑ ቢሆንም የግል ባለሀብቶች የሚያስመጡትን የመድኃኒት ዓይነቶች ወደ አገር ውስጥ እንደማያስገባም ጠቁመዋል፡፡

በክልል ደረጃ ያሉ የእንስሳት ክሊኒኮች ማሟላት  ያለባቸው የመመርመሪያ መሣሪያዎች ስለማይሟሉ በትክክል በሽታውን ለይቶ መድኃኒት ከመስጠትና መሟላት ያለበት የመድኃኒት ዓይነት ከመጠየቅም አንፃር ክፍተት መኖሩም ተገልጿል፡፡

የግብርና ሚኒስቴርና የግብርና ቢሮዎች ለእንስሳት ክሊኒኮች ግብዓት ከማሟላት አንፃር በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ዶ/ር ሰለሞን ይመክራሉ፡፡

በባለሥልጣኑ በኩል የእንስሳት መድኃኒት አስተዳደር መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን በትክክል የመድኃኒት አቅርቦት የግንዛቤ ክፍተት ሙሉ በሙሉ ባይቀርፍም ችግሩን በተወሰነ መልኩ ሲያግዝ እንደሚችል ዶ/ር ሰለሞን ይናገራሉ፡፡

በእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት የተነሱ ችግሮች ዘርፈ ብዙ ሲሆኑ፣ አንድና ዋነኛው አዋጅ ላይ ያሉ ማነቆዎች እንዳሉ ተገልጿል፡፡

የመድኃኒት ናሙና ተልኮ በላቦራቶሪ ካልተፈተሸ መድኃኒት መመዝገብ የማይቻል ሲሆን፣ ለዚህም ከሦስት ወራት በላይ ጊዜ የሚወስድና አንድን መድኃኒት ለማስመዝገብ 500 ዶላር እንደሚጠየቅ ተገልጿል፡፡

በአገር ውስጥ የተመዘገቡ 650 የሚደርሱ መድኃኒት መኖራቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ሰለሞን፣ ከዚያ ውስጥ 24 በመቶው ብቻ በአገር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት ላይ የተሠማሩ አስመጪዎች 100 ሲሆኑ፣ ጅምላ አከፋፋዮች ደግሞ ከመቶ በታች መሆናቸውን ተገልጿል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር፣ የእንስሳት ሐኪሞች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ እንስሳት መድኃኒት መኖ አስተዳደርና ቁጥጥርና ባለሥልጣን፣ በእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት ችግርና መፍትሔዎቻቸው ላይ ጥር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረጉት ውይይት ዘርፈ ብዙ ችግር እንዳለበት የተገለጸው የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦትና ሕክምና በቀጣይ ከታች ጀምሮ ተናቦ መሠራት እንዳለበት ሐሳብ ተነስቷል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ ጥሩነሽ ተፈራ እንደተናገሩት የፖሊስና የአዋጅ ችግሮች በተመለከተ ችግሮችን ለመቅረፍ ወደ ኋላ እንደማይሉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...