Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ ከሚመረተው ቡና 66 በመቶ ያህሉ ለዓለም ገበያ መቅረብ እንዳልቻለ ተጠቆመ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ከሚመረተው ቡና ከ66 በመቶ በላይ የሚሆነው በጥራት ጉድለት ምክንያት፣ ለዓለም አቀፍ ገበያ መቅረብ እንደማይችል የኢትዮጵያ ቡና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

አገሪቱ ከምታመርተው ቡና ውስጥ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የሆነ የጥራት ደረጃ በመያዝ ለዓለም አቀፍ ገበያ 2.6 እስከ ሦስት ዶላር ድረስ መሸጥ የሚችለው፣ 34 በመቶ  ያህል እንደሆነ አስታውቋል።

ከአጠቃላይ ምርቱ ውስጥ በጥራት ደረጃው አራተኛ በአምስተ ላይ የተቀመጠቡና ምርት ለዓለም አቀፍ ገበያ ቢቀርብም ውድቅ እንደሚደረግ፣ ይሸጥ ከተባለም አንድ ዶላር በታች መሆኑን የተናገሩት የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ናቸው።

  ዳይሬክተሩ ይህን የተናገሩት የተቋማቸውን 2013 .ም. የመጀመርያ ግማሽ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ጥር 19 ቀን 2013 .ም. ሲያቀርቡ ነው፡፡

የጥራት ችግሩ በዋነኝነት የተጠቀሰው በኢትዮጵያ ያሉ የቡና ተክሎች 70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸው 50 ዓመት በላይ የሆኑና ዛፍ የሚባሉ ዓይነት መሆናቸው ሲሆን፣ ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት  መስጠት አለመቻላቸውን በምክንያትነት አስረድተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በቂ የቡና ምርት በመኖሩ ተጠቃሚዎች የተሻለ ምርት ፈልገው እንደሚገዙ፣ በኢትዮጵያ የሚመረተው ቡና ከጥራቱ ብዛቱ ስለሚበልጥ የሚፈለገውን ገቢ ማግኘት ማዳገቱን ተናግረዋል፡፡ አገሪቱ  የምታመርተው የቡና ምርት ከጥራት ጋር ቢሆን የተሻለ ገቢ ማስገኘት ይቻላል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

የቡና ተጠቃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ በዓለም ላይ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በዘርፉ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አሁን ያሉትን ያረጁ የቡና ዛፎች በመጓንደልና በማንሳት፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት 200 ሺሕ ሔክታር በላይ በአዳዲስ ተክሎች እንዲተኩ በማድረግ እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

‹‹አርሶ አደሩ ከተጠቃሚነት አንፃር በድንገት ተነስቶ የቡና ተክልን ነቅሎ በጫት ወይም በባህር ዛፍ ቢቀይር አይገርመንም፤›› ብለዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት 139,835 ቶን ቡና በመላክ 525 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፣ የዕቅዱን 65 በመቶ ብቻ በማሳካት 91,812 ቶን ቡና ወደ ውጭ ተልኮ 304.5 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ለአፈጻጸሙ መቀነስ በዋናነት በኮቪድ-19 ተፅዕኖ ምክንያት አንዳንድ ገዥ አገሮች  የገቡትን ኮንትራት በጊዜው ባለመፈጸማቸውና እንዲራዘምላቸው በማድረጋቸው  እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአገር ወስጥ የቡና ዋጋ ከዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ጋር የማይናበብ በመሆኑ፣ የዓለም የቡና ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል  ባለማሳየቱ የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን 41,155 ቶንና በዋጋ 60 ሚሊዮን ዶላር ወይም 16.5 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ተናግረዋል።

በዘርፉ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ያሉት አዱኛ (ዶ/ር)፣ ከቡና ጥራት ባለፈ የሎጂስቲክሰ አገልግሎቱ አለመዘመን በራሱ ለገቢ መቀነሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የተሻሻለ የቡና ዝርያ መኖሩ፣ አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ የመቀበል ፍላጎቱ እየጨመረ መምጣቱና ምቹ የአየር ሁኔታ መኖሩ የቡና ምርችን የበለጠ ማሳደግ እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ቡና የሚቀበሉ አገሮች አምስት ብቻ እንደነበሩ፣ ከአንድ ዓመት ወዲህ ግን ፍላጎት ያላቸው አገሮች ወደ 35 መድረሳቸው ተነግሯል፡፡

በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ወደ ውጭ ከሚላክ ቡና 2.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እንደታቀደ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

 ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሆና ሳለ የራሷ አገራዊ መለያ (Brand) የላትም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዚህም ሳቢያ ከኢትዮጵያ የተሸጠን ቡና የባለቤትነት (Property Right) የመጠየቅ መብት አገሪቱ የላትም ብለዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድም የኢትዮጵያን ቡና ከሌላ ቡና ጋር ቀላቅሎ ለመከላከልና ለማስቀረት ታስቦ ‹‹የኢትዮጵያ ቡና›› የሚል የራሱን የሆነ መለያ (ሎጎ) ተሠርቶ፣ በአገር ውስጥ የማስመዝገብ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነና ወደፊትም ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅና ለማስመዝገብ ሥራ መጀመሩን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች