- በእነ አቶ ስብሐት ነጋ ላይ 14 የምርመራ ቀናት ተፈቀደ
- መርማሪዎች ሕግና ፖለቲካን ቀላቅለው ለፍርድ ቤት እንዳያቀርቡ ተጠየቀ
በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ሌሊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተነገረና ከ29 ቀናት በኋላ ኅዳር 23 ቀን 2013 ዓ.ም. እጃቸውን የሰጡት የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ለ40 ቀናት፣ የት እንደታሰሩና ለምን በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤት ተናገረ፡፡
የምርመራ ቡድኑ ይህንን የተናገረው ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ወ/ሮ ኬሪያን፣ የፓርላማ አባልና የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩትን ወ/ሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔርን ፍርድ ቤት ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡ መርማሪ ቡድኑ ሁለቱን ተጠርጣሪዎች ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ፍርድ ቤት አቅርቦ 14 የምርመራ ቀናት ሲፈቀድለት፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት፣ በተለይ ወ/ሮ ኬሪያ ለምን በ48 ሰዓታት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እንደቀሩና ለ40 ቀናት የት እንደታሰሩ አጣርቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶ እንደነበር ጠበቆቻቸው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ በማቅረባቸው ነው፡፡
መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው 14 የምርመራ ቀናት ውስጥ በተጠርጣሪዋ ላይ የሠራውን ምርመራ ለፍርድ ቤቱ ከመናገሩ በፊት፣ ትዕዛዙ መከበሩን ወይም ለምን እንዳላከበረ ፍርድ ቤቱ እንዲያረጋግላጥላቸው ጠበቆቻቸው ጠይቀዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት ተጠርጣሪዋ ለ40 ቀናት የት እንደነበሩ ለማጣራት ሞክሯል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የፌዴራል ፖሊስና መከላከያ በርካታ ተጠርጣሪዎችን ይዘው ስለነበርና እያንዳንዱን ተጠርጣሪ የመለየት ሥራ ይሠራ ስለነበር፣ የፌዴራል ፖሊስ የሥራ ድርሻም ሰፊ ስለነበር ለማጣራት እንደተቸገረ ገልጿል፡፡ አሁን ምርመራውን እየሠራ የሚገኘው መርማሪ ቡድን ተጠርጣሪዋን ያገኘው ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በመሆኑንና ፍርድ ቤቱም የሚያውቀው ይህንን በመሆኑ፣ ከዚህ ውጪ ያለውን የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ተናግሯል፡፡
የወ/ሮ ኬሪያ ጠበቆች አቶ ዘረሰናይ ምሥግናና አቶ ሐፍቶም ከሰተ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበውን ክርክር በመቃወም እንዳስረዱት፣ ፌዴራል ፖሊስ ሰፊ አይደለም፡፡ እያንዳንዱን ተጠርጣሪ ሲይዝ በሕዝባዊ መዝገብ ላይ ይመዘግባል፡፡ ማን የት እንዳለ ያውቃል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ከጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በፍርድ ቤት በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ ምን እንደሠራ ከመግለጽ ባለፈ፣ ወ/ሮ ኬሪያ የትና እንዴት እንዲቆዩ ያደረጋቸው አካል ቀርቦ እንዲያብራራ ማድረግ እንጂ፣ በራሱ ማብራራት እንደሌለበት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
በሕጉ መሠረት በ48 ሰዓታት ውስጥ መቅረብ ሲገባቸው ለ40 ቀናት የት እንደታሰሩ እንኳን ሳይታወቅ የመቆየታቸውን ሒደት፣ ፍርድ ቤቱ መፍትሔ ካልሰጠበት፣ የፍርድ ቤቱን የወደፊት ሒደት አጠራጣሪ እንደሚያደርገው ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የታሰሩበት ቦታ በግልጽ መነገር እንዳለበትም አክለዋል፡፡ እነሱ እንኳን (ጠበቆቹ) ተጠርጣሪዋ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ እንኳን ለማግኘትና ለማነጋገር ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካላቸውና በአዲስ አበባ ከተማ ዘመዶቻቸውን ማግኘት ስላልቻሉ የጥብቅና ውል መዋዋል እንዳልቻሉም ጠቁመዋል፡፡
ደንበኞቸው የተያዙት ፍርድ ቤቱ በሰጠው የመያዣ ትዕዛዝ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤት የቀረቡት ግን ከ40 ቀናት በኋላ ነው፡፡ ነገር ግን መርማሪ ቡድኑ እሱ ያገኛቸው ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሆነ መግለጹ ተገቢ አይደለም፡፡ ሕጉ ለሁሉም እኩል ከሠራ ደንበኛቸው፣ ‹‹መቼና የት ተያዙ፣ የት ቆዩ?›› የሚለውን ፍርድ ቤቱ መጠየቅ አለበት፡፡ የሰጠውን ትዕዛዝ ማረጋገጥ እንዳለበት ጠቁመው፣ ሕጉ የተጻፈው ለነበረው፣ ላለውና ወደፊት ለሚመጣው ታሳቢ ተደርጎ በመሆኑ፣ የሰጠውን ትዕዛዝ መተግበር አረጋግጦ መመዝገብ እንዳለበት በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ ነፃና ገለልተኛ መሆን እንዳለበትና ኃላፊነቱም መሆኑንም ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡
ያለውን ወቅታዊ ጫናና የአገሪቱን ሁኔታ የሚረዱ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ግን ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ወንጀል በተሳተፉበት ልክ እንጂ ለተገኘው ሁሉ የሚታደል መሆን ስለሌለበት ምርመራው በአግባቡ ሊካሄድና ሊመራ እንደሚገባውም ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ራሳቸው ተጠርጣሪዎቹ የትና እንዴት እንደቆዩ እንዲናገሩ ጠይቋቸው ወ/ሮ ኬሪያ እንደተናገሩት፣ ‹‹እኔ ለ40 ቀናት በፌዴራል ፖሊስ አንድ ቤት ውስጥ ተዘግቶብኝ ነበር፡፡ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እየመጣች አጠቃላይ መረጃ ትቀበለኝ ነበር፡፡ በታሰርኩበት ወቅት ማንንም አላገኝም ነበር፡፡ አሁንም እዚያው ነኝ፤›› ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ሙሉም ተጠይቀው፣ ለ31 ቀናት በታሰሩበት ቦታ (ለብቻቸው) ለምን ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ ሲጠይቁ፣ ‹‹እስከምትሰባሰቡ ነው፤›› ይሏቸው እንደነበር ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ እስከ ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ወ/ሮ ኬሪያ ከታሰሩ 61 ቀናት ሲሆናቸው፣ ወ/ሮ ሙሉ 51 ቀናት እንደሆናቸው ጠበቆቻቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ በሁለቱ ተጠርጣሪዎች ላይ በተሰጠው 14 ቀናት የሠራውን ምርመራ በሚመለከት እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ ከመደበኛ የመንግሥት አወቃቀር ውጪ ተደራጅተው፣ ብሔርንና እምነትን መሠረት ያደረገ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ፣ ንፁኃን እንዲገደሉና የአገር ንብረት እንዲወድም አስደርገዋል፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የትግራይ ልዩ ኃይልና መከላከያ ሠራዊቱን የከዱ አባላት፣ በሰሜን ዕዝ ላይ ጦርነት እንዲከፍቱ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚዎችን ሲያማክሩ እንደነበር ገልጿል፡፡ የአሥር ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ በመቀሌ የነዳጅ ዲፖ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የደረሰባቸውን ጉዳት አሥልተው እንዲያሳውቁ ደብዳቤ መጻፉን፣ የመርማሪ ቡድኑ በማዋቀር ወደ ትግራይ ክልል ልኮ የምርመራ ውጤትና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች የምርመራ ውጤት ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን በማስረዳት 14 ተጨማሪ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤት የተጠርጣሪዎቹን ተሳትፎ እንዲያስረዳ ለመርማሪ ቡድኑ ጥያቄ አቅርቦለት፣ የሐሳብና የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር የሚሳይ ማስረጃ ማግኘቱንና የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል በመሆናቸው፣ የተለያዩ ውሳኔዎችን ከኮሚቴው ጋር ማሳለፋቸውን ተናግሯል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ባቀረቡት መከራከሪያ ሐሳብ፣ ደንበኞቻቸው የተያዙት ከሁለት ወራት በፊት ነው፡፡ መርማሪ ፖሊስም የቀረው የሰዎችን ምስክርነት መቀበል በመሆኑና ምስክሮቹም እነ ማን እንደሆኑ የሚያውቁበት ሁኔታ ስለሌለ፣ የዋስትና መብታቸውን በሕጉ በተቀመጠው መሠረት በጠባቡ (Exception) ተርጉሞ የዋስትና መብታቸውን እንዲጠብቅላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሁለቱ ተጠርጣሪዎች ላይ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ተጠርጣሪዎቹ ለምን በ48 ሰዓታት ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና የት እንደቆዩ አጣርቶ እንዲቀርብ መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ለማጣራት መሞከሩን ጠቁሞ፣ ነገር ግን በወቅቱ በርካታ ተጠርጣሪዎች ተይዘው ስለነበር ለመለየት አስቸጋሪ እንደነበር የገለጸውን እንዳልተቀበለው ተናግሯል፡፡ የነበረውን ሁኔታ ወደኋላ ሄዶ ለማጣራትም ‹‹ምን ያህል ጠቃሚ ነው?›› የሚለውን ፍርድ ቤቱ መዝኖ፣ ተይዘው የቆዩበትን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ምርመራ እንዲሠራ ትዕዛዝ በመስጠት፣ ከምርመራው ስፋትና ገና በመታየት ላይ ከመሆኑ አንፃር፣ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በአቶ ስብሐት ነጋ የምርመራ መዝገብ የተካተቱትን አባዲ ዘሙ (አምባሳደር)፣ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ፣ ወ/ሮ ሕርይቲ ምሕረተ፣ አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ፣ አቶ ተክለወይኒ አሰፋ፣ አቶ ወልደጊዮርጊስ ደስታና አቶ ገብረ መድኅን ተወልደ ላይ መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው 14 ምርመራ ቀናት ውስጥ የሠራውን የምርመራ ሪፖርት ሰምቷል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ ተጠርጣሪዎቹ መንግሥትንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሙከራ ወንጀል፣ እንዲሁም አገር በመካድ ከሕወሓትና ኦነግ ከተባሉ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ተልዕኮዎች በመፈጸም ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
አቶ ስብሐት፣ አባዲ ዘሙ (አምባሳደር)፣ ወ/ሮ ቅዱሳን፣ ወ/ሮ ሕርይቲና አቶ ቴዎድሮስ፣ በጡረታ ከመንግሥት መሥሪያ ቤት የተሰናበቱ ቢሆንም፣ በአቶ ሥዩም መስፍን የሚመራና ከመደበኛ የመንግሥት አወቃቀር ውጪ ተደራጅተው በሥራ ላይ የነበሩ አመራሮችን ያማክሩና ድጋፍ ይሰጡ እንደነበር ገልጿል፡፡ በአገሪቱ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ብሔርንና እምነትን መሠረት ያደረገ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ፣ በርካታ ንፀኃን ዜጎች እንዲገደሉና ንብረታቸው እንዲወድም ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የትግራይ ልዩ ኃይልና መከላከያ ሠራዊትን የከዱ አባላት፣ በሰሜን ዕዝ ላይ ጦርነት እንዲከፍቱ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባላትን ሲያማክሩ እንደነበር መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ የትግራይ ክልል የመከላከያ ሠራዊት ሊኖረው እንደሚገባ በመግለጽ የተለያዩ ሰነዶችን በማዘጋጀት ለሥራ አስፈጻሚው በመስጠት፣ ወጣቶች ወደ ጦርነት እንዲገቡ የመንቀስቀስና የማነሳሳት ሥራ ሲሠሩ እንደነበር የሚያረጋግጥ የሰነድና የተንቀሳቃሽ ምሥል ማስረጃ መሰብሰቡን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ፣ ንፁኃን ዜጎች በግፍ እንዲገደሉ፣ ንብረት እንዲወድም፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በየክልሉ እንዲመለመሉ በማድረግና ወደ ትግራይ ክልል ሄደው እንዲሠለጥኑ ማድረጋቸውንም መርማሪ ቡድኑ የሚያሳይ ማስረጃ መሰብሰቡን ገልጿል፡፡
ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ሰለሞን (ዶ/ር)፣ አቶ ተክለወይኒ፣ አቶ ወልደ ጊዮርጊስና አቶ ገብረ መድህን ደግሞ ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን፣ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይልና የከዱ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በማደራጀት፣ በሰሜን ዕዝና በፌዴራል ፖሊስ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም፣ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች እንዲዘረፉ ማድረጋቸውንም ጠቁሟል፡፡ በጦርነቱ ከተሸነፉ በኋላም ራሳቸውን ቀይረው ለማምለጥ ሲሞክሩ በመከላከያ ሠራዊቱ መያዛቸውንም አክሏል፡፡
ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን፣ ለጦርነቱ ምሽግ የሚቆፍሩ ማሽኖችን ሲያቀርቡ እንደነበርና መንግሥት ለመጠባበቂያ ያስቀመጠውን ነዳጅ ከዲፖ ውስጥ በማዘረፍ ለጦርነት ዓላማ እንዲውል በተለያዩ ቦታዎች ሲደብቁ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘቱን ተናግሯል፡፡
አቶ ተክለ ወይኒ፣ አቶ ወልደጊዮርጊስና አቶ ገብረ መድኅን የተባሉ ተጠርጣሪዎች፣ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች በመዘዋወር ኅብረተሰቡ ለጦርነቱ የገንዘብና የሎጂስቲክስ ድጋፎችን እንዲያደርጉ ሲንቀሳቀሱና ወጣቶችን እየመለመሉ ወደ ጦርነቱ ሲልኩ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎችን መለየቱን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡
በተጠርጣሪዎቹ ላይ የ15 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ ግንኙነት ሲያደርጉባቸው የነበሩ ስልኮቻቸውን ለምርመራ መላኩን፣ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖዎች ላይ የደረሰ ጉዳት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል በመቋረጡ የደረሰ ጉዳት፣ በወደሙ ኤርፖርቶች የደረሰን ጉዳት ለማወቅ ደብዳቤ መላኩንና ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ የቀሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረውና ማስረጃዎችን የሚያሰባስብ የምርመራ ቡድን በትግራይ ክልል ስለላከ የምርመራ ግኝቱን እየተጠባበቀ መሆኑን ጠቁሞ፣ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድት ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሌላ የምርመራ መዝገብ አቶ ዓባይ ወልዱ፣ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ ረዳዒ በርሄ (ዶ/ር)፣ ሙለታ ይርጋ (ዶ/ር)፣ ኪሮስ ሐጎስ (ዶ/ር)፣ አቶ ዕቁባይ ታፈረ፣ አቶ ጌታቸው ተፈራ፣ አቶ ሐምዶማርያም ተሰማና አቶ ንጋቱ ኃለፎምን የምርመራ ሒደትን ተመልክቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው 14 ቀናት የመራው የምርመራ ውጤት በእነ አቶ ስብሐት ምርመራ ሥራ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ አብርሃም (ዶ/ር) የተጠረጠሩበትን የወንጀል ድርጊት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
አብርሃም (ዶ/ር) ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወርቅና ብር ወደ ደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ እንዲዘዋወር በማድረግ መዝረፋቸውንና ማዘረፋቸውን የሚያስረዱ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ተጠርጣሪው ለግብረ አበሮቻቸው ሲያከፋፍሉ እንደነበር፣ ለጦርነቱ ምሽግ ማስቆፈሪያ ማሽን ሲያስቀርቡ፣ ከነዳጅ ዲፖዎች ነዳጅ ሲያሸሹ እንደነበርና ጦርነቱ ሲጠናቀቅ ራሳቸውን ቀይረው ሲሸሹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስረድቷል፡፡ ቀሪ የምርመራ ሥራዎች እንዳሉት በማስረዳትም የጠየቀው የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድት ጠይቋል፡፡
ለሁሉም ተጠርጣሪዎች አራት ጠበቆች የቆሙላቸው ሲሆን፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ባቀረበው የምርመራ ሪፖርት ላይ መከራከሪያ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ እንዳስረዱትም፣ ደንበኞቻቸው የተጠረጠሩበትን የወንጀል ድርጊት በትክክል ማወቅ አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም የምርመራ ሒደቱና በምርመራው የተገኘው ውጤት በፍርድ ቤቱና በሕጉ ሥርዓት (Procedure) መሠረት መቅረብ ሲገባው የቀረበው ሕግና ፖለቲካ በተቀላቀለበት ሁኔታ ነው፡፡ በመሆኑም ለየትኛው መከራከር እንዳባቸው መለየት አስቸጋሪ ነው፡፡
መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው የምርመራ ሪፖርት ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸውና የሚታወቁ ናቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ እንደማንኛውም ተጠርጣሪ ዜጋ በግለሰብ ደረጃ ስለቀረቡ የወንጀል ድርጊታቸው ተለይቶ መቅረብ አለበት እንጂ፣ ‹‹መንግሥትን ያማክሩ ነበር›› ተብሎ መቅረብ እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡ በዚሁ ሁኔታ ከቀጠለ ማለቂያ የሌለው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ሆኖ እንደሚቀጥልና በሕግ ፊት በእኩልነት የመዳኘትና ፍትሕ የማግኘት መብት እያጡ እንደሚሄዱም አክለዋል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ተጠርጣሪ፣ ከተጠረጠረበት ጉዳይ ጋር መቼ፣ የትና እንዴት እንደሚገናኝ በማሳየት ማቅረብ እንጂ፣ ‹‹ወጣት ይመለምሉ ነበር፤›› ብሎ በጥቅል ማቅረብ ተጠርጣሪዎቹ ፍትሐዊ ዳኝነት እንዳያገኙ እንደሚያደርጋቸውም ጠበቆቹ አስረድተዋል፡፡ ደንበኞቻቸው ወደ ፍርድ ቤት ሲገቡ ፍርድ ቤት ሳይፈቅድ እንዲቀርፁ እየተደረገ በመገናኛ ብዙኃን እንዲለቀቅ ማድረግም መብታቸውን መጣስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ምክር እንደሚሰጡ እንጂ ያደረጉት ነገር ተለይቶ ስላልቀረበ፣ በግምት ሰው እንደሞተና ንብረት እንደወደመ መርማሪ ቡድኑ መግለጹ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
መነሻው የማይታወቅ በስሜታዊነት (Sensetional) የተደረገ፣ ግልጽነት የጎደለውና ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች (ICCPR) ስምምነትን የጣሰ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የመንግሥት ኃላፊዎች ሆነው የሠሩትን እንደ ወንጀል አድርጎ ማቅረብ የሚቻለው በሒደትና በማስረጃ መሆን ሲገባው፣ መርማሪ ቡድኑ እርግጠኛ ሆኖ ‹‹ወንጀል ፈጽመዋል›› እያለ ማቅረቡ ከፍርድ በፊት ንፁህ ሆነው የመገምት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚያሳጣቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አብርሃም (ዶ/ር)ን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ ‹‹የዘረፋና የተዘረፈ መሆኑን አረጋግጠናል፤›› ካለ፣ ‹‹ለምን ፍርድ ቤት እንመጣለን? መዝገቡ ተዘግቶ ዓቃቤ ሕግ ክስ ካለው ይከሰስ፤›› በማለት፣ መርማሪ ቡድኑ በደንበኞቻቸው ላይ ያቀረበውን የምርመራ ሪፖርት ተቃውመዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ራሳቸውን ቀይረው ሊያመልጡ ሲሉ እንደያዛቸው መግለጹን በሚመለከትም ጠበቆቹ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የቀየሩት ልብስና ማንነት የለም፡፡ የኤርትራ መንግሥት ከተማውን በመድፍና በሮኬት እንደሚደብድብ እየገለጸ ባለበት ሁኔታ አንዱ ጋ ሊቀመጡ አይችሉም፡፡ በክልሉ ወደፈለጉበት ቦታ የመንቀሳቀስ መብት አላቸው፡፡ ይኼ ስም ማጥፋት (Character Assassination) ነው፤›› በማለት ሪፖርቱን ተቃውመው ተከራክረዋል፡፡
አብርሃም (ዶ/ር) ፈጽመውታል ተብለው የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት፣ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት ሲካሰሱበት የነበረ መሆኑን ጠቁመው፣ ወርቅ ተዘርፏል ማለት እንደማይቻልና ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአገር ተቋም በመሆኑ በኃይል ካልሆነ በስተቀር በቀላሉ የማይዘረፍ መሆኑን ጠበቆቹ አስረድተዋል፡፡ ደንበኞቻቸው ‹‹በጦርነት ከተሸነፉ በኋላ፤›› በሚል መርማሪ ቡድኑ የገለጸው፣ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ያለበት የፖለቲካ አነጋገር በመሆኑ፣ ወደ ፍርድ ቤት መምጣት ስለሌለበት ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግም አክለዋል፡፡
የውጭውን ጫና ተቋቁሞ የሕጉን ድርሻ ብቻ ማየት ተገቢና የፍርድ ቤቱም ኃላፊነት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥታት የሚጨቃጨቁበትን ፍርድ ቤት ማምጣት አስፈላጊ እንዳልሆነና ሕጉም እንደማይፈቅድ ተናግረዋል፡፡
በመከላከያ ሠራዊት ላይ ወንጀል ከተፈጸመ፣ በወንጀል ሕጉ ድንጋጌ መሠረት ባደረጉት ልክ መጠየቅ እንዳለባቸው፣ ይህ ሲሆን ደግሞ በገለልተኝነት የመዳኘት መብታቸው እየተረጋገጠ እንደሚመጣ አክለዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ጠበቆቹ ላነሱት መከራከሪያ ሐሳብ በሰጠው ምላሽ እንዳብራራው፣ ጠበቆች ፖለቲካዊ ይዘት ከሕጉ መለየት እንዳለበት ያቀረቡትን ሐሳብ ይቀበላል፡፡ ሻዕቢያ በክልሉ ይኑር ወይም አይኑር መርማሪ ቡድኑ ያለው ነገር ስለሌለ ጠበቆች ማንሳት የለባቸውም፡፡
የምርመራ ውጤቱን በግልና በቡድን ለይቶ ማቅረቡን ተናግሯል፡፡ አለባበሳቸውንና ማንነታቸውን ቀይረው ያለው ያለ ምክንያት ሳይሆን፣ ስማቸውን ቀይረውና መታወቂያ አሠርተው ይዘው በመገኘታቸውና ማስረጃ በማግኘቱ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ዓባይ ወልዱ (አምባሳደር) ስማቸውን ቀይረው፣ ጥምጥም ጠምጥመውና የቄስ ልብስ ለብሰው መታወቂያ በማሠራት ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን ለአብነት ጠቅሷል፡፡ ራሳቸው የፈረሙበት ማስረጃ በመሆኑ ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡ አግባብ መሆኑንም አክሏል፡፡ ገንዘብን በሚመለከትም በመኪና ተጭኖና ጫካ ውስጥ ተወስዶ ለቤተሰብ ሲከፋፈል የሚያሳይ ማስረጃ መሰብሰቡንም ጠቁሟል፡፡ የእንዳንዳቸው የወንጀል ድርጊትን በሚመለከትም በግልና በቡድን መለየቱን ጠቁሞ፣ የሰለሞን (ዶ/ር) እና የአብርሃም (ዶ/ር)ን ለአብነት ጠቁሟል፡፡
በሥዩም መስፍን (አምባሳደር) የሚመሩ ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ በቡድን ሲያስፈጽሙ እንደነበር፣ ወጣቶችን ከቤንሻንጉል ጉምዝና ከኦሮሚያ ክልሎች መልምለው መቀሌ ላይ ሲያሠለጥኑ እንደነበር በመጠቆም፣ ይህንን ለፍርድ ቤቱ መግለጹ ፖለቲካዊ ይዘት እንደሌለው ተናግሯል፡፡ በአገር ደረጃ ሲፈጽሙት የነበረና ከአካባቢያቸው ውጪ ራሳቸውን ቀይረው ሲንቀሳቀሱ ከመገኘታቸው አንፃር፣ ራሳቸውን አይደብቁም ማለት ስለማይቻል የዋስትና ጥያቄያቸውን እንደሚቃወም ገልጾ የጠየቀው 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ፣ ምርመራው ጅምር መሆኑንና ውስብሰብ መሆኑን ፖሊስ የገለጸውን ከግምት ውስጥ ማስገባቱን ተናግሮ፣ የዋስትና ጥያቄውን በማለፍ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለየካቲት 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡