በተጠረጠረበት ሐሰተኛ መረጃዎችን ማሠራጨት ወንጀል ላለፉት 60 ቀናት (እስከ ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ) በእስር ላይ የነበረው የአውራምባ ታይምስ ማኔጂንግ ኤዲተር በ50 ሺሕ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈታ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡
ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ለስድስተኛ ጊዜ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ ነበር፡፡
ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት ፍርድ ቤቱ ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ‹‹ለመጨረሻ ጊዜ›› በማለት የምርመራ ጊዜ ከመፍቀዱ አንፃር፣ የክስ መመሥረቻ ጊዜ እንደሚጠየቅበት ወይም የዋስትና መብት እንደሚከበርለት የተጠበቀ ቢሆንም፣ ከመርማሪ ቡድኑ ግን ተጨማሪ ጊዜ ተጠይቋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ ምርመራውን ሊያጠናቅቅ እንዳልቻለ ገልጾ፣ ተጠርጣሪው በሚሠራበት ድርጅት ውስጥ ያለውን የሥራ ድርሻ የሚገልጽ ማስረጃ እንደሚያቀርብና በስልኩ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር ያደርግ የነበረውን ግንኙነት ለማወቅ፣ ስልኩን ለቴክኒክ ምርምራ ሰጥቶ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በሰዎች ምስርክነት እንዳረጋገጠውም ከሕወሓት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በመገናኘት ሐሰተኛ መረጃ ሲያሠራጭ እንደነበር ስለታወቀ፣ በትግራይ ክልል ለምርመራ የተላከው ቡድንን ውጤት እየተጠባበቀ መሆኑን በመግለጽ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
የተጠርጣሪው ጠበቃ ባቀረቡት መከራከሪያ ሐሳብ እንደገለጹት፣ ደንበኛቸው ከታሰረ 60 ቀናት ሆኖታል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ እየተባለ ሲቀጠር ይኼ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
ከመሥሪያ ቤቱ ስለተጠየቀው የሥራ ድርሻ መግለጫ ደብዳቤም በችሎት ‹‹የአውራ አምባ ታይምስ ማኔጂንግ ኤዲተር ነው›› ብለው መናገራቸውን በማስታወስ፣ ይህ ባይሆን እንኳ ዋስትና እንደማያስከለክለው ገልጸዋል፡፡ ሐሰተኛ መረጃ አሠራጭቷል ተብሎ መጠርጥሩም ቢሆን፣ በሕጉ መሠረት ክርክር አድርጎ ቢፈረድበት እንኳ ከሦስት ዓመታት በላይ ስለማያስቀጣው ዋስትና ሊያስከለክል እንደማይገባ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የቴክኒክ ምርመራ መጠበቅም ከዋስትና ጋር እንደማይገናኝና እንደ አዲስ ‹‹ከሕወሓት ሰዎች ጋር ይገናኛል›› ብሎ ማንሳት የተጠርጣሪውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለሚያመጣ ዋስትናው እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱም ለጋዜጠኛ ዳዊት ደመወዙ ስንት እንደሆነ ጠይቆ ‹‹አሥር ሺሕ ብር›› እንደነበር ከገለጸለት በኋላ በ50 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡