የዘንድሮ የእግር ኳስ ውድድሮች የተጀመሩት አስቀድሞ ከኮቪድ ፕሮቶኮል ጋር በተገናኘ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ሰነድ በማዘጋጀትና በሰነዱ ላይ ፕሮቶኮሉ በሚፈቅደው መሠረት አስፈላጊው ምክክርና መግባባት ላይ በመድረስ ነው፡፡ ይሁንና የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በየደረጃው በሚደረጉ ውድድሮች ምርመራዎች ስታዲየም በር ላይ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በየደረጃው የሚያወዳድራቸውን ጨምሮ የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች እየተካሄዱ ነው፡፡ በዋናነት ባለቤት ተፈጥሮለት በአዲስ አበባ፣ በጅማ እና በባህር ዳር ስታዲየሞች እንደሚካሄድ ቀደም ብሎ ፕሮግራም የተያዘለትና ከታኅሣሥ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሳምንት ሁለት ጊዜ እየተካሄደ ያለው የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመርያው ዙር የጨዋታ መርሐ ግብር ሊጠናቀቅ ተቃርቧል፡፡ ከፍተኛ ሊጉም ሆነ ብሔራዊ ሊግ በተመሳሳይ በተወሰኑ ከተሞች ላይ ጨዋታው ቀጥሎ ይገኛል፡፡
ጨዋታዎቹን ብዙኃኑ ተመልካች የሚከታተላቸው አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ከሁሉም የውድድር ሥፍራዎች የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገው የኮቪድ-19 ምርመራ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እንዲያውም ውድድሮች ሲጀመሩ የነበረው ምርመራ አሁን ላይ ለይስሙላ ካልሆነ እንደ ቀልድ እየታየ ስለመምጣቱ የሚናገሩ አልጠፉም፡፡
ኮቪድ-19ን በመከላከሉ ረገድ ያለው ቸልተኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ውድድሩ እንደ ቀድሞ በተዟዙሮ ባለመሆኑ ቡድኖች ሜዳ ላይ የሚያሳዩት የአልሸነፍ ባይነት ፉክክር ማራኪና ተስፋ ሰጪ መሆኑ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡
እንደ ሙያተኞቹ ፉክክሩ ሊደምቅ የቻለው ቀደም ሲል በነበረው የተዟዙሮ የጨዋታ ሥርዓት (ፎርማት) ቡድኖች በጉዞ የሚያባክኑት ጉልበት አሁን ላይ ውድድሩ በተወሰኑ ከተሞች ላይ እንዲሆን መደረጉ ሙሉ ጉልበታቸውን ለጨዋታው የሚያውሉበት አጋጣሚ በመፈጠሩ ነው፡፡ የኮቪድ ጉዳይን በተመለከተ ወረርሽኙን ታሳቢ ያደረገ አለመሆኑ እንደሚያስፈራቸው ግን አልሸሸጉም፡፡
የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ በሁሉም ደረጃ የሚካሄዱ ውድድሮች የኮቪድ-19 ምርመራው የስታዲየሞች ተመልካች አልባነት ትርጉም አልባ እንዲሆን የሚያደርግ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ የምርመራውን ሒደት አስመልክቶ እንደ ሙያተኞች አስተያየት ከሆነ፣ ‹‹ብዙዎቹ ቡድኖች ለተጨዋቾቻቸው ምርመራ የሚያደርጉት ስታዲየም በር ላይ ነው፡፡ አስገራሚው ነገር ደግሞ የምርመራው ውጤት የሚነገረውም እዚያው ስታዲየም በር ላይ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በወረርሽኙ የተጠቃ ተጨዋች ካለ ስታዲየም እስኪደርስ ድረስ ከቡድኑ አባላት ጋር በአንድ አውቶቡስ መጓዙ ነው፤›› በማለት ክፍተቱን ይጠቁማሉ፡፡
በሌላ በኩል የምርመራው ሒደት ያን ያህል ክፍተት ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ምርመራው ስታዲየም በር በመሆኑና ውጤቱም እዚያው ስታዲየም በር ስለሚነገር፣ አሠልጣኙ ቀዳሚ አድርጎ ከሚመርጣቸው ተጨዋቾች ውስጥ አንዱ ላለመሆኑ ምንም ዓይነት ዋስትና የሌለው ስለመሆኑ ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡
ችግሩ በየደረጃው በመከናወን ላይ በሚገኙት ውድድሮች የሚስተዋል የአደባባይ ምስጢር እንደሆነ የሚናገሩት ሙያተኞቹ፣ የሚመለከተው አካል ይህን ጉዳይ አንድ ሊለው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ከኮቪድ-19 ምርመራ ጋር በተገናኘ አትሌቲክሱን ጨምሮ በሌሎቹም ስፖርቶች ተመሳሳይ ችግሮች የሚስተዋሉ ስለመሆኑ ከሰሞኑ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ያደረገውን የሩጫ ውድድር መመልከቱ በቂ ማሳያ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ዙር ጨዋታ የሚጠናቀቅበትና የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት የሚጀመርበትን ቀን በሚመለከት ሊግ ካምፓኒው ለክለቦች አሳውቋል፡፡ በዚሁ መሠረት የአንደኛ ዙር ውድድር የሚጠናቀቀው የካቲት 18 ቀን ሲሆን፣ የሁለተኛው ዙር የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት የሚከፈተው ደግሞ በማግሥቱ ከየካቲት 19 ጀምሮ እስከ መጋቢት 18 ቀን ድረስ ለአንድ ወር እንደሚቆይ ሊግ ካምፓኒው አስታወቋል፡፡