Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየሊግ ካምፓኒው የኃላፊነት ወሰንና ቅጣት የተላለፈባቸው ረዳት የእግር ኳስ ዳኞች

የሊግ ካምፓኒው የኃላፊነት ወሰንና ቅጣት የተላለፈባቸው ረዳት የእግር ኳስ ዳኞች

ቀን:

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በሦስት ከተሞች ተወስኖ እየተከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ከዳኝነት ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲቀርቡበት ይደመጣል፡፡ አዲስ አበባ ላይ በተከናወኑ ውድድሮች ሲታዩ የነበሩ የዳኝነት ችግሮች አሁን ጨዋታው እየተከናወነ በሚገኝበት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ ሁለት ረዳት ዳኞች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ይሁንና ውሳኔውን ተከትሎ የአወዳዳሪው አካል የኃላፊነት ‹‹ወሰን›› እስከ ምን ድረስ ነው? የሚለው ደግሞ በሌላ በኩል ማነጋገሩ አልቀረም፡፡

ውሳኔውን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ‹‹የፕሪሚየር ሊጉ አወዳዳሪ አካል (ሊግ ካምፓኒው) ውድድሩን በባለቤትነት መምራት ካልሆነ፣ የዳኞችን ጉዳይ በሚመለከት የሊግ ካምፓኒው ኃላፊነት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመርያ መሠረት ዳኞች ጥፋት ፈጽመዋል ተብሎ የሚታመን ከሆነ አሠራሩ የዳኞችና የዲሲፕሊን ኮሚቴዎች ውሳኔዎች መቅረብ የነበረባቸው ለሊግ ካምፓኒው ሳይሆን፣ ለፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ነው፤›› በሚል ቀደም ሲል፣ በሊግ ካምፒኒው አማካይነት በሁለቱ ረዳት ዳኞቹ ላይ የተላለፈው ውሳኔ እንደገና ደንብና መመርያውን የተከተለ እንዲሆን ጠይቋል፡፡ ሊግ ካምፓኒውም ቅሬታውን በመቀበል ውሳኔው የኃላፊነትና የአሠራር ቅደም ተከተሉን ተከትሎ ውሳኔው እንዲፀና ስለማድረጉ ይናገራል፡፡

የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ቅሬታ አስመልክቶ የሊግ ካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ዳኜ እንደሚያስረዱት ከሆነ፣ ‹‹ፌዴሬሽኑ ፌዴራል ረዳት ዳኛ አሸብር ታፈሰና ፌዴራል ረዳት ዳኛ ባደግ ገብሬ በተላለፉት የሕግ ጥሰት የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት እያንዳንዳቸው የስድስት ወራት የዕገዳ ቅጣት እንዲተላለፍባቸው ከተወሰነው ውሳኔ ጋር ተያይዞ ቅሬታ የለውም፡፡ ስህተቱ ሊፈጸም የቻለው ውድድሩ ኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ችግር እንደ ወትሮው በተዟዙሮ ሳይሆን በተመረጡ ከተሞች መሆኑ፣ ይህንኑ ተከትሎ የዳኞች ኮሚቴና የዲሲፕሊን ኮሚቴ ከሊግ ካምፓኒው ጋር አብረው እንደሚሠሩ በደብዳቤ በጠየቁት መሠረት ውድድሩን አብረውን እንዲመሩ በመደረጉ የተፈጠረ ክፍተት  ነው፤›› ብለው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የማስተካከያ ጥቆማ ተገቢነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ክፍሌ ሒደቱን ሲያስረዱ፣ ጥር 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በተከናወነው የባህር ዳርና የሰበታ ከተማ ቡድኖች ያደረጉትን ጨዋታ በረዳት ዳኝነት ጨዋታውን የመሩት ዳኞችን በሚመለከት፣ የጨዋታው ታዛቢ ዳኛ ዋና ኢንስፔክተር ወርቁ ዘውዴ ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ ሁለቱ ረዳት ዳኞች ከጨዋታ ውጪ በሆነ አቋቋም የሚገኝ ተጨዋች ኳስ ከጓደኛው አግኝቶ ግብ ሲያስቆጥር ትክክል ነው ብለው እንዲፀድቅ አድርገዋል በሚል የወሰኑት ውሳኔ ለሊግ ካምፓኒው ጽሕፈት ቤት አቅርበው ጽሕፈት ቤቱም ውሳኔውን አንዲያፀድቅ ማድረጉን  ያስረዳሉ፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በቀረበለት ውሳኔ መሠረት ቅጣት የተላለፈባቸው ሁለቱ የፌዴራል ረዳት ዳኞች ውሳኔው የፀናባቸው መሆኑን ለወሰነው የዳኞች ኮሚቴና ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በደብዳቤ እንዲያውቁት ማድረጉንም ኃላፊው አልሸሸጉም፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ. ም በጻፈው ደብዳቤ፣ ሁለቱ ፌዴራል ረዳት ዳኞች በውድድር አመራሮችና ኢንስትራክተሮች መመርያ መሠረት ተግባራዊ ባለማድረጋቸው የተላለፈባቸው ዕገዳ፣ በውድድርና ኢንስትራክተሮች መመርያ አንቀጽ 31 ቁጥር 16 መሠረት ውድድሩን ከመሩበት ቀን ጀምሮ እያንዳንዳቸው ስድስት ወራት ከጨዋታ አመራርነት የታገዱ መሆኑን አሳውቋል፡፡

በጅማው የባህር ዳርና የሰበታ ከተማ ጨዋታ ላይ ከታየው የዳኝነት ስህተት ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም ላይም በግልጽ ሲታይ የነበረ መሆኑን የሚናገሩ አንዳንድ ሙያተኞች፣ ‹‹ያለፈው አልፏል፡፡ ለወደፊቱ ግን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ይሁን እንዲህ ዓይነቱ የዳኝነት ስህተት ሲታይ ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ያለበት የፍትሕ አካል ከአድልኦና ከይሉኝታ የፀዳ ውሳኔ መወሰን ይኖርበታል፤›› ይላሉ፡፡

ፕሪሚየር ሊጉ አሁን ላይ ምንም እንኳ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተመልካች ባይታደምበትም በሱፐር ስፖርት አማካይነት ወደ ኅብረተሰቡ እየደረሰ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ከኃላፊነት ወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ አለመግባባቶች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑና የሊግ ካምፓኒው፣ እንዲሁም የፍትሕ አካላት በተለይ ከመመርያና ደንብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚመለከት ‹‹ማን ለማን››  የሚለው ጥርት ባለ መልኩ መድረክ ተፈጥሮ ምክክር ተደርጎበት ግልጽ ሊደረግበት እንደሚገባ የሚመክሩ አልጠፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...