የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለዘመናዊ የግብይት ሥርዓት በፈር ቀዳጅነት የሚጠቀስ ተቋም ነው፡፡ የአገሪቱን ዋና ዋና የወጪ ንግድ ምርቶች የሆኑትን ቡና፣ ሰሊጥና የመሳሰሉ ምርቶችን በማዕከል በማገበያየት ይታወቃል፡፡ በየጊዜው የሚያገበያያቸውን የምርት ዓይነቶችም እየጨመረ ዕለታዊ የግብይት መጠኑን እያሰፋ ይገኛል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት እንኳን ከ19.8 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ከ320 ሺሕ ቶን በላይ ምርቶች ማገበያየቱ የተቋሙን አቋም ያመላክታል፡፡ በአብዛኛው በወጪ ንግድ ምርቶች ላይ ያተኮረው ግብይት ወደፊት በአገር ውስጥ ገበያ የሚፈለጉ ምርቶችን በማገበያየትም፣ ዋጋን የማረጋጋት ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራም ምርት ገበያው ማንኛውንም ዓይነት ምርት ለማገበያየት የሚችል መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እንደ ፊቸር ገበያ ያሉ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችሉ ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን፣ ከግብርና ምርት በተጨማሪ ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶችን በምርት ገበያው በኩል እንዲገበያዩ ዕቅድ ያለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከወቅታዊ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አንፃር የምርት ገበያው አፈጻጸም ከዕቅዱ ጋር የተጣጣመ መሆኑንም በማመልከት፣ በትግራይ ክልል ሕግን ከማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ በተለይ የሰሊጥ ምርት አቅርቦትና አፈጻጸም፣ እንዲሁም በአጠቃላይ የስድስት ወራት የተቋሙትን ክንውን በተመለከተ ዳዊት ታዬ የምርት ገበያውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራን አነጋግሯል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚያገበያያቸውን የምርት ዓይነቶች እየጨመሩ ነው፡፡ በብዛት እየተሠራ ያለው ግን ለወጪ ንግድ የሚቀርቡ ምርቶችን በማገበያየት ነው፡፡ የአገር ውስጥ ገበያን ከማረጋጋት አንፃር የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሚና አለው ማለት ይቻላል? ለዚህ የታሰበ ነገር አለ?
አቶ ወንድማገኝ፡- አሁን እየተሠራ ሥራ አለ፡፡ ለምሳሌ በቆሎ ወደ ግብይት ሥርዓቱ ለማስገባት አንድ አሠራር አምጥተናል፡፡ ይኸም የመጋዘን ደረሰኝ አገልግሎት ነው፡፡ የዛሬ ሦስትና አራት ዓመት በቆሎ ከተመረተ በኋላ የግብይት ዋጋው ወደቀ፡፡ የሚሸጠው ለዓለም ምግብ ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ አምራቹ አመረተ፣ ገበያ የለውም ወይም ገበያው ተመጣጣኝ ዋጋ አይሰጥም፡፡ ይህ ችግር ነበር፡፡ ስንዴ ከውጭ የሚገባውና እኛ አገር የሚሸጠው ጥሩ አልነበረም፡፡
ሪፖርተር፡- ጥሩ አልነበረም ሲባል?
አቶ ወንድማገኝ፡- ጥሩ አልነበረም፡፡ ማለት አምራቹ ጥሩ ዋጋ የማያገኝበት ሁኔታ ነበር፡፡ ባሌና አርሲ የዛሬ ሦስትና አራት ዓመት ብዙ ተመርቶ የሆነው ይህ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አሉ፡፡ በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቆላ አካባቢ ስንዴ እንዲዘራ እየተደረገ ነው፡፡ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ይህ እያደገና ምርታማነት እየጨመረ ሲሄድ ዋጋ ሌላ ጉዳይ ሆኖ ሲቀርብ፣ ስለዚህ ያንን ለማረጋጋት ነገሮችን ማየት ይፈልጋል፡፡ ይህንን ከሁለት አንፃር ማየት እንችላለን፡፡ አንደኛው በተለይ አምራቹ ተጠቃሚ ሆኖ መቀጠልና አዋጭ ሆኖ መቀጠል ካለበት ይህ መታየት አለበት፡፡ እኛ አገር የሚታወቀው ምርት ይመረታል፣ ምርት በሚደርስበት ጊዜ ዋጋ ይወድቃል፡፡ አቅርቦቱ ትልቅ ሲሆን ዋጋ ይወርዳል፡፡ ከዚያ ትንሽ ከቆየ በኋላ በዚህ መካከል ላይ ያሉ ተዋንያን ምርቱን ይገዙትና ያከማቹታል፡፡ ወይ አርሶ አደሩ አልተጠቀመ፣ ወይ ሸማቹ አልተጠቀመ፣ በዚህ መካከል ያሉት ተዋንያን ናቸው የሚጠቀሙት፡፡ አሁን የመጋዘን ደረሰኝ ፋይናንሲንግን ለመተግበር የጀመርነው ሥራ አለ፡፡ ይህም አምራቹ ምርቱን ካመረተ በኋላ መጋዘን ያስገባል፣ አስይዞ ይበደራል፡፡ አስይዞ ተበድሮ የገበያውን ሁኔታ እያየ የሚገበያይበት ይሆናል፡፡ ዓመቱን በሙሉ በተወሰነ ዋጋ ምርቱን መሸጥ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህ ለሸማቹ ጥቅም አለው፡፡ ለሻጩም በወደቀ ዋጋ ሸጦ እንዳይጎዳ ስለሚያደርግ፣ እንዲህ ያለውን ነገር ለመሥራት አስበናል፡፡ የዋጋ ሥርዓቱን የገበያውን የፍላጎትና የአቅርቦት ስለሆነ የሚመራው በዚያ ሥርዓት ለማስኬድ አስበናል፡፡ በተለይ ምርቶቹ በወደፊት ኮንትራት መሠረት እንዲገበያዩ የሚያስችል ነው፡፡ ይህ የወደፊት ግብይት ከዛሬ ሦስት ወር በኋላ ነው ብለህ ዛሬ ግብይት መፈጸም እንደ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ግብይት ለመጀመር አሁን ጥናት እያደረግን ነው፣ ተግባራዊም እናደርጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለው አሠራር ጠቀሜታው ምንድነው? ዋናው ጥያቄዬ እንዲህ ያለው አሠራር ገበያውን ያረጋጋል የሚል ነው?
አቶ ወንድማገኝ፡- የ‹‹ፊቸር ማርኬት›› ገበያ ለመጀመር የተለያዩ ነገሮችን እያየን ነው፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር የሚያስገኘው ብዙ ጥቅም አለ፡፡ ገና ሳታመርት የምትሸጥበትን ዋጋ ታውቃለህ፡፡ የዛሬ ሦስት ወር በዚህ ዋጋ ይህንን አቀርብልሃለሁ ትላለህ፡፡ ገበያውም የሚፈልገው ስለሆነ ‹‹ፊቸር››ም የሚያስቀምጠውና የሚታወቅ ዋጋ አለው፡፡ ስለዚህ ይኼ መረጋጋትን ያመጣል፡፡ መቼ እንደሚመረት ይታወቃል፡፡ መቼ ገበያ እንደሚያቀርብ ያውቃል፡፡ እዚህ ላይ ያሉት አቅራቢዎች ያንን የማረጋጋት ሥራ በቀጣይነት ያስኬዳሉ፡፡ አሁን ለምሳሌ የምንሸጠው ቡና እኮ ዛሬ ላይ ጥር ወር ላይ ሆነን፣ ለመጋቢት የሚቀርብ ተብሎ ነው ዛሬ የሚገበየው፡፡ ስለዚህ ሚያዝያ ላይ ምን ያህል አቅርቦት ገበያ ውስጥ እንዳለ ይታወቃል ማለት ነው፡፡ የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር፣ እሱም ደግሞ ከሰብል ኢንሹራንስ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር ለሚችል ነገር ካለ ኢንሹራንስ ሊገባ ይችላል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለው አሠራር አርሶ አደሩም እንዳይጎዳ ያደርጋል፡፡ አምራቹም አይጎዳም፡፡ የተረጋጋ ዋጋ ይኖራል፡፡ ስለዚህ አንድ ጊዜ የሆነ ነገር ጠፋ ተብሎ ዋጋው ሰማይ የሚወጣ፣ እንደገና ደግሞ ምርቱ ደረሰ ሲባል ገበያ የሚያጣበት መሆን የለበትም፡፡ የዛሬ 15 ዓመት አካባቢ ሰካካዋ ግሎባል በመጣበት ጊዜ የበቆሎ ማስፈጫ ዋጋ ከማምረቻው ዋጋ በለጠ፡፡ ይህ መረጋጋት አይሆንም፡፡ አሁን ግን በፊቸር ገበያ ከሠራን ይደረጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ዋጋም ይታወቃል፡፡ በጣም የተትረፈረፈ ምርት ካለ ደግሞ ኢንዱስትሪዎች እሴት ጨምረው ፕሮሰስ አድርገው ኤክስፖርት ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡
እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ማንኛውንም ግብርና ለማሳደግና መካናይዝድ ለማድረግ የምንሠራው ሥራ ከግብይት ሥርዓቱ ጋር ካልተሳሰረ ዘላቂነት አይኖረውም፡፡ ውጣ ውረድ ይኖረዋል፡፡ በመርህ ገበያ መር ግብርና ነው ፖሊሲያችን፡፡ ግን የግብይት ሥርዓት መፈጠር አለበት፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ምርቶችን እንይ፡፡ ወተትን እንውሰድ፣ ወተት ይመረትና ይህንን የወተት ግብይት የምናስኬድበት ሥርዓት ስለሌለን የሆነ ጊዜ ላይ ብዙ ይመረትና ገበያ ያጣል፡፡ በተለይ ሰሜን ሸዋ ሰላሌ አካባቢ በፆም ጊዜ ወተት ይመረትና የሚገዛው የለም፡፡ ይህ ይታወቃል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወተት የለም፡፡ አትክልትና ፍራፍሬንም ብታይ የግብይት ሥርዓት ስለሌለው መቼ ይቀርባል? ማን ይገዛል? እንዴት ይረጋጋል? የሚለው አይታወቅም፡፡ ለሌላው አገር ኮሞዲቴ ኤክስቼንጅ (ምርት ገበያ) የማይሸጥ ነገር የለም፡፡ ሁሉ ነገር ይሸጣል፡፡ ምክንያቱም ለአምራቹ አስተማማኝ የሆነ ገበያ መፈጠር አለበት፡፡ አስተማማኝ የሆነ ሲስተም መፈጠር አለበት፡፡ እኛ ግን ከመቂና ከባቱ ምርት ለመግዛት እዚያ ያለው አምኖ ከላከ በኋላ ደላላ በመሀል ይበላዋል፡፡ ስለዚህ የፊቸር ገበያ መፈጠር አስተማማኝ ምርት እንዲያመርት ያግዛል፡፡ ይህን ያህል ሔክታር ሽንኩርትና ቲማቲም አመረትኩ ካለ እሱን የሚገዛው ሥርዓት ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ መጋዘን ላይ ገብቶ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ውጭ ያለውንም ግብይት እያሰብን ነው ያለነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ላይ የምናስበው ነገር እኛ ብቻ ሳንሆን፣ ሦስት አራት ተዋንያን ኖረን ይህንን ሥራ መሥራት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ ማለት ነው? እንዴት?
አቶ ወንድማገኝ፡- በምሳሌ ልግለጽልህ፣ ጥጥ ላይ እያጠናን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ልዩ የሚያደርገው ሁሉንም አገልግሎት ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ እኛ ነን የምንሰጠው፡፡ የመጋዘን አገልግሎት ደረጃ የማውጣት ሥራ እንሠራለን፡፡ ሌላው ዓለም ግን የጥራት ሰርተፊኬሽኑን የሚሠራው ሌላ አካል ነው፡፡ ምርት ትሰጣለህ ደረጃ ያወጣል፡፡ በዚያው ይሄዳል፡፡ እኛ ግን ይህንን አጣምረን እንሠራለን፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የመጋዘን አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ሌላው አገር ይህንን የመጋዘን አገልግሎት የሚሰጥ ሌላ አካል ነው፡፡ ከባንኮች ጋር ክፍያዎች የማያስተላልፉና የመቀነሱ ሥራም የምርት ገበያው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ እናገበያያለን፡፡ የገበያ መረጃም እንሰጣለን፡፡ ይህ ማለት እኛ አምስት አገልግሎቶችን ነው አንድ ላይ የምንሰጠው፡፡ ስለዚህ ለምሳሌ ጥጥ ላይ እንሠራለን ብለን ባሰብነው ሥራ፣ አንደኛ የምርት ማቆያ መጋዘኑን ሌላ አካል ሊሠራው ይችላል፡፡ ምርቱን ሰብስቦ መጋዘን ያደርጋል፡፡ እኛ መጋዘን መገንባት የለብንም፡፡ ይህንን ሥራ የመንግሥትም የግልም ድርጅት ሊሠራው ይችላል፡፡ የመጋዘን አገልግሎቱን ብቻ አንድ አካል እንዲሠራው እያሰብን ነው፡፡ ደረጃ ለማውጣቱ ደግሞ ኢንስቲትዩት አለ፡፡ ዘመናዊ ላብራቶሪ ያለው ነው፡፡ እነሱ ደግሞ የላብራቶሪውን ሥራ ቢሠሩ እኛ ግብይቱን እንሠራለን፡፡ ስለዚህ ሦስት አካላት ሆነን ይህንን ሥራ ልንሠራ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ለግብይት ሁልጊዜ ለገበያ ከምንሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የገበያ መረጃ መስጠት ነው፡፡ ገበያው እንዲህ እየሆነ ነው ተብሎ ሲታወቅ ነው ምን ላምርት? መቼ ላምርት? የሚለው የሚመጣውና እነዚህን ነገሮች ከተለያዩ አካላት ጋር በማቀናጀት ሥራዎችን እንሠራለን ማለት ነው፡፡ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋርም እየተነጋገርን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በምን ጉዳይ? ወርቅን ወደ ገበያው ለማምጣት?
አቶ ወንድማገኝ፡- ወርቅ ብቻ አይደለም፡፡ ማንኛውንም ዓይነት የማዕድን ምርት ለማገበያየት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከወቅታዊ የሥራ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ በዓለም ደረጃ ግብይት ተቀዛቅዟል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ኮቪድ-19 ያሉ ችግሮች ቢኖሩም ኢኮኖሚው እያደገ ነው ይባላል፡፡ የለም እየተቀዛቀዘ ነው የሚሉም መረጃዎች ይሰማሉ፡፡ አሁን ያለው የግብይት ሒደትና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የተዘበራረቀ ነውና ከእናንተ የግብይት አፈጻጸም አንፃር የግብይት ሒደቱ እንዴት ይታያል? ምን አቅዳችሁ ምን አገኛችሁ?
አቶ ወንድማገኝ፡- እንደሚታወቀው እኛ የግብርና ምርቶችን ነው የምናገበያየው፡፡ የምናገበያያቸውን ምርቶች ግብይት ስንመለከት በግማሽ በጀት ዓመቱ ካስቀመጥነው ዕቅድ አንፃር 99 በመቶ ነው ያሳካነው፡፡ በ2013 ግማሽ በጀት ዓመት 323 ሺሕ ቶን ምርት ለማገበያየት አቅደን 320 ሺሕ ቶን አገበያይተናል፡፡ ይህም 99 በመቶ ማለት ስለሆነ ከዕቅድ አንፃር ጥሩ ሊባል የሚችል ነው፡፡ እንግዲህ ከሞላ ጎደል ኮቪድ-19ም ሆነ ሌሎች ተግዳሮቶቹም ቢኖሩም፣ መሠረታዊ የግብርና ምርቶችን ነውና የምናገበያየው ከዕቅድ አንፃር ያመጣብን ተፅዕኖ አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ሰው ቡና መጠጣቱን አላቆመም፡፡ ምግብ መብላቱን አላቆመም፡፡ በተለይ የእኛ የግብይት መዳረሻዎች ላይ አጋጣሚ ሆኖ በአንዳንድ ምርቶቻችን ላይ በተነፃፃሪነት የተሻለ ዋጋ ነበር፡፡ በተለይ በሰሊጥ የገበያው ሁኔታ ጥሩ ነበር፡፡ ፍላጎትም ነበር፡፡ ዋጋው ጥሩ ስለነበር፡፡ ምርቱ ወደ ገበያ ቀርቧል፡፡ የእኛ አንዳንድ ምርቶች በተለይ ማሾ የሚባለው ምርት ኦርጋኒክ (ተፈጥሯዊ) ስለሆነ ገበያው ውስጥ በጣም ይፈለጋል፡፡ በኢንዶኔዥያና በሌሎች የእስያ ገበያዎች በጣም ስለሚፈለግ ጥሩ ገበያ ነበረው፡፡ ስለዚህ ከኮሮና ጋር በተያያዘ የምርት አቅርቦቱ እንደፈራነው አልነበረም፡፡ ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ምርቱ ተመርቶ እየተሰባሰበ በነበረበት ወቅት ላይ ስለነበር፣ ይህንን ያህል ጉዳት አልነበረውም፡፡ ይጎዳሉ ተብሎ ይፈራ የነበረው ምርቶች ነበሩ፡፡ ግን እንደተፈራው አይደለም፡፡ ከዕቅዳችን አንፃር ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በዚህ ስድስት ወራት ውስጥ ግን እኛ ዘንድ የሚገበያየው የቡና መጠን በትንሹ ቀንሷል፡፡
ሪፖርተር፡- በእናንተ በኩል የቡና ግብይት ለምን ቀነሰ?
አቶ ወንድማገኝ፡- በተወሰነ ደረጃ ሊገለጽ የሚችለው ከአማራጭ ግብይት ጋር በተያያዘ የተፈጠረ መሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ በስድስት ወራት ውስጥ 105 ሺሕ ቶን ቡና ነው የተገበያየው፡፡ በአማራጭ ግብይት ደግሞ 28 ሺሕ ቶን ነው የተገበያየው፡፡ ይህንን አንድ ላይ ብንደምር 133 ሺሕ ቶን ነው የሚሆነው፡፡ የእኛ ዕቅድ 136 ሺሕ ቶን ለማገበያየት ነበር፡፡ ስለዚህ በተነፃፃሪ በአማራጭ ግብይት የተገበያየው ስለጨመረ የተፈጠረ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- አማራጭ ገበያ የምንለው የቱን ነው?
አቶ ወንድማገኝ፡- ከምርት ገበያ ውጪ ያሉ አንደኛው ማኅበራት በቀጥታ ኤክስፖርት ማድረግ የሚችሉ ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ በትግራይ ክልል ሕግ ከማስከበር ዘመቻው ጋር ተያይዞ በሰሊጥ ግብይት ላይ ተፅዕኖ ነበር ይባላል፡፡ በእርግጥ በአካባቢው የነበረው አለመረጋጋት በቂ የሆነ የሰሊጥ ምርት ወደ ገበያ እንዳይመጣ አድርጓል? አጠቃላይ የሰሊጥ ግብይት ሒደቱ ምን ይመስላል?
አቶ ወንድማገኝ፡- ሰሊጥ የምንቀበልባቸው ቅርንጫፎች ብዙ ናቸው፡፡ ቡና ከምንቀበልባቸው ውጪ 12 ቅርንጫፎች አሉን፡፡ ትግራይ ውስጥ ያሉት ሦስት ቅርንጫፎች ናቸው፡፡ እነዚህም ሁመራ፣ ሽራሮና ዳንሻ ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው ምርቱ ጥቅምት መጀመርያ ላይ ነው መግባት የሚጀምረው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁንም ያልገባና ሊገባ የሚችል ምርት አለ፡፡ ከሕግ ማስከበሩ ጋር ተያይዞ ዳንሻ አካባቢ ቶሎ ነው ነፃ የወጣው፡፡ ዳንሻ ቶሎ ነፃ ሲወጣ ቶሎ ብለን ቅርንጫፉን አድሰን ሥራ እንዲጀመር አደረግን፡፡ ያም ከመሆኑ በፊት በተለይ ዳንሻ አካባቢ ያለው ቅርንጫፍ አቅራቢዎች እንዳይቸገሩ አማራጭ ቦታዎችን ከፈትንላቸው፡፡ አብርሃ ጅራና ጎንደር በምርጫቸው ሄደው እንዲገበያዩ አደረግን፡፡ ከዚያ በኋላ ዳንሻን ወደ ሥራ አስገባን፡፡ ከዚያም ሁመራ ሽራሮና ማይካድራ አካባቢ ያሉት ወደ ዳንሻ ምርት እንዲያመጡ አድርገናል፡፡ አሁን ዳንሻ ያለው መጋዘናችን ሞልቷል፡፡ ሌላው ከሰሊጥ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጉዳይ ከዚህ ቀደም ዓመቱ ሲጀምር ምርት የሚወጣበት ጊዜ ላይ የገበያውን ሁኔታ እያዩ አቅርቦቱም በዚያው የሚሄድ ነበር፡፡ ዘንድሮ የሆነው ደግሞ ገና ዓመቱ ሲጀምር ባለፈው ከነበረበት 1,370 እና 1,400 ነበር የዘለቀው፡፡
አሁን በቶን አንድ ሺሕ ዶላር ዋጋው መውጣት ሲጀምር ባለፈው ዓመት ከነበረበት አንፃር ዋጋው የተሻለ ስለነበር ቶሎ የማቅረብ ሁኔታ መጣ፡፡ ሁለተኛ ባለፈው ዓመት ምርት ገበያው ላይ ለዓመታት እንደ ተግዳሮት ሲነሳ የነበረው የአገር ውስጥ የግብይት ዋጋና የዓለም ዋጋ አይናበብም የሚል ፈተና ነበር፡፡ ይህንን ለማጣጣም ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የዓለም አቀፍ ማመላከቻ ዋጋዎች አሉና እነሱን ለማናበብ ሳምንታዊ ገበያዎችና ሌሎችም ዋጋዎች ታሳቢ ተደርገው፣ ዋጋ የሚወጣበትና ዋጋው ከወጣ በኋላ ትመና እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ትመና ውስጥ የሚገበያዩበት ሁኔታ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት በጣም ትልቅ የምርት ፍላጎት ስላለ የፈለገው ደረጃ ቢሆን በአንዱ ዋጋ የመግዛት ዝንባሌ ተፈጥሮ ነበር፡፡ አንደኛ ድሮ ከነበረበት የአገር ውስጥ ገበያና የዓለም ዋጋ ስለማይናበብ፣ ለምሳሌ የውጭ ዋጋ አራት ሺሕና አምስት ሺሕ ሆኖ ሰባት ሺሕ ብር የተሸጠበት ጊዜ አለ፡፡ ሁለት ሺሕ ብር በኩንታል እየከሰረ የሚሸጥበት ሁኔታ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ለምንድነው ይህንን ያህል ኪሳራ ተገብቶ የሚሸጠው?
አቶ ወንድማገኝ፡- ያው ዶላር ለማግኘት ነው፡፡ የኤክስፖርት ሥራ ሳይሆን ዶላር ለማግኘት ነው፡፡ ይኼ የውጭ ምንዛሪ ተመኑም ላይ እንደ አገር ብዙ ፈተና ስለሚፈጥር ይህ መስተካከል አለበት ተብሎ ሲወሰን፣ በአንድ ጊዜ በዓለም አቀፍ ዋጋ አራት ሺሕና አምስት ሺሕ ብር እንዲመለስ ተደረገ፡፡ ስለዚህ በዚህ እየተገበያየ ሲሄድና 4,500 ብር ሲሸጥ አቅራቢ አካባቢ ትልቅ ቅሬታ ፈጠረ፡፡ ምክንያቱም በፊት ሰባት ሺሕ ብር የሚሸጠውን ምርት አሁን አራት ሺሕ ብር ሲሆን ትንሽ የማመንታት ሁኔታ ነበር፡፡
ሁለተኛ አቅራቢዎች ወይም ምርቱን የሚገዙ ሰዎች ሁሉንም ደረጃ አምስት የምንለውን ጭምር በአንድ ዋጋ የመግዛት ሁኔታም ይታይ ነበር፡፡ ጥራትም ችላ መባል ጀምሮ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ቀስ ብለን ሰሊጥና አኩሪ አተር ከዓለም ዋጋ ጋር ነው የሚናበበው የሚል ነገር እንዲፈጠር አደረግን፡፡ እሱ እየመጣ ሲሄድ ቀስ ብሎ ደግሞ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ምርቶች የተለያየ ዋጋ እንዲሰጥ አደረገ፡፡ ይህም ጥራት ያለው ምርት በተሻለ ዋጋ እንዲሸጥ ዕድል ሰጠልን፡፡ የተሻለ ምርት ይዤ ስመጣ የተሻለ ዋጋ አገኛለሁ የሚል አመለካከት ፈጥሮ መሸጥ ተቻለ፡፡
ሪፖርተር፡- በግማሽ የበጀት ዓመቱ ምን ያህል ሰሊጥ አገበያያችሁ ከዕቅዳችሁ አንፃርስ ምን ያህል አሳክታችኋል?
አቶ ወንድማገኝ፡- ግብይቱና ቅበላው ይለያያል፡፡ ወደ 141 ሺሕ ቶን ነው የተቀበልነው፡፡ ግብይቱ ወደ 139 ሺሕ ቶን ነው፡፡ ነገር ግን አፈጻጸማችን ከዕቅድ በላይ ነው፡፡ በግማሽ ዓመቱ እናገበያያለን ብለን ዕቅድ ይዘን የነበረው 114 ሺሕ ቶን ሰሊጥ ሲሆን፣ ያገበያየነው 139 ሺሕ ቶን ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት አገበያይተነው የነበረው 106 ሺሕ ቶን ነው፡፡ በዘንድሮው ግማሽ ዓመት ከተገበያነው ጋር ሲነፃፀር ወደ 33 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ከሕግ ማስከበሩ ጋርም ሆነ ከፀጥታ ችግሩ ጋር ተያይዞ በሰሊጥ ግብይታችሁ ላይ የተፈጠረው ተፅዕኖ ያን ያህል አይደለም እያሉኝ ነው?
አቶ ወንድማገኝ፡- ከሕግ ማስከበሩ ጋር ተያይዞም ሆነ ባለፉት ስድስት ወራት የሰሊጥ ግብይት አፈፃፀማችን በብዙ አልተጎዳም፡፡ ነገር ግን ተፈርቶ ነበር፡፡ ፍራቻውም ተዘርቶ ላይሆን ይችላል፣ የአንበጣም ሥጋት ነበር፡፡ በተወሰነ ደረጃ ማሳው ማሽላ ተዘርቶበታል የሚሉም ነገሮች ስለነበሩ ሥጋት ነበር፡፡ አሁን እኛ ባለን መረጃ ግብይቱ ጥሩ እየሄደ ነው፡፡ ከዕቅዳችን በላይ ሆኖ አፈጻሙ 122 በመቶ ነው፡፡ ምናልባት በቀጣይ ዓመቱ ሲያልቅ ደግሞ ወዴት እንደሚሄድ እናያለን፡፡ ከሌሎች ምርቶች ግብይት አንፃርም ከቡና እናገኛለን ብለን ያቀድነው 136 ሺሕ ቶን ነበር ያገበያየነው፣ 125 ቶን አገበያይተናል፡፡ ይህ የዕቅዳችን 77 በመቶ ነው፡፡ ነጭ ቦሎቄ 19,894 ቶን ነበር ያሰብነው 17,677 ቶን ወይም 89 በመቶውን አሳክተናል፡፡ በስድስት ወራት 21 ሺሕ ቶን አኩሪ እናገበያያለን ብለን 22 ሺሕ ቶን አገበያይተናል፡፡ ይህም ከዕቅዳችን በላይ ነው፡፡ 21 ሺሕ ቶን አረንጓዴ ማሾ እናገበያያለን ብለን 20.9 ቶን አገበያይተናል፡፡ በአዳዲሶቹ ምርቶች ላይ ዕቅዱ ብዙ አልነበረም፡፡ 500 ቶን ነበር ያቀድነው፡፡ ግን 2,256 ቶን አገበያይተናል፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህ አዲስ የገቡ የምርት ዓይነቶችን ከዕቅዳችሁ ወደ አራት እጥፍ ማገበያየት የቻላችሁበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ወንድማገኝ፡- ወደ አራት እጥፍ የሚሆን አገበያይተናል፡፡ በተለይ በጥር ወር በጣም ብዙ እያገበያየን ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ አንደኛ እነዚህ አዳዲስ ምርቶች ወደ ግብይት ሥርዓቱ ሲገቡ ጥሩ ዋጋ ማግኘታቸው ነው፡፡ በተለይ ዥንጉርጉር ቦሎቄ፣ ነጭ እርግብ አተር የሚባሉት በጥሩ ዋጋ ነው እየተገበያዩ ያሉት፡፡ አርሶ አደሩም መረጃ አግኝቷል፡፡ ዘንድሮ በቂ በሚባል ደረጃ ግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራ ተሠርቷል፡፡ እነዚህ ምርቶች በሚመረቱባቸው አካባቢ ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ እንዲያመጡ ተደርጓል፡፡ ሁለተኛ ሕገወጥነትን ለመቆጣጠር መቻሉ ነው፡፡ ለምሳሌ ቀይ ቦሎቄ ቀድሞ በዚህ ገበያ በአስገዳጅነት እንዲገበያይ በተደረገበት ወቅት፣ አንዳንዶች ይኼ ቀይ አይደለም ዥንጉርጉር ነው እያሉ ያስወጡ ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉም የቦሎቄ ዓይነት ወደ ግብይቱ ስለገባ ሕገወጥነቱ በተወሰነ ደረጃ ቀንሷል፡፡ እንዲያውም በሚቀጥሉት ጊዜያት የተሻለ እናገበያያለን የሚል ግምት አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቀጣይ የሚኖረው ሚና እንዴት ይገለጻል? በተለይ የካፒታል ገበያም እየመጣ ነውና ይህ ዕድል ከእናንተ ሥራ ጋር እንዴት ይተሳሰራል?
አቶ ወንድማገኝ፡- ሌላው አገር ለምሳሌ የወርቅ ኮሞዲቴ ኤክስቼንጅ የሚባል አለ፡፡ አንዳንድ አገሮች ለተለያየ ምርቶች የተለየ ኤክስጄንቾች አሏቸው፡፡ እኛ አንደኛ ቀጥታ ወደ ግብይት ሥርዓት ሊገቡ የሚችሉ የግብርና ምርቶችን መጨመር አንዱ ሥራችን ይሆናል፡፡ ሁለተኛ አሁን ወደ ኢንዱስትሪ እየሄድን ነው፡፡ እነዚህ ኢንዱትሪዎች ግብዓት ይፈልጋሉ፡፡ እንደሚታወቀው የእኛ ኢንዱስትሪዎች ሊሆኑ የሚችሉት አግሮ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ስለዚህ አግሮ ኢንዱስትሪ ፕሮሰሲንግ ላይ የሚገቡ ምርቶች ለምሳሌ ጥጥ፣ ሌላው ቀርቶ ቆዳ እንዲገባ ጥናት እያደረግን ነው፡፡ አገሪቱ ትልቅ የቅመማ ቅመም ሀብት አላትና እንዲህ ያሉንም ምርቶች ወደ ግብይቱ የማስገባት ዕቅድ አለ፡፡ እንደ ዕርድ፣ ዝንጅብል፣ ጥቁር አዝሙድና የመሳሰሉት በጥናታችን ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን ታሳቢ እናደርጋለን፡፡ ወደፊት ደግሞ በኢንዱስትሪ ፕሮሰስ የተደረጉ ምርቶችን ማገበያየት ይቻላልና ይህንንም እያየን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?
አቶ ወንድማገኝ፡- ሲሚንቶ በግብይት ሥርዓት ማስተላለፍ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- እንዲህ በማድረግ የሲሚንቶ ግብይት ችግርን መፍታት ይቻላል?
አቶ ወንድማገኝ፡- አዎ፡፡ ለውጭም ማቅረብ ይቻላል፡፡ በአገር ውስጥም ማቅረብ ይቻላል፡፡ እንደ ሲሚንቶ ሁሉ ስኳርንም በተመሳሳይ በስቶክ ኤክስቼንጅ ላይ መሸጥ ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ ምንም ነገር ኮንትራት ሆኖ ደረሰኝ ነው የሚሸጠው፡፡ የካፒታል ገበያ ማለት ይህንን የአዋሽ ባንክ ሼር በዚህ እሸጣለሁ ነው፡፡ ዘይት ሁሉ ማስገባት ትችላለህ፡፡ ስለዚህ የትኛውም ምርት በተለይ የኢንዱስትሪ ምርቶች አሁን ባለው የግብይት ሒደት መቀጠል አይችሉም፡፡ ግብይት ሥርዓት ውስጥ ገብተው እንዲገበያዩ ማድረግ ይችላል፡፡ የካፒታል ገበያ ላይ መጥተህ በነፃ ገበያ ሥርዓት ታገበያየለህ፡፡ አቅርቦትና ፍላጎት ነው ገበያውን መምራት ያለበት፡፡ ደርባ፣ ናሽናል ሲሚንቶና ሌሎችም ፋብሪካዎች ምርቶች በምንፈጥርላቸው መስኮች እንዲገበያዩ ማድረግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ብዙ ምርቶች ወደዚህ እንዲገቡ እናደርጋለን፡፡ በነገራችን ላይ ቡና ብዙ ጊዜ ነው የሚሸጠው፡፡ ምርቱ ሳይመጣ አራት አምስቴ ይሸጣል፡፡ ስለዚህ ይኼ ከካፒታል ገበያ የሚለይ አይሆንም፡፡ ወደፊት የፋይናንስ ገበያው እየሰፋ ሲሄድ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው መሆን ያለበት፡፡ ስለዚህ ሌሎች አዳዲስና ዘመናዊ አሠራሮችንም እንተገብራለን፡፡ አሁን ብዙ ተነካክቶ ብዙ ተዋንያን ኖረውበት ነው ምርቶቻችን የሚሸጡት፡፡ ግን ለምሳሌ የመጋዘን ሰርተፍኬሽን ሥራን፣ የቡና ጥራት ደረጃ የማውጣት ሥራን ኩባንያዎች ቢወሰዱ፣ ሌላው የሥራ ዓይነት ደግሞ በሌላ አካል ቢሠራ ብዙ ነገር መለወጥ ይቻላል፡፡ በዘመናዊ አሠራር የእኛ አምራቾች ካሉበት ሆነው ለሌሎች አገሮች ምርቶቻቸውን መሸጥ የሚችሉበትን ሥርዓት እያጠናከርን ነው፡፡ ይህ ትልቅ እመርታ ይኖረዋል፡፡ በኦንላይን ቤቱ ተሁኖ ግብይት እንዲፈጸም የሚያስችል አሠራር እንዲኖረን እየሠራን ነው፡፡