Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያ በግማሽ ዓመት የ19.8 ቢሊዮን ብር ምርት አገበያየ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰሊጥ ምርት ከዕቅድ በላይ ሲገበያይ ቡና ከዕቅድ በታች ሆኗል

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 2013 ግማሽ የበጀት ዓመት 19.8 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ማገበያየቱን አስታወቀ፡፡ አራተኛውን የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከል በጎንደር ከተማ በሚቀጥለው ሳምንት ለአገልግሎት አበቃለሁ ብሏል፡፡

ምርት ገበያ 2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያው መንፈቅ የ19.8 ቢሊዮን ብር ግብይት የፈጸመው 323,140 ቶን ምርት በማገበያየት መሆኑን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ ገልጸዋል፡፡

የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም ከዕቅዱ አንፃር ሲታይ የአምስት በመቶ የግብይት ቅናሽ የታየበት ሲሆን፣ በዋጋ ደረጃ ግን 13 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡አጠቃላይ አፈጻጸሙም በግማሽ ዓመት አሳካዋለሁ ብሎ ካቀደው 99 በመቶን ማከናወን ችሏል፡፡

በግማሽ ዓመቱ 114 ሺሕ ቶን ሰሊጥ ለማገበያየት አቅዶ ከዕቅዱ በላይ 122 በመቶ መከወኑን የሚያመለክተው መረጃ፣ በስድስት ወር ውስጥ የተገበያየው የሰሊጥ ምርት መጠን 139 ቶን መሆኑም አመልክቷል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ከዕቅድ በታች የሆነ አፈጻጸም የታየው በቡና ግብይት ላይ ሲሆን፣ በግማሽ ዓመቱ ለማገበያየት ከታቀደው ማሳካት የተቻለው 77 በመቶ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ምርት ገበያው በግማሽ በጀት ዓመቱ አገበያያለሁ ብሎ ያቀደው 136 ቶን ቡና ቢሆንም፣ ያገበያየው 105 ቶን ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በሌሎች አማራጭ የግብይት ሥርዓቶች ቡና ለውጭ ገበያ በመቅረቡ ነው ተብሏል፡፡

ለግብርና ምርት አቀነባባሪዎች በተከፈተው ልዩ የግብይት መስኮትም 10,592 ቶን አኩሪ አተር 198 ሚሊዮን ብር ማገበያየት ስለመቻሉ የሚያመለክተው መረጃ፣ ነጭ የርግብ አተር፣ ዥንጉርጉር ቦሎቄና ፒንቶ ቢን ወደ ዘመናዊ የግብይት መድረክ መግባታቸው ምርት ገበያው የሚያገበያየውን ምርት ብዛት 12 አድርሶታል፡፡

ጥጥ፣ ቅመማ ቅመምና ጥራጥሬን ጨምሮ ዘጠኝ ተጨማሪ ምርቶችን ወደ ግብይት ለማስገባት የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አቶ ወንድማገኝ በሰጡት ማብራሪያ አመልክተዋል፡፡ የክፍያና ርክክብ ሥርዓትን በተመለከተ ከተገበያዮች ሁለት በመቶ ዊዝ ሆልዲንግ ታክስና 30 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ እሴት ታክስ በመቀነስ 379.3 ሚሊዮን ብር ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ፈሰስ ማድረጉንም የምርት ገበያው የስድስት ወር ሪፖርት ያመለክታል፡፡

 የመጋዘን የብድር አገልግሎት ለመስጠት ከአራት ባንኮች ጋር ስምምነት ስለመፈራረሙ ሌላው በስድስት ወሮች ውስጥ ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ ተጠቃሽ ሆኖ ቀርቧል፡፡  የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አገልግሎቱን የበለጠ ለማስፋት በሥራቸው በሺሕ የሚቆጠሩ አባላትን የያዙ አሥር የኅብረት ሥራ ማኅበራት በልዩ ሁኔታ የአባልነት ወንበር እንዲያገኙ ማድረጉም ታውቋል፡፡ ከዚህም ሌላ በሻኪሶ፣ በባህርዳርና በቄለም ወለጋ ቅርንጫፎች ለመክፈት የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ ሲሆን፣ የተገበያዮችን የግብይት ተሳትፎ ለማሳደግም ለጥራጥሬና ቅባት እህል 1681 ለቡና 112 አባል ያልሆኑ ቀጥታ ተገበያዮች ተመዝግበው በቅበላ ሒደት ላይ ናቸው ተብሏል፡፡

ምርት ገበያው ተቋማዊ አቅሙን በማሳደግ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት በሰጠው ትኩረት በቡሌ ሆራና በመቱ የተገነቡትና እያንዳንዳቸው 150 ሺሕ ኩንታል የሚይዙ መጋዘኖች አጠናቋል፡፡ በጎንደርና በሁመራ የተጀመሩት የመጋዘን ግንባታዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ 11 የቡና መቀበያ ቅርንጫፎች ክረምት ከበጋ ሊያገለግሉ የሚችሉ የናሙና መውሰጃዎች ተገንብተው ሥራ ላይ እንደዋሉም ታውቋል፡፡ 

በዚህ ግማሽ ዓመት የቡና ተገበያዮች ናሙና እያዩ እንዲገበያዩ በማድረግ፣ የጥራት ደረጃ አሰጣጥ አውቶሜት ከማድረግ በተጨማሪ የአራት ዓይን (Maker Checker) የክትትል ሥርዓት ሥራ ላይ ውሏል፡፡ ተገበያዮች የሁሉንም ምርቶች የቅድመ ግብይት መረጃ በየዕለቱ ከግብይት በፊት እንዲያገኙ ማድረግ ስለመቻሉም ተገልጿል፡፡ ጥራትን መሠረት ያደረገ የግብይት ዋጋ እንዲሰፍን በመሥራት፣ ሻጮች ምርታቸውን በቅድመ ግብይት ምዝገባ የሚያሳውቁበት አሠራር በመዘርጋትና አቅራቢዎች ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን ካቀረቡበት ቅርንጫፍ ወስደው ጥራቱን አሻሽለው እንዲያቀርቡ በማድረግ የአሠራር ማሻሻያዎች ስለመደረጋቸውም ተነግሯል፡፡ 

ምርት ገበያው በግማሽ በጀት ዓመቱ ከገጠሙት ችግሮች መካከል በሁመራ፣ ዳንሻና ሽራሮ የሚገኙ የምርት መቀበያና የሁመራ ግብይት ማዕከላት በአካባቢው በሚደረገው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ምክንያት አገልግሎታቸው መቋረጡና የኮንትሮባንድ ንግድ ተጠቃሽ ናቸው ብሏል፡፡ ችግሮቹን ለመከላከል የዳንሻ ቅርንጫፍ በተዘጋበት ወቅት አቅራቢዎች ምርታቸውን ወደ ጎንደርና አብርሃጅራ ቅርንጫፎች እንዲያቀርቡ በማድረግና ዳንሻ ቅርንጫፍ በአካባቢው ሰላም ከሰፈነ በኋላ ወደ መደበኛው ሥራ ሲመለስ ወደ ሁመራና ሽራሮ ቅርንጫፎች መቅረብ የነበረበትን የሰሊጥ ምርት ከአቅራቢዎች በመረከብ የግብይት ሥርዓቱ እንዳይቋረጥ መደረጉንም አስታውሷል፡፡

የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ አሁንምነጭ ቦሎቄና ሌሎች ምርቶች ሕገወጥ ንግድ በመቀጠሉ፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተቀራርቦ እየተሠራ ነውብሏል፡፡ 

በትግራይ ክልል ከሕግ ማስከበር ሥራው ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ችግር የሰሊጥ ምርት በበቂ ሁኔታ ያለመቅረቡ እየተጠቀሰ ቢሆንም፣ አቶ ወንድማገኝ በግማሽ ዓመቱ የሰሊጥ ምርት ግብይት ከዕቅዱ በላይ ስለመከናወኑ ገልጸዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ በግማሽ በጀት ዓመቱ ምርት ገበያው ለማገበያየት አቅዶ የነበረው 114 ሺሕ ቶን ሰሊጥ ቢሆንም፣ 139 ሺሕ ቶን ማገበያየት ችሏል፡፡ የሰሊጥ ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግብይቱ 33 በመቶ ዕድገት የታየበት ስለመሆኑ አቶ ወንድማገኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 2012 ግማሽ የበጀት ዓመት ተገበያይቶ የነበረው የሰሊጥ ምርት መጠን 106 ቶን ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በጎንደር የሚከፈተው ማዕከል የዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱን አገልግሎት ለአርሶ አደሩ፣ ለአቅራቢዎች፣ ለግብርና ምርት አቀነባባሪዎች፣ ለላኪዎችና ለሌሎችም አካላት የበለጠ ተደራሽ በማድረግ ካሉበት  ሆነው ግብይት እንዲፈጽሙ የሚያስችል ነው ብሏል፡፡

 ምርት ገበያው ከዋናው መሥሪያ ቤት በተጨማሪ በሀዋሳ፣ በሁመራና በነቀምት የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም አስታውሷል፡፡ ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማስፋት በአዳማና በጅማ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላትን ግንባታ ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በሚዛንና በቴፒ አዳዲስ ቅርንጫፎችን ለመክፈት መዘጋጀቱንም አቶ ወንድማገኝ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች