በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ 18 ኩባንያዎች አንዱ የሆነው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የኢንዱስትሪውን የገበያ ድርሻ መልሶ መያዝ መቻሉ ተመለከተ፡፡
የአገሪቱን ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ወቅታዊ አቋምና የ2013 ግማሽ የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም በሚያመለክተው ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት መሠረት፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ17ቱ የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ብልጫ ተወስዶበት የነበረውን የገበያ ድርሻ መልሶ ይዟል፡፡
እንደ የሒሳብ ሪፖርቱ፣ በ2013 ዓ.ም. የመጀመርያ ግማሽ የሒሳብ ዓመት የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ጨምሮ 18ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጥቅል ካሰባሰቡት 8.72 ቢሊዮን ብር ዓረቦን ውስጥ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት 4.84 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ዓረቦን መሰብሰብ ችሏል፡፡
ድርጅቱ የሰበሰበው ጠቅላላ የዓረቦን መጠን በኢንዱስትሪው በጥቅል ከተሰበሰበው ዓረቦን ውስጥ 55.5 በመቶ መሆኑም ታውቋል፡፡
17ቱ የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በስድስት ወራት ውስጥ የሰበሰቡት የዓረቦን መጠን 3.88 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ የያዙት የገበያ ደረጃም 44.5 በመቶ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ዕድገት የታየበት በመሆኑ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለው የገበያ ድርሻ ከፍ እንዲል ከማድረጉም በላይ የግማሽ ዓመቱ ዕድገት ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ29 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
ከአኃዛዊ መረጃው መገንዘብ እንደሚቻለውም፣ በግማሽ ዓመቱ 18ቱም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሰበሰቡት ዓረቦን ከ2012 ግማሽ ዓመት አንፃር ሲታይ፣ የ22.5 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ግን ዕድገቱ 29 በመቶ መሆኑ የዘርፉን የግማሽ ዓመት አፈጻጸም በተለየ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡
የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ኢንዱስትሪውን መቀላቀል ከጀመሩበት ከ26 ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በብቸኝነት ይዞት የነበረውን ገበያ እየተካፈሉ በመቆየት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የገበያ ድርሻን እስከ 33 በመቶ ማውረድ ችለው ነበር፡፡
ከሦስት ዓመት ወዲህ ግን የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የገበያ ድርሻውን ከፍ እያደረገ በመምጣት፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት የገበያ ድርሻውን ወደ 45 በመቶ፣ በ2013 ግማሽ ዓመት ደግሞ ወደ 55.5 በመቶ ማድረስ ችሏል፡፡
በግማሽ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የደረሰበት ደረጃ ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የኢንዱስትሪውን ገበያ ለመያዝ ያስቻለው ነው፡፡
ይፋዊ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በ2012 ዓ.ም. 18ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከሰበሰቡት ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች 55 በመቶ የሚሆነውን ገበያ ይዘው ነበር፡፡
በ2011 የሒሳብ ዓመትም 62 በመቶ የአረቦን ሽፋን በግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተያዘ መሆኑን ሲያሳይ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የገበያ ድርሻ 38 በመቶ እንደነበር ያመለክታል፡፡
የ17ቱን የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የዓረቦን አሰባሰብ በተመለከተ ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርቱ የሚያመለክተው፣ ከፍተኛውን ዓረቦን በማሰባሰብ ቀዳሚ የሆነው አዋሽ ኢንሹራንስ ነው፡፡
በ2013 ግማሽ የሒሳብ ዓመት አዋሽ ኢንሹራንስ ማሰባሰብ የቻለው ጠቅላላ የዓረቦን መጠን 548.7 ሚሊዮን ብር በመሆኑ፣ 6.3 በመቶ የሚሆነውን የገበያ ድርሻ እንደያዘ ያመለክታል፡፡
ከአዋሽ ኢንሹራንስ ቀጥሎ ከፍተኛውን ዓረቦን ያሰባሰቡት ደግሞ ኒያላ ኢንሹራንስ፣ ኅብረት ኢንሹራንስና አፍሪካ ኢንሹራንስ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በግማሽ ዓመቱ 18ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሰበሰቡት የዓረቦን መጠንም፣ ከ2012 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ22 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡
በግማሽ ዓመቱ ከተሰበሰበው 8.7 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ 8.35 ቢሊዮን ብር ወይም 95.8 በመቶ የሚሆነው ከጠቅላላ ኢንሹራንስ ሲሆን፣ 368.2 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከሕይወት ኢንሹራንስ የተሰበሰበ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 18ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጠቅላላ ያላቸው የካፒታል መጠን 9.65 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 2.82 ቢሊዮን ብር ካፒታል የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሲሆን፣ ቀሪው ከ6.8 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው የካፒታል መጠን ደግሞ የ17ቱ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ነው፡፡
ከ17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ የካፒታል መጠኑ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሆነው አዋሽ ኢንሹራንስ ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ያስመዘገበው የካፒታል መጠን 1.31 ቢሊዮን ብር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡ ቀሪዎቹ 16 የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከ115 ሚሊዮን ብር እስከ 891 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጥቅል በመላ አገሪቱ ያላቸው ቅርንጫፎች ብዛት ከ605 እንደሚልቅ ይታወቃል፡፡