‹‹የእኛ ቀጣዩ ሥራ ትግራይን መገንባት ነው። የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ ችግር ያለበት በሬሽን የሚኖር ነው። ስለሆነም ቶሎ ብለን ሕዝባችን ከዚህ ችግር እንዲወጣ መደገፍ አለብን፣ ማቋቋም አለብን፣ የተሰደዱትን መመለስ አለብን።››
ከላይ የተገለጸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት በትግራይ ክልል የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጠናቀቁ በይፋ በተገለጸ በቀናት ውስጥ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የሕግ ማስከበር ዘመቻው የተፈጸመበትን ሒደትና ቀጣይ ሥራዎችን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ውጊያ ምክንያት ከቀዬአቸው ተፈናቀለው ወደ ሱዳን የተሰደዱ ነዋሪዎች ቁጥር 30 ሺሕ ገደማ እንደነበር በወቅቱ የወጡ ሪፖርቶችን በዋቢነት በመጥቀስ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ከትግራይ የተፈናቀሉትን ስደተኞች የመመለስ ሥራ ለመንግሥታቸው ከባድ ኃላፊነት እንዳልሆነና በሳምንት ውስጥ የሚተገብሩት እንደሆነ በወቅቱ አስረድተዋል።
‹‹የተከበረው ምክር ቤት እንደሚያውቀው ይህ የለውጥ ሒደት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሷል፣ አቋቁሟል። ከትግራይ የተፈናቀሉ 30 ሺሕ ገደማ የሚሆኑትን መመለስና ማቋቋም ለእኛ ቁርስ ናት። ይህንን የማድረግ ልምድ አለን። በሶማሌ ልምድ አለን፣ በጌዴኦ ልምድ አለን፣ በሁሉም ቦታ ተፈናቅሎ የነበረውን መልሰን አቋቁመናል። ከትግራይ የተፈናቀሉትንም በሳምንት መልስን እናቋቁማለን። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋማት ሊያግዙን ከፈለጉ በራችን ክፍት ነው፤›› ብለው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከላይ የተገለጸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስረዱት በኅዳር ወር 2013 ዓ.ም. መገባደጃ ሳምንት ላይ ሲሆን፣ ከዚህ ንግግራቸው በኋላ ድፍን ሁለት ወራት ተቆጥረዋል።
በእነዚህ ድፍን ሁለት ወራት በትግራይ ክልል የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ መፍትሔ እያገኘ ሳይሆን፣ ተባብሶ እንደ ቀጠለና የነዋሪዎች ሥቃይም እየሰፋና ጥልቅ ሆኖ እየቀጠለ ስለመሆኑ በሥፍራው የአቅማቸውን ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የሰብዓዊ ዕርዳታና የሰብዓዊ መብት ተቋማት ይገልጻሉ።
የክልሉ ነዋሪዎች የሚቀምሱት አጥተው ሕይወታቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ እየገፉ ከመሆናቸው ባለፈ፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙባቸው እንደሚገኝም መረጃዎች ያለመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ፣ በቦታው ያሉ የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት፣ እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቦታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ሁኔታ በመከታተል ከሁለት ሳምንታት በፊት ያቀረበው ሪፖርት በክልሉ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ያሳያል።
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ጨርጨር ወረዳ በሚገኙት ኡላጋና ቢሶበር መንደሮች በመጓዝ ከኅዳር 5 እስከ ኅዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በአካባቢው ስለደረሰ የሲቪል ሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት መዘረፍና መውደም እንደ ደረሰ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።
ቢሶቦር አካባቢ በነበረው ውጊያ 31 ሰላማዊ ነዋሪዎች መገደላቸውን፣ አብዛኞቹም በጦርነቱ ምክንያት የሞቱ መሆናቸውን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ ከዚህ ውጭ ለሕወሓት መረጃ ታቀብላላችሁ ተብለው ግድያ የተፈጸመባቸው መኖራቸውንም አመልክቷል።
ለአብነትም አቶ ተስፋዬ አበራ የተባሉ የቢሶበር ነዋሪ የነበሩ ሟች ታርደው የሞቱ መሆናቸውን ሬሳውን በማየት መረዳት እንደተቻለ፣ ነገር ግን ማን እንደ ገደላቸው እንደማያውቁ የሟቹን ቀብር ከፈጸሙት ምስክሮች መረዳቱን ገልጿል።
በተጨማሪም አንድ እናት የባለቤታቸውንና የልጃቸውን አሟሟት ለኮሚሽኑ በሐዘን ከገለጹ በኋላ፣ የተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ‹‹ለጠላት መረጃ ታቀብላለህ›› በሚል ያላግባብ እንደ ገደሉባቸው፣ አንድ ሌላ የቢሶበር ነዋሪም አካል ጉዳተኛ ልጃቸው በተመሳሳይ እንደተገደለ ለኮሚሽኑ መግለጻቸውን በሪፖርቱ አስታውቋል።
በአካባቢው የነበረውን ውጊያ በመሸሽ ላይ ሁለት ነፍሰ ጡር ሴቶች መንገድ ላይ ሲንገላቱ የነበረ መሆኑን ከነዋሪዎች መረዳቱንና አንደኛዋ እናት መንገድ ላይ ለመውለድ በመገደዳቸው ልጃቸው እንደ ሞተባቸው፣ ሁለተኛዋ እናት ደግሞ ከከፍተኛ ሥቃይ በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰው መውለዳቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በተመለከታቸው አካባቢዎች ማለትም በሁመራ፣ በዳንሻ፣ በቢሶበርና ኡላጋ የሚኖረው ኅብረተሰብ የደኅንነት ሥጋት ውስጥ እንደሚገኝ፣ በተለይ በሁመራና በዳንሻ በሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ላይ ብሔር ተኮር መንገላታቶች እየደረሱ በመሆኑ መንግሥት በፍጥነት መፍትሔ እንዲያበጅለት ጠይቋል።
በዚህ ሪፖርት በተካተቱ አካባቢዎች በተወሰኑ የፀጥታ ኃይል አባሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተገቢው ምርመራ ተደርጎ፣ የአጥፊዎቹ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባም ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳቡን ለመንግሥት አቅርቧል።
ለነዋሪዎችና ተፈናቃዮች የመጀመሪያ ዙር ዕርዳታ መደረጉ አበረታች ቢሆንም፣ በነዋሪዎቹና በአካባቢዎቹ ላይ ከደረሰው ጉዳት አንፃር ከፍተኛ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልግ መሆኑን፣ በተለይም ግጭት ባልቆመባቸውና የፀጥታ ሁኔታው አሥጊ በሆነባቸው የክልሉ አካባቢዎች ለሲቪል ሰዎች ዕርዳታ ለማቅረብ የመከላከያ ሠራዊቱን ድጋፍ ጨምሮ፣ አስፈላጊው ጥረት መደረግ እንዳለበትም ኮሚሽኑ ለመንግሥት ባቀረበው በምክረ ሐሳቡ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርቱንና ምክረ ሐሳቡን ለመንግሥት ካቀረበ በኋላም ቢሆን፣ በክልሉ የሰብዓዊ ቀውስ እየተባባሰ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና የጨረቃ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ዓለም አቀፋ የቀይ መስቀል ተቋማት ፌዴሬሽን ሐሙስ ጥር 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት መግለጫም በክልሉ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ እየተባባሰና የተረጂዎች ቁጥርም በአሳሳቢ ደረጃ እያሻቀበ እንደሆነ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ቶላ በትግራይ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ ሲገልጹ፣ ‹‹በወቅቱ መድረስ ባለመቻሉ በክልሉ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ አሳሳቢና ጥልቅ እየሆነ መጥቷል፤›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከስድስት ሳምንታት በፊት ባደረገው ዳሰሳ በክልሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ነዋሪዎች ቁጥር 2.2 ሚሊዮን እንደነበር የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በአሁኑ ወቅት የተረጂዎች ቁጥር ከሦስት ሚሊዮን በላይ እንደ ደረሰ አስትውቀዋል፡፡
‹‹ዋና ከተማዋ መቀሌን ጨምሮ በጦርነቱ ተፅዕኖ ያልደረሰበት የትግራይ ክልል አካባቢ የለም፤›› ያሉት አቶ አበራ ቶላ፣ ‹‹ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ የተቻለው ግን በከተሞችና ዋና ዋና መንገዶች ላይ ለሚገኙ አካባቢዎች ብቻ ነው፤›› ብለዋል።
ማኅበሩ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ መቸገሩን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ለአብነትም እንደ ሽሬ፣ አዲግራትና ሐውዜን የመሳሰሉ አካባቢዎችና ሌሎች ገጠራማ አካባቢዎች መድረስ አለመቻሉን ተናግረዋል።
የማኅበሩ አምቡላንሶችም በተደጋጋሚ የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ጦርነቱ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ 60 የሚሆኑ አምቡላንሶች ጥቃት እንደተፈጸመባቸውና እንደተነጠቁ አመልክተዋል።
ይህንንም ሲያስረዱ ማኅበሩ ሰብዓዊ አገልግሎት ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ በጦርነቱ የሚሳተፉት ወገኖች በጥርጣሬ በማኅበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ገልጸዋል።
ዕርዳታ ማድረስ ያልተቻለባቸው አካባቢዎች ለመግባት ያልተቻለውም፣ በአካባቢዎቹ አሁንም ድረስ ውጊያ በመኖሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
በክልሉ ቀደሞውንም በሴፍቲኔት የዕርዳታ ፕሮግራም ሥር የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ስለነበሩ፣ በጦርነቱ ምክንያት የመጣው ቁጥር ተጨምሮበት ሁኔታውን በእጅጉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰው፣ በተለይም አልሚ ምግብ ለሚፈልጉ ሕፃናት በፍጥነት ሊደረስላቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።
‹‹ያለው የሰብዓዊ ቀውስ በፍጥነት ምላሽ እየተሰጠው ባለመሆኑ ዛሬ የነበረው የተረጂዎች ቁጥር በንጋታው እያሻቀበ ይገኛል፡፡ ሁኔታው የተለየና ጥልቅ እየሆነ ነው፤›› ብለዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃ ደስታ ከሳምንት በፊት በሰጡት አስተያየት፣ በክልሉ በተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ሰዎች የሚቀምሱት አጥተው እስከ መሞት እየደረሱ እንደሆነ ጠቁመዋል።
‹‹በምዕራብ ትግራይ አካባቢ በጉሎ መኸዳ ወረዳ አሥር ሰዎች መሞታቸውን፣ በዓድዋ ደግሞ ሦስት ሕፃናት በረሃብ ስለመሞታቸው ሪፖርት ደርሶናል፤›› ብለዋል።
አቶ አብርሃ እስካሁን እየተደረገ ባለው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት መድረስ የተቻለው ጥቂት የማኅበረሰብ ክፍሎችን ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል።
እየተደረገ ባለው ጥረት በመቀሌ 50,000 ነዋሪዎች ዕርዳታ እንደተደረገላቸው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥም እስከ 300,000 ለሚደረሱ ነዋሪዎች ዕርዳታ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለአብዛኞቹ የክልሉ ነዋሪ አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ያሉት አቶ አብርሃ፣ እሳቸው የሚመሩት ቢሮ ባደረገው ዳሰሳ በአሁኑ ወቅት 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ ዕርዳታ እንደሚያስፈለገው መረጋገጡንና ከዚህ ውስጥ ደግሞ 2.5 ሚሊዮን የሚሆናት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሰብዓዊ ዕርዳታውን በፍጥነት ለማድረስም ሁሉንም የክልሉን መሥሪያ ቤቶች በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት የቢሮው ኃላፊ አቶ አብርሃ፣ ወደ ክልሉ ምዕራባዊ ዞን የአስተዳደር መዋቅር ገና ባለመዋቀሩ ወደዚያ አካባቢ ዕርዳታ ማድረስ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
ከላይ የተገለጹት መረጃዎች በትግራይ ክልል አፋጣኝ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ነዋሪዎች ቁጥር አራት ሚሊዮንና ከዚያ በላይ እንደሆነ ቢጠቁሙም፣ የፌዴራል መንግሥት መረጃ ግን በትግራይ ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ተረጂዎች ቁጥር እንደሚባለው እንዳልሆነ በመግለጽ ላይ ነው።
ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይህንኑ የተናገረ ሲሆን፣ በኮሚሽኑ መረጃ መሠረት በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ነዋሪዎች ቁጥር 2.5 ሚሊዮን ብቻ ነው።
ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ምትኩ ካሳ ከሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ፣ በክልሉ በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉና ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ነዋሪዎች ብዛት ሰባት መቶ ሺሕ እንደሆነ ገልጸዋል።
የተቀሩት ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚፈልጉ 1.8 ሚሊዮን የክልሉ ነዋሪዎች፣ ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በፊትም ሰብዓዊ ዕርዳታ ይደረግላቸው የነበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
‹‹ከሕግ ማስከበር ዕርምጃው በፊት ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚደረግላቸው 1.8 ሚሊዮን ዜጎች ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ 1.1 ሚሊዮን የሚሆኑት በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ የነበሩ ናቸው። በተጨማሪም የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ፕሮግራም ሥር 500 ሺሕ ነዋሪዎች ድጋፍ ይደረግላቸው የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ በተረፈ ያሉት 110 ሺሕ ነዋሪዎች ደግሞ ቀደም ብሎ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በነበረው ግጭት ተፈናቀለው ዕርዳታ የሚደረግላቸው ናቸው፤›› ብለዋል።
ከተገለጸው አኃዝ ውጪ በሕግ ማስከበር ጋር ተያይዞ የተፈናቀሉ ተጨማሪ ነዋሪዎች መኖራቸውን ለመለየት፣ ከፌዴራልና አጋር አካላት የተውጣጣ ቡድን እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ለተለዩት 2.5 ሚሊዮን ነዋሪዎች የተሟላ የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ የሚያስችል በቂ አቅርቦት መኖሩን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ አለ ያሉትን አቅርቦትም እንደሚከተለው ዘርዝረዋል።
‹‹በተለያዩ መጋዘኖች 311,526 ኩንታል የእህል ክምችት እንደሚገኝ፣ 60 ሺሕ ኩንታል ዱቄት፣ 1.7 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይትና 173,200 ኩንታል ስንዴ፣ ከ51 ሺሕ ኩንታል በላይ አልሚ ምግብ፣ እንዲሁም 28,480 አልባሳትና የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶች ዝግጁ ናቸው፡፡ ለተጎጂዎች ለማድረስ እየተሠራ ነው። የኮሚሽኑ በአቅርቦት ረገድ ክፍተት የለበትም፣ ያለው ክምችት ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መመገብ የሚችል ነው፤›› ብለዋል፡፡
ይህንን አቅርቦትም በክልሉ በሚገኙ 97 የምግብ ማሠራጫ ማዕከሎች አማካይነት ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጹት ኮሚሽነሩ ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት፣ ለነፍሰ ጡር እናቶች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለሕሙማን አስቸኳይ ዕርዳታውን በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጋር በጥምረት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።
በክልሉ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ለመሥራት እንዲቻል፣ በሰላም ሚኒስቴር የሚመራ አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ መቋቋሙንም ጠቁመዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከሚገኙ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደሮችና ከአገሮቹ ተወካዮች ጋር በትግራይ ክልል ያለውን ሰብዓዊ ሁኔታ በተመለከተ የተወያዩ ሲሆን፣ በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በክልሉ ተፈጽመዋል የተባሉ ሰብዓዊ ጥሰቶችን መንግሥት እየመረመረ እንደሆነ ገልጸዋል።
በክልሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጋጥሟል ተብሎ የሚነሳውን ጉዳይ በተመለከተም፣ በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማጣራት በመካሄድ ላይ እንደሆነ ገልጸው፣ የተጀመረው የማጣራት ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ችግር የፈጠሩ አካላት በጥንቃቄ ተለይተው ተጠያቂ ለማድረግ መንግሥት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
አቶ ደመቀ አክለውም በትግራይ ክልል በመንግሥትና በዕርዳታ ድርጅቶች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በዚህም መድኃኒቶችን ጨምሮ ምግብና ምግብ ነክ ድጋፎችን በተለዩ 92 ማሠራጫ ጣቢያዎች ማዳረስ መጀመሩን ተናግረዋል።