Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብና ንብረትን ለማስተዳደር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ጥያቄ ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብና ንብረት ከተመለሰ በኋላ፣ በተቀናጀ ሁኔታ ሊያስተዳድር የሚችል ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ ሊዘጋጅለት እንደሚገባ ተጠየቀ፡፡

ይህ የተገለጸው የፋይናስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብና ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ (Money Laundering) እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት (Financing of Terrorism) ወንጀሎች ለመከላከል የሚያስችል ሥልጠና፣ ከዴንማርክ መንግሥት ጋር በመተባበር ከጥር 24 እስከ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐርመኒ ሆቴል በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

በፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል የፋይናንስ ሱፐርቪዥን ቡድን መሪ አቶ ሙሉጌታ ተመሥገን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በወንጀል የተገኘ ሀብትን ማስመለስና የተመለሰውን ሀብት ማስተዳደር የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ሀብት የማስመለሱን ጉዳይ በተለመከተ በዳይሬክቶሬት ደረጃ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር ተቋቁሟል፡፡ ሆኖም ሀብቱ ከተመለሰ በኋላ ከማስተዳደር ጋር የተያያዘው ጉዳይ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

ሀብት በማስመለስ ላይ በቅንጅት እየተከናወነ ያለው ሥራ ውጤት ከማስመዘገቡ ጋር ተያይዞ፣ የማስተዳደር ሥርዓቱም ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

የጣና ኮፐንሃገን የፀረ ሕገወጥ ገንዘብና ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ አማካሪ አቶ ቢኒያም ሽፈራው በበኩላቸው፣ የተለያዩ አካላት ገንዘብ ከመዘበሩ በኋላ ለተለያየ ዓላማ ሊያውሉት እንደሚችሉ ገልጸው፣ ሆኖም ‹‹ገንዘቡን ለማስመለስ ምን እየተሠራ ነው›› ለሚለው ክፍተቶች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት ድርጊቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡

 ሀብት ቀላል ጉዳይ ባለመሆኑ ትኩረት መስጠት ያሻል የሚሉት አማካሪው ከአገሪቱ በሙስና፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ገንዘብን አስመስሎ ማቅረብ (ፎርጂድ) እና በኮንትሮባንድ የሚዘረፈውን ገንዘብ ለማስመለስና ለማስተዳደር የሚያስችል ራሱን የቻለ የሕግ ሥርዓት ያስፈልገዋል ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹ይህን መሰል ጉዳዮች እየታዩ ያሉት በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ሲሆን፣ በአዋጅ ቁጥር 780/2005፣ በፀረ ሙስና ሕጎች፣ በፀረ ሽብር አዋጅ 1176/2012፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግና በሌሎች አዋጆች ነው፡፡ አሠራሩ የተበታተነ በመሆኑ ለማስፈጸምም፣ ወደ ተግባር ለመግባትም ጉዳዩን ከባድ አድርጎታል፤›› ብለዋል፡፡

ገንዘብና ንብረትን ለማስመለስ በመጀመርያ ተመሳስሎ የቀረበውንም ሆነ የሸሸውን በደንብ በዝርዝር ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል የሚሉት አማካሪው፣ ወንጀልና ሀብቱ በትክክል የተገናኙ መሆናቸው ሲረጋገጥ ማገድና መያዝ ቀጣዩ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ከመታገድና ከመያዝ በዘለለ ግን ንብረቱ ተወርሶ ለተገቢው ተግባር መዋል እንዳለበት፣ ይህም ሀብቱ ሳይባክን ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርገዋል በማለት አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ቢኒያም ገለጻ በወንጀል የተገኘ ገንዘብን ማስመለስና ማስተዳደር ወደ መሬት አውርዶ በሕግ ማዕቀፍ ሥር ማስተዳደር አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከልና ሌሎችም በጉዳዩ ላይ ሥልጣንና ተልዕኮ ያላቸው ሁሉ በጉዳዩ ላይ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ በበኩላቸው፣ ሕገወጥ ገንዘብና ሀብትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ (Money Laundering) በአገራችን ሰፊ የሆነ ተፅዕኖ እያደረሰ ስለሚገኝ የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልገው፣ የሚዲያ አካላት ድርሻም በተለይ እንደነዚህ ዓይነት ውስብስብ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ መረጃዎችን በመስጠት ረገድ ትልቅ ነው ብለዋል፡፡

የፋይናንስ ሱፐር ቪዥን ቡድን መሪው እንደገለጹት በዓለም ላይ አራት የፋይናንስ ደኅንነት ዓይነቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም በኢትዮጵያ ያለው የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ አስተዳደር ሲባል፣ ይህም አጠቃላይ መረጃዎችን ለሦስተኛ ወገን የሚያሳልፍ እንጂ ሰው ማሰር አይችልም፣ አይከስም፣ አይመረምርም፣ አይበረብርም፣ ቀጥታ ከውጪ አገር ብር አያመጣም፡፡ በመሆኑም የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል ሥልጣኑ ከፋይናንስ ተቋማትና ፋይናነስ ነክ ካልሆኑ የንግድና የሙያ ማኅበራት የሚቀርቡለትን የጥሬና የጥርጣሬ ግብይት ሪፖርቶችን ተንትኖ ማቅረብ ነው፡፡ አጠቃላይ ከውጪ ያለውን ሀብት የማስመለስ ሥራ በጋራ በመሆን የፋይናንስ ደኅንነት ማዕከል መረጃ በማቀበልና ዓቃቤ ሕግ ክስ በመመሥረት፣ እንዲሁም ሌሎች ኃላፊነቱ በሚመለከታቸው አካላት የሚሠራ እንጂ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚሰጥ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች