Tuesday, January 31, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ድጋፍና ተቃውሞ በእኩልነት ይስተናገዱ!

ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት የሕግ የበላይነት ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ በሕግ የበላይነት የማይተዳደር አገር የሥርዓት አልበኞች መፈንጫ ይሆናል፡፡ የሕግ የበላይነት ማለት ደግሞ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል የሚሆኑበትና የሚዳኙበት ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ስም ግን አድልኦና ሸፍጥ የሚፈጸም ከሆነ፣ የምንነጋገረው ስለሕገወጥነት ይሆናል ማለት ነው፡፡ አገርን በሥርዓት መምራትም ሆነ መመራት የሚቻለው ፍትሕ ለሁሉም እኩል ተደራሽና ተዓማኒ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ አንዱ የሚደሰትበት ሌላው የሚከፋበት ብልሹ አሠራር ለሕግ የበላይነት ተፃራሪ ከመሆኑም በላይ፣ ለሰላምና ለመረጋጋት ጠንቅ ነው፡፡ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ እኩል ከሚሆኑባቸው ማመላከቻዎች አንዱ፣ የፈለጉትን የመደገፍ የማይፈልጉትን የመቃወም መብት ነው፡፡ በተጨማሪም ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ቡድን ድረስ በሰላማዊ መንገድ ቅሬታ ማቅረብ መብት ነው፡፡ ይህ መብት ደግሞ በሕግ ጭምር የተረጋገጠ ነው፡፡ በመንግሥት ላይ በሰላማዊ መንገድ ቅሬታ ማቅረብም ሆነ፣ መንግሥት ለሠራው መልካም ተግባር ድጋፍ መስጠት በእኩልነት መስተናገድ ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ መንግሥት ላይ ቅሬታ ያላቸው አካላት በሰላማዊ መንገድ እንዳይስተናገዱ እየተደረገ፣ ለመንግሥት ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ከተፈቀደላቸው በምንም ዓይነት መመዘኛ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሰሞኑን እየታየ ያለው ኢፍትሐዊነት መቆም አለበት፡፡

ባልደራስ በመባል የሚታወቀው የፖለቲካ ፓርቲ ሰላማዊ ሠልፍ ለማካሄድ ጠይቆ በመንግሥት መከልከሉ ይታወሳል፡፡ ከቀናት ልዩነት በኋላ ግን በኦሮሚያ ክልል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ሠልፍ ተደርጓል፡፡ የተቃውሞ ሠልፍ ቢሆን ኖሮ እንደማይፈቀድ የታወቀ ነው፡፡ ይህን መሰሉ አጉል ድርጊት አንፃራዊውን ሰላም ያደፈርሳል እንጂ አይጠቅምም፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት ግድም በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ገና ከመነሻው ተስፋ ተጥሎበት የሚሊዮኖችን ድጋፍያገኝ የቻለው፣ ኢፍትሐዊ የሆኑ ድርጊቶች ለዓመታት ሕዝቡን መቀመቅ ስለከተቱት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) ወደ ሥልጣን መንበሩ እንዲመጡ ባደረገው ለውጥ እስር ቤት ታጉረው የነበሩ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወገኖች ተፈተዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሽብርተኝነት ተከሰው የተወሰነባቸውና ክስ የተመሠረተባቸው እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ በመቀጠልም የምሕረት አዋጅ ወጥቶ ያለ ኃጢያታቸው የተወነጀሉ ጭምር እንዲሁ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ በመንግሥት ላይ ብረት ያነሱ ወገኖች ጭምር በለውጡ ተስፋ አድርገው ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪ ለመሆን አገር ውስጥ ከተዋል፡፡ ይኼንን የመሰለ ተስፋ ሰጪ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ቢቻል ኖሮ፣ በኢትዮጵያ ምድር ታሪክ እንደሚሠራ የብዙዎች እምነት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን አላስፈላጊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ የበርካቶች ሕይወት ተቀጥፏል፣ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡

መንግሥት በዚህ ጊዜ ሕግ እያስከበረ አገር የማረጋጋት ኃላፊነት እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ዕርምጃው ሕግን የሚፃረርና ቅራኔዎችን ለማባባስ በር የሚከፍት ከሆነ ግን ቆም ብሎ ማሰብ አለበት፡፡ የዘፈቀደ ውሳኔና አድሎአዊነት ከሕግ ጋር ተቃርኖ ከመፍጠሩም በላይ፣ የሕዝብን ድጋፍና አመኔታ ያሳጣል፡፡ በሥርዓት መምራት ሲቸግር ደግሞ ሌላ ዙር ቀውስ ይፈጠራል፡፡ አገርን በሥርዓት ለመምራት የሚቻለው፣ የሕግ የበላይነትን አሳማኝ በሆነ መንገድ በማረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ትናንት አምባገነንነትን ከጫንቃው ላይ አሽቀንጥሮ የጣለ ሕዝብ፣ ተመሳሳይ ድርጊቶችን ለመታገስ ፍላጎት እንደሌለው መታወቅ አለበት፡፡ የአገር ሰላምና መረጋጋትን የሚያውኩ ድርጊቶችን ወደ ጎን በማለት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መነሳት ሲገባ፣ አገርንና ሕዝብን ማዕከል ያላደረጉ የቡድን ፍላጎቶች ላይ መንጠልጠል የኢትዮጵያን ተስፋ ለማጨናገፍ ለሚፈልጉ ኃይሎች መሣሪያ መሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያን በአንድነት ቆመን፣ ተከባብረንና ተረዳድተን ከወደቀችበት አንስተን ታላቅ አገር እናድርጋት ሲባል፣ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ እናስተናግድ ማለት ነው፡፡ አንዱ የራሱን መብት ሲያስከብር የሌላውንም ማክበር እንዳለበት መረዳት መሆኑንም መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት ሥርዓት ለመፍጠር መሞከር ግን አደጋ ይጋብዛል፡፡ የሚያዋጣው ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ አገር ለመፍጠር በጋራ መሥራት ነው፡፡

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሐሳቦቻቸውን ለሕዝብ ለመሸጥ የሚችሉት፣ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ ብቻ ሲሆን እንደሆነ ሊረዱ ይገባል፡፡ ሐሳቦቻቸው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኙት ዴሞክራሲያዊ፣ ተዓማኒና ጠቃሚ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ የተለመደው የሴራና የአሻጥር መንገድ ላይ ለመጓዝ መሞከር፣ በአገርና በሕዝብ ህልውና ላይ መቆመር ነው፡፡ የአገሪቱ የተበላሸ የፖለቲካ ታሪክ አንዱን አሳዳጅ ሌላውን ተሳዳጅ እያደረገ በርካታ ዓመታት ባክነዋል፡፡ አሁን ግን ያንን የተበላሸ ታሪክ የሚቀለብስ ዕድል ሲገኝ፣ ተንከባክቦ ወደሚፈለገው ግብ ለማድረስ ለምን ይቸግራል? ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች ጠበቃ መሆን ይሻላል፡፡ ብልሹና ኢፍትሐዊ አሠራሮች እንዲወገዱ መታገል አስፈላጊ ነው፡፡ በቂም በቀል፣ በጥላቻና በክፋት የታጠረው የአገሪቱ የፖለቲካ አጉል ልማድ ገጽታውን በአስቸኳይ ቀይሮ ወደ ሥልጡን ግንኙነት ማምራት አለበት፡፡ ለዘመኑ የማይመጥን አድሎአዊነትና ራስ ወዳድነት ኢትዮጵያን ሥቃይዋን ከማብዛት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰፍቶ ለውይይትና ለድርድር በፍጥነት መዘጋጀት ይገባል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ለሰላማዊና ለሕጋዊ ፉክክር ዝግጁ ሲሆን፣ ኢፍትሐዊነትና ብልሹ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ በአግባቡ ለመምራትም ሆነ ለመመራት የሚቻለው አገር በሕግ የበላይነት ሥር ስትተዳደር ብቻ ነው፡፡

በሥራ ሒደት ስህተት ማጋጠሙ አይቀሬ ነው፡፡ የሚያበሳጨው ግን ስህተት በአንድ ዓይነት መንገድ ሆን ተብሎ ሲደጋገም ነው፡፡ ከስህተት ተምሮ የተሻለ ነገር ለመሥራት ተነሳሽነት ሊኖር ሲገባ፣ አድልኦና ኢፍትሐዊነት የሥርዓቱ መገለጫ እስኪመስል ድረስ በብዙ ቦታዎች ይታያል፡፡ ለጠባብ ፖለቲካዊ መስመር ብቻ ሲባል ግን አገርን ዘንግቶ ሥልጣንን የሁሉም ነገር ግብ ማድረግ ውድቀት እንጂ ዕድገት አያመጣም፡፡ ይህ ዓይነቱ ስህተት ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ የንፁኃን ወገኖቻችንን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ በርካቶችን ለአካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ዳርጓል፡፡ መጠኑ የማይታወቅ ከፍተኛ የአገር ሀብት አውድሟል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አሳዛኝና አሳፋሪ ስህተት በመማር አገርንና ሕዝብን መታደግ ይገባል፡፡ ከእያንዳንዱ ዜጋ ጀምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ስብስቦች ከስህተታቸው በመማር፣ ኢትዮጵያን የማዳን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከሥልጣን በፊት አገር ትቅደም፡፡ ይህ የተከበረ ሕዝብና ይህች ታሪካዊት አገር ሊከበሩ ይገባል፡፡ አስተዋዩና ጨዋው ሕዝብ መደመጥ አለበት፡፡ ፖለቲካ በጥበብ እንጂ በነሲብ አይመራም፡፡ በሴራ ጉንጎና የትም አይደረስም፡፡ በጨለማ ጥቁር ድመት ፍለጋ ዓይነት ከንቱ ድርጊት ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦችና ቡድኖች ከታሪክ ይማሩ፡፡ በታሪክ ያጋጠሙ ስህተቶች ታርመው ኢትዮጵያ መድመቅ ይኖርባታል፡፡ የወቅቱ የሕዝባችን ጥያቄ በሕግና በሥርዓት መመራት ነው፡፡ ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ፉክክር የሚኖረው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

ስሜታዊነት በምክንያታዊነት ካልተገራ አገርን ቀውስ ውስጥ እንደሚከትና ሕዝብን እንደሚያተራምስ ከበቂ በላይ ታይቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ረዥሙ የነፃነት ዘመን፣ ከሕዝቡ አንድ ላይ ለአገሩ ዘብ መቆምና መስተጋብር፣ ከኅብረ ብሔራዊ አንድነትና አሁን እየታየ ካለው መልካም አጋጣሚ መነሻነት አዲስ ታሪክ መሥራት ይገባል፡፡ ፖለቲከኞች ለሕዝብ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ፣ የኢትዮጵያ ትንሳዔ እንዲረጋገጥ፣ ሕዝባችን በሰላምና በአንድነት የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ፣ የሐሳብ ልዩነቶች በነፃነት እየተደመጡ አገር የዴሞክራሲ ጮራ እንድትሆን፣ ከአሳፋሪውና አሸማቃቂው ድህነት ለመገላገል፣ ኢትዮጵያዊያን ከስደት ይልቅ በአገራቸው በመረጡት ሥፍራ ሠርተው እንዲኖሩ፣ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ወለል ብሎ ተከፍቶ አማራጭ ያላቸው ጠንካራ ፓርቲዎች እንዲፎካከሩ፣ ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅሞች ይልቅ የአገር ጥቅም የበላይ እንዲሆን፣ ከተስፋ መቁረጥ ይልቅ ብሩህ ተስፋ እንዲኖርና ለመሳሰሉ ጠቃሚ አገራዊ ጉዳዮች ሲባል ለሕግ የበላይነት መስፈን መረባረብ ይገባል፡፡ ኢፍትሐዊነትና አድሎአዊነት ተወግደው ኢትዮጵያዊያን በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት መኖር አለባቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልበተኝነት ተወግዶ ሰላማዊና ሕጋዊ ፉክክር መለመድ አለበት፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዛ አገሩ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ወሳኝ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሥልጣን ላይ ያሉም ሆኑ ለሥልጣን የሚፎካከሩ ሕዝብን ያክብሩ፡፡ ድጋፍና ተቃውሞ መብት መሆናቸውን ይወቁ፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ይህንን መብት ያክብር!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እንዲሠማሩ የሚፈቅድ መመርያ እየተዘጋጀ ነው

በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ...