Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበፀጥታ ችግር ምክንያት በትግራይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሙሉ ለሙሉ ለማድረስ እንዳልተቻለ ተጠቆመ

በፀጥታ ችግር ምክንያት በትግራይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሙሉ ለሙሉ ለማድረስ እንዳልተቻለ ተጠቆመ

ቀን:

በትግራይ ክልል 94 የሰብዓዊ ዕርዳታ ማሰራጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው ድጋፍ ለመስጠት እየተሠራ ቢሆንም፣ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች አሁንም ድረስ የዘለቀ የፀጥታ ችግር በመኖሩ ሙሉ ለሙሉ የሰብዓዊ ዕርዳታዎች እየተሰራጩ እንዳልሆነ ተገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ማክሰኞ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በትግራይ ክልል ሲካሔድ የቆየው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተጠናቀቀ መባሉን ተከትሎ የመልሶ ማቋቋምና ሰብዓዊ ድጋፍን የማዳረስ ሥራ መጀመሩን በመግለጽ፣ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን የማዳረሻ መንገዶች መከፈታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና አሁንም ድረስ በተለይ በሕግ እየተፈለጉ ያሉ ሰዎች ተደብቀውባቸዋል ተብለው የሚገመቱ እንደ ተከዜ ወንዝና አካባቢው ያሉ ሥፍራዎች ግን የፀጥታ ችግሮች ስላሉባቸው፣ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች እንዳልተዳረሱ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ምክንያት የውጭ የረድኤት ድርጅቶች በአገሪቱ የሰብዓዊ ዕርዳታ መስመሮች አልተከፈቱም እንደሚሉ፣ ይህም ያለ ምንም ክልከላ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ጭምር ለመግባት ካላቸው ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ የውጭ ዕርዳታ ሰጪዎች ሁሉም ባይሆኑም የተወሰኑት የገቢያቸውና የኑባሬ ምንጫቸው ግጭቶችና ብጥብጦች በመሆናቸው፣ ለዚህ ግብዓት ይሆናቸው ዘንድም በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በመሸጥ ለመደመጥና ለመታየት እየሠሩ ነው ሲሉ ቃል አቀባዩ ተችተዋል፡፡

በትግራይ ክልል የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች እየተዳረሱና ሕዝቡም እየተረዳ እንዳልሆነ፣ የተለያዩ የውጭ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋማት ሲያስታውቁ ቆይተዋል፡፡

የኖርዌጂያን ረድኤት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ጃን ኤገላንድ ሰኞ ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ በትግራይ ክልል ግጭት ከተጀመረ 12 ሳምንታት ቢያስቆጥርም ይኼ ነው የሚባል የሰብዓዊ ሥራ እንዳልተጀመረ ገልጸዋል፡፡

‹‹የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች በክልሉ ማዕከላዊና ምዕራባዊ አካባቢዎች መድረስ አልቻሉም፡፡ ሁለት የስደተኛ ጣቢያዎችን ሙሉ ለሙሉ መድረስ አይቻልም፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ሊገቡባቸው የቻሉባቸው ጥቂት ሥፍራዎችም በዋና ዋና መንገዶችና በመቀሌ የታጠሩ ናቸው፡፡ የረድኤት ሠራተኞችም የሥልጣን ተዋረዱ በማይታወቅበትና በሚቀያየሩ የፈቃድ አሠራሮች ውስጥ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፤›› የሚለው የዋና ጸሐፊው መግለጫ፣ ‹‹ስደተኞችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች፣ ልጆችና ወንዶች እጅግ ተስፋ በሚያስቆርጥ አሳዛኝ ሆኔታ ውስጥ ያሉ ሲሆን፣ ያለ ዕርዳታና ጥበቃ ለብቻቸው እየማቀቁ ናቸው፤›› ይላል፡፡

በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉትና ሰኞ ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር የተወያዩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ድርጅት ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ እንዳሉት፣ በትግራይ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ የከፋ ከመድረሱ በፊት አፋጣኝ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ኮሚሽነሩ አክለውም የተወሰነ ዕርዳታ እየተሰራጨ ቢሆንም እጅግ ለሚያስፈልጋቸው ማዳረስ የግድ ያስፈልጋል ብለው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰላማዊው ዜጋ ዕርዳታ ማዳረስ ሲሆን፣ ይህም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩትን የኤርትራ ስደተኞችን ይመለከታል ብለዋል፡፡

ብሉምበርግ የተባለው ሚዲያ ኮሚሽነሩን ጠቅሶ እንዳስነበበው፣ 20,000 የኤርትራ ስደተኞች ከሕፃፅና ሽምልባ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ወጥተው የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡

ይኼንን አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ ዲና (አምባሳደር) ከኤርትራ ስደተኞች በጦርነቱ ተደናግጠው ወደ አዲስ አበባ የመጡ እንዳሉና አስቀድሞ በነበረ ስምምነትም ከኅብረተሰቡ ጋር ለመቀላቀል ስለተፈቀደላቸው መቀላቀላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና እነዚህን ስደተኞች ወደ መጠለያ ካምፖች የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...