የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ቀውስ አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ተናገረ፡፡ ቀደም ብሎ ተከስቶ የነበረው ፖለቲካዊ ቀውስ ወደ ጦርነት እንዳያመራ በተቻለው መጠን የመፍትሔ ሐሳብ ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሶ፣ የፈራው ደርሶ በትግራይ ከባድና አሰቃቂ ጦርነት መካሄዱንና አሳሳቢ የሆኑ የሰብዓዊ፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚዊ፣ አስተዳደራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውሶች መከሰታቸውን ገልጿል፡፡
‹‹በጦርነቱ በሁለቱም ወገን የተሠለፉት ታጣቂ ወገኖቻችን ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በሁለቱም በኩል ተሠልፈው ሰለባ የሆኑት ወገኖቻችን በመሆናቸው ጉዳቱ ክልላዊ ብቻ ሳይሆን አገራዊም ነው፡፡ በጦር ሜዳ በተሠለፉ ወገኖች ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ፣ በሲቪል ወገኖቻችን የደረሰው ሞትና አካል ጉዳትም ከባድ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በትግራይ በተለያዩ ከተሞች እየተነገሩ ያሉ መርዶዎች ጉዳቱ ምን ያህል ከባድ እንደነበር የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ከሞትና አካል ጉዳት ባሻገር ከቀዬአቸው የተፈናቀሉና ለረሃብ የተጋለጡ ወገኖች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ የፌዴራል መንግሥት እንደገለጸው፣ 700,000 ተፈናቃዮችን ጨምሮ ከሁለት እስከ አምስት ሚሊዮን ወገኖች የዕለት ደራሽ ፈላጊዎች ሆነዋል፡፡ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚለው ደግሞ፣ የዕለት ደራሽ የሚጠብቀው ሕዝብ ብዛት ከአራት እስከ አምስት ሚሊዮን እንደሆነ ነው፡፡ በዚህ አኃዝ ውስጥ በርካታ ሴቶች፣ ሕፃናትና ሽማግሌዎች ተካተዋል፤›› ብሏል፡፡
ትግራይ ውስጥ የነበሩ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች የሕክምና መሣሪያዎቻቸው እንደተዘረፉና እንደወደሙ የክልሉ ጊዜያዊ መስተዳደር አባላት መግለጻቸውን ጠቁሞ፣ ለእናቶች ወሊድና ለአስቸኳይ ሕሙማን ማመላለሻ የሚውሉ ከ400 በላይ አምቡላንሶች እንደተዘረፉና እንደወደሙ በተደጋጋሚ መነገሩን፣ በዚህም ምክንያትም ለክልሉ ነዋሪዎች ይሰጥ የነበረው የጤና አገልግሎት በእጅጉ እንደተስተጓጎለ አስረድቷል፡፡
ከአንድ እስከ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ መቅረታቸውንና ትምህርት ይጀመር ቢባል እንኳ የመማሪያ ቁሳቁሶች ስለወደሙ ከፍተኛ የጥገናና ቁሳቁሶችን የማሟላት ሥራ የሚጠይቁ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡
የጥገና ሥራ እየተከናወነ ቢሆንም እስካሁን የመብራት፣ የስልክ፣ የውኃና የባንክ አገልግሎት የማያገኙ በርካታ ወረዳዎችና አካባቢዎች እንዳሉና መሠረተ ልማቶችና አገልግሎቶች መቋረጣቸው በነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረሱ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
በተለይ የመብራትና የውኃ አገልግሎቶች ጊዜ የማይሰጡ የዕለት ተዕለት የህልውና መሠረቶች መሆናቸው ታሳቢ ሲደረግ፣ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ከባድ እንደሚያደርገውና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አንዳንድ መንገዶች የፈራረሱ ሲሆን በግንባታ ሒደት የነበሩም ግንባታቸው መቋረጡን መድረክ ገልጿል፡፡ ለመንገድ ግንባታ ይውሉ የነበሩ ከባድ ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎችም ገሚሶቹ ለጦርነቱ ተግባር እንዲውሉ ሲደረጉ፣ ገሚሶችም ተዘርፈው መወሰዳቸውንም አክሏል፡፡
በክልሉ የንግድ እንቅስቃሴ በእጅጉ ስለተዳከመ የሸቀጦች ዋጋ እጅግ መናሩን ጠቁሞ፣ ድሮውንም ቢሆን ከፍተኛ የዋጋ ንረት ይታይባቸው የነበሩ ሸቀጦች የጦርነቱ ተፅዕኖ ታክሎበት ዋጋቸው የማይቀመስ በመሆኑ፣ ሕዝቡን ለከፋ ችግር መዳረጉንና ይህንን የሸቀጦችን ችግር በመቅረፍ ረገድ አስተዋጽኦ ያደርጉ የነበሩ አምራች ድርጅቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ማምረት ማቆማቸውን ገልጿል፡፡
በትግራይ በአምራችነት ተሰማርተው የነበሩ 1,000 አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶችና 80 የሚሆኑ ትልልቅ ድርጅቶች ሥራ በማቋረጣቸው ባለቤቶቻቸውና ሠራተኞቻቸው ለችግር መዳረጋቸውን፣ በእነዚህ ድርጅቶች ይሠሩ የነበሩ ከ350 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ዕጣ ፈንታም አሳሳቢ መሆኑን፣ በውጭ ዜጎች ተጀምረው ማምረት ጀምረው የነበሩ በግንባታ ላይ የነበሩ ድርቶች ሁሉ አሁን ሥራ ማቋረጣቸውን አብራርቷል፡፡
በትግራይ ክልል ከደረሰው ማኅበራዊና ኢኮኖሚዊ ቀውስ በተጨማሪ፣ የመንግሥት መዋቅሮች በመፈራረሳቸው ሕዝቡ ከመንግሥት ሲያገኝ የነበረው አገልግሎት በመቋረጡ ለከፋ ችግር ተዳርጓል፡፡ ከተሞችም ሆኑ የገጠር ቀበሌዎች በጠራራ ፀሐይ ዝርፊያ የሚያካሂዱባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን፣ ከዝርፊያ ባሻገር ሕይወት የማጣትና አስገድዶ የመደፈር ሰለባዎች የሆኑ ወገኖች በርካቶች መሆናቸውን በክልሉ አስቸኳይ አዋጅ ታውጆ ለትግበራው ኮማንድ ፖስት ቢቋቋምም ኮማንድ ፖስቱ የፖሊስን ሥራ ተክቶ ሊሠራ ስላልቻለ፣ የሚደርሰውን ሰቆቃ መቋቋም አለመቻሉን ገልጿል፡፡ የመንግሥት አገልግሎት የሚሰጡ መሥሪያ ቤቶች ገና ስላልተቋቋሙ ሕዝቡ የዕለት ተዕለት አገልግሎት አግኝቶ መንቀሳቀስ አለመቻሉንም ጠቁሟል፡፡
ጦርነቱ በሕዝቡ ላይ ያሳደረው ሌላው ችግር ከባድ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ማስከተሉን የጠቆመው መድረክ፣ ሕዝቡ ሳይመክርበትና ሳይወስንበት የተጀመረው ድንገተኛ ጦርነት ዓይቶት ወደማያውቅ ከፍተኛ ችግር ስለከተተው፣ መውጫ ቀዳዳው ጠፍቶ ከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ ይገኛል፡፡ በማኅበረሰብ ደረጃ የሥነ ልቦና መዛባት (Trauma) ገጥሞት ይገኛል፡፡ እንዲህ ያሉ ሰቆቃዎች በማኅበረሰብ ደረጃ የሚከሰቱት ሕዝብ ባልተጠበቀው ሁኔታ ዕልቂት መፈናቀልና ውድመት ሲያጋጥም ነው፡፡ ይህ ችግር በጦርነቱ ቀጣና በነበሩት የትግራይ ተወላጆች ብቻ ሳይሆን የጥፋት ቡድን ተባባሪ እየተባሉ በገፍ በሚፈረጀው በመሀል አገር ባለው የክልሉ ተወላጅ ጭምር መሆኑን ገልጿል፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ የደረሰው የዜጎች መፈናቀልና የሰብዓዊ ዕርዳታ መስተጓጎል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለረሃብ አደጋ ያጋለጠ በመሆኑ ሰፊ አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ሆኗል፡፡ እስካሁን የዕለት ደራሽ ምግብ፣ ውኃና የሕክምና አገልግሎት ያልደረሳቸው ወገኖች በርካታ መሆናቸው መገንዘቡንና መንግሥት ይህን ለማድረግ እየሞከረ ቢሆንም፣ ካለው የችግሩ ስፋት አኳያ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል፡፡
በመሆኑም አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕርዳታዎችን በማሰባሰብ ሰፊ ሥራ መሥራት እንዳለበትና ዕርዳታው ያልደረሳቸው አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑና ወገኖችን ከረሃብ እንዲታደጉ ጠይቋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖች እጅግ በርካታ መሆናቸውንና ወገኖች ሲፈናቀሉ የንግድ ድርጅታቸውና የቤት ቁሳቁሶቻቸው ሁሉ የተዘረፉ፣ የወደሙ በመሆኑ፣ በአስቸኳይ የመልሶ መቋቋም ሥራ ተከናውኖ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡ በዚህ ረገድም ለማቋቋሚያ የሚያስፈልገው ሀብት እጅግ ብዙ ስለሚሆን ከወዲሁ የሀብት ማሰባሰቡ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አክሏል፡፡
በጦርነቱ ሒደት የሴቶች ጥቃትና መደፈር ጨምሮ በርካታ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ ነዋሪዎች አቤቱታ እያሰሙ መሆኑን ጠቁሞ፣ ጉዳዩ ገለልተኛ በሆነ ወገን ተጣርቶ አጥፊዎች የሚቀጡበትና ተጎጂዎቹ የሚካሱት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
የወደሙት መሠረተ ልማቶች እጅግ በርካታ በመሆናቸው ሰፊ የመልሶ ግንባታ ተግባር መከናወን ግድ እንደሚልና የተቀናጀ ዕቅድ ወጥቶለት በተቀመጠ ጊዜ መፈጸም እንዳለበት ተናግሯል፡፡ ጉዳቱ ከፍተኛ ስለሆነም ከአገር ሀብት በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ማሰባሰቡ የግድ የሚል መሆኑንም አክሏል፡፡
በክልሉ ሲካሄዱ የነበሩ የንግድ፣ የምርትና የአገልግሎት ሥራዎች ስለተስተጓጎሉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ወደ ነበሩበት የሚመለሱበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት፣ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩትን ወገኖች ከማበረታታት ጀምሮ ሥራ ለመጀመር የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ የቁሳቁስና የቴክኒክ ዕርዳታ የሚያከናውን ‹‹ግብረ ኃይል›› በማቋቋም በአጭር ጊዜ ወደ ተግባር የሚገቡበት ሁኔታ እንዲያመቻች ጠይቋል፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አሁን እየተንቀሳቀሰ ያለው በተወሰነ የክልሉ አካባቢዎች ብቻ መሆኑን የጠቆመው መድረክ፣ በተለይ የትግራይ ምዕራባዊ ዞንና ከፊል ደቡብ ዞን ‹‹የአማራ ክልል ግዛቴ ነው›› በሚል የተቆጣጠረው በመሆኑ በአካባቢው ያሉ የሕዝቡ እንቅስቃሴዎች የተገደቡ ሆነዋል፡፡
እነዚህ አካባቢዎች የአስተዳደር ወሰናቸው ወይም ማንነታቸው ይታወቅ የሚል የሕዝብ ጥያቄ ካለ ሕገ መንግሥቱንና አግባብነት ያላቸው አገራዊ ሕጎችን ተከትሎ በዴሞክራሲያዊ አግባብ የሚፈጸም እንጂ እንዲሁ በኃይል ከተከናወነ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት ስለማያስከትል፣ መንግሥት ይህን ችግር በመፍታት ረገድ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
የአማራ ክልላዊ መንግሥትም ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብን ተከትሎ እስኪቋጭ ድረስ እንዲታገስና ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነትን እንዲወጣ አሳስቧል፡፡
በክልሉ ያለው ያለመረጋጋት መንፈስ አንዱ ምንጭ የውጭ ኃይል በተለይም ኤርትራ ጦር እስካሁን በክልሉ መገኘቱ ጠቁሞ፣ ሕዝቡ በዚህ ኃይል ከፍተኛ ግፍ ይፈጸምብናልና በሚል ይውጣልን የሚል ስሞታ እያሰማ ባለበት ሁኔታ፣ ‹‹የማንም ውጭ ጦር በምድራችን የለም›› የሚል መግለጫ እየተሰጠ በመሆኑ፣ ይበልጥ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ እንዳገኘው መድረክ ገልጿል፡፡ ይህ ጉዳይ እውነት አይደለም የሚል ክርክር ካለም ገለልተኛ ቡድን ቢያጣራውና ግኝቱን ቢቀርብ ተገቢ እንደሚሆንና መንግሥትም አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠይቋል፡፡