Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትካርድ የበዛበት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

ካርድ የበዛበት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

ቀን:

ከተጀመረ አሥረኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳሳዊ ከሆነው ክህሎት ይልቅ አሉታዊ ጎኖቹ እየጎሉ በዳኞች በሚመዘዙ ካርዶች መነጋገሪያ ሆኖ ይገኛል፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት ውድድሮች በተመረጡ ስታዲየሞች እንዲከናወን ከመደረጉ ጎን ለጎን በተለይ የፕሪሚየር ሊጉ እያንዳንዱ ጨዋታ በሱፐር ስፖርት አማካይነት ቀጥታ ሥርጭት እንዲተላለፍ መደረጉ፣ በጨዋታው ሒደት ውስጥ አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ እንቅስቃሴዎች በመልሶ ዕይታ የሚረጋገጥበት ዕድል ስላለ የሊጉ አሉታዊ ጎኖች የአደባባይ ሚስጥር ሆነዋል፡፡

ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች አካባቢ ከዳኝነት ጋር ተያይዞ ውጤት የሚያስቀይሩ ክስተቶች ሲፈጠሩ የሚስተዋሉ ግርግሮችና ሁከቶች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችሉ መልኩ ተወግደዋል፡፡ ቡድኖች እንደ ቀድሞ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ የሚያደርጉት የተዟዙሮ ጨዋታዎች ቀርተው በተመረጡ ውስን ከተሞች ላይ ተቀምጠው መርሐ ግብሮቻቸውን እያከናወኑ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ስፖርታዊ ጨዋነትን ከማስፈን አኳያ በቡድን አመራሮችና ተጨዋቾች እንዲሁም ብዙ ጊዜ ከአቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ የጨዋታ ዳኞች በፈጠሯቸው የዳኝነት ክፍተቶች ምክንያት ዛሬም አላስፈላጊ መገፋፋቶችና ውዝግቦች መፈጠራቸው አልቀረም፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እግር ኳሱን በበላይነት የሚያስተዳር አካል እንደመሆኑ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ የተለያዩ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ እንደ ዕድል ሆኖ ከከፍተኛው (ሱፐር) ሊጉና ብሔራዊ ሊጉ በተለየ በሱፐር ስፖርት አማካይነት ‹‹ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ›› ተብሎ በቀጥታ ሥርጭት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለብዙ የዓለም አገሮች እንዲደርስ መደረጉ በተለይ ባለ ክህሎት ወጣት ተጨዋቾች በታላላቅ ሊጎች የመታየት ዕድል እንደሚፈጠርላቸው የብዙዎች እምነት ነው፡፡

ይሁንና በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ወጣቶቹን ጨምሮ ተጨዋቾች የሚያሳዩት ባህሪይ ስፖርቱ ከሚጠይቀው ዲሲፕሊን ጋር ተያይዞ ዕድሎችን እንዳያሳጣቸው የሚሠጉ አልጠፉም፡፡ ሜዳ ላይ በሆነው ባልሆነው ዳኞች የሚወስኗቸው ውሳኔዎችን (የብቃታቸው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ) ተከትሎ የቡድን አመራሮችን ጨምሮ የተጨዋቾች ከበባና ወከባ ዘርፉን አሳሳቢ እያደረገው ይገኛል፡፡

አስረኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብሩን ያጠናቀቀው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ በጨዋታ ዳኞች የተመዘዙ ቢጫና ቀይ ካርዶች ከወትሮ በተለየ መልኩ ከቡድን አመራሮችና ተጨዋቾች አልፎ የሕክምና ባለሙያተኞች ጭምር ያካተተ ሆኖ ታይቷል፡፡ ባለፈው ሳምንት አዳማ ከተማና ሐዋሳ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ የአዳማው የሕሐሕሕክምና ባለሙያ ዮሐንስ ጌታቸው የቅጣት ሰለባ የሆኑት በዚሁ ጨዋታ ላይ ፈጽመዋል በተባለው ሰዓት በማቃጠል የዲሲፕሊን ጥፋት ነው፡፡

በፌዴሬሽኑ የሥነ ምግባር ደንብ መሠረት አሥር ሺሕ ብርና የሦስት ጨዋታ ቅጣት የተላለፈባቸው የሕክምና ባለሙያው አቶ ዮሐንስ፣ አዳማ ከተማ ተጋጣሚውን ሐዋሳ ከተማን ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ማለትም 86ኛው ደቂቃ ድረስ 3 ለ 1 እየመራ በሚገኝበት ሰዓት፣ የአዳማ ተጨዋች ጉዳት ሲደርስበት የጨዋታው ዋና ዳኛ የሕክምና ባለሙያው ወደ ሜዳ ገብተው የመጀመርያ የሕክምና ዕርዳታ አድርገው ተጨዋቹን ከሜዳ ውጪ አስወጥተው ተገቢውን ሕክምና እንዲያደርጉ ሲጠየቁ አላስፈላጊ ጊዜ ሲያባክኑ በቢጫ ያስጠነቅቋቸዋል፡፡ ይሁንና የሕክምና ባለሙያው አሁንም የዳኛውን ቢጫ ችላ በማለታቸው በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ እንዲወጡ ማድረጋቸው ምናልባትም ይህ የዳኛው ውሳኔ የሕክምና ባለሙያን በሚመለከት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመርያ ክስተት ሊያደርገው እንደሚችል ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡

በሳምንቱ ጨዋታ የዳኞች ቢጫና ቀይ ካርድ ሰለባ ከሆኑ ተጨዋቾች መካከል የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ኃይለ ማርያም ሻንቆን ጨምሮ በርካቶችን ሰለባ ያደረገ ነበር፡፡ በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ግብ ጠባቂዎች የቅጣት ሰለባ ከሚሆኑባቸው ጥፋቶች መካከል፣ ባልተፈቀዱ ቦታዎች ኳስ በእጅ በመያዝ የግብ ዕድሎችን ማበላሸት የሚለው ይጠቀሳል፡፡

በቡድን አመራሮችና ተጨዋቾች የሚፈጸሙ የዲሲፕሊን ጥፋቶች እንደተጠበቁ ሆኖ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለእነዚህና መሰል ጥፋቶች መነሻ የሚሆኑ በተለይም ዳኝነት ላይ የሚስተዋለውን የአቅም ውስንነት፣ ወቅታዊ የሆኑ የዳኝነት ሕጎች ላይ የሙያ ማሻሻያ መስጠት ካልቻለ ከዚህም የከፋ ሊያስከትል የሚችልበት ዕድል እንዳለ የሚናገሩ አልጠፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...