ባደጉና ባዳጊ አገሮች ከሚኖሩት 7.6 ቢሊዮን ሰዎች መካከል 80 በመቶ ያህሉ የባህል መድኃኒቶች ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ተጠቃሚዎች የሚገኙት ባዳጊ አገሮች መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ከዓመታት በፊት ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡
ባህላዊ መድኃኒቶችን ከሚያዘወትሩት አገሮች መካከልም ቻይና፣ ህንድና ናይጀሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የባህል መድኃኒቶችን ለገበያ በማብቃት ትልቅ ሥራ መሥራታቸው ይነገራል፡፡ በአፍሪካ ናይጀሪያና ጋና የባህል መድኃኒት ከዘመናዊ መድኃኒት ጋር አቀናጅተው በመጠቀም ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ሲዳሰስ ከአጠቃላዩ ዘዝሐሕሕዝብ መካከል 80 ከመቶ ያህሉ የባህል መድኃኒት ተጠቃሚ ሆኖ እንደሚስተዋል ነው፡፡
መንግሥትም ከሌላው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ለባህል መድኃኒት ትኩረት ሰጥቶ ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ከሚታዩትም እንቅስቃሴዎች መካከል በመሠረታዊ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ውስጥ የባህል መድኃኒት ጉልህ ድርሻ እንዲኖረውና የበኩሉንም አስተዋኦ እንዲያበረክት ማድረግ ይገኝበታል፡፡
ለባህል መድኃኒት አዋቂዎች ማኅበር ሕጋዊ ዕውቅና፣ ለማኅበሩ መገልገያ የሚሆን ቢሮና ለአባላቱም ከዓምና ጀምሮ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠቱ ከእንቅስቃሴዎቹ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በተከታታይ ከተሰጡት ሥልጠናዎች መካከል ከጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት እየተካሄደ ያለው ሁለተኛው ዙር ሥልጠና ይገኝበታል፡፡ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ያለውና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች በተሳተፉበት በዚህ ዓይነት ሥልጠና የባህል መድኃኒት በኢትዮጵያ፣ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት፣ የባህል መድኃኒት ዕውቀትና የአዕምሯዊ ንብረት አያያዝ በሚሉ ርዕሶች ላይ ውይይት ይካሄዳል፡፡
ከዚህም ሌላ የባህል መድኃኒት የአመዘጋገብ ሒደት፣ ጤናና ምግብ ያላቸው ግንኙነት፣ መድኃኒትነት ያላቸውን ዕፀዋት መንከባከብና እንዴት መተካት እንደሚቻል፣ እንዲሁም የሕክምና ሥነ ምግባር ላይ ትኩረት ያደረጉ ትምህርት አዘል ግንዛቤ ማስጨበጫዎች ይሰጣሉ፡፡
ወ/ሮ ፍሬሕይወት ተካ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የባህላዊና ዘመናዊ መድኃኒት ምርምር ዳይሬክቶሬት ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደ ኃላፊዋ አነጋገር የዓለም አገሮች የመድኃኒት ብግርነትን ለመከላከል ወደ ተፈጥሯዊ መድኃኒት እየተመለሱ ናቸው፡፡
ዳይሬክቶሬቱ ለ40 ዓመታት ያህል ከባህል መድኃኒት አዋቂዎች ጋር በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን፣ በዚህም የባህል መድኃኒት አዋቂዎች በጤና ሥርዓት ውስጥ የበኩላቸውን አስታዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማስቻሉን ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሐጂ ሼክ አሊ አደም ስለዚሁ ጉዳይ በስልክ ጠይቀናቸው፣ ‹‹በኢትዮጵያ የባህል መድኃኒት ከ3,000 ዓመት ወይም ከአክሱም ዘመነ መንግሥት በፊት ሲሠራበት የኖረና ከኬሚካል የፀዳ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የባህል መድኃኒት እኩሉ በሚጠጣና በሚዋጥ ከፊሉ ደግሞ በሚቀባ እና በማሽተት የሚወሰድ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸው፣ ‹‹እሬት›› ብቻ 400 ዓይነት በሽታዎችን የመፈወስ አቅም እንዳለው በተለይ የአጥንት መሸርሸርን፣ ስኳር በሽታን፣ ደም ግፊትን እንደሚፈውስ ስንፈተ ወሲብንም እንደሚከላከል አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የባህላዊና ዘመናዊ መድኃኒት ዳይሬክቶሬት ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ከገባው ጥናት ለመረዳት እንደተቻለው ደግሞ፣ ለተለያዩ በሽታዎች ፍቱን ናቸው ተብለው የተለዩ 35 የባህል መድኃኒቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል 13ቱ ልዩ ልዩ የባህል መድኃኒቶች በላቦራቶሪና በእንስሳት ላይ ሙከራ ተደርጎባቸዋል፡፡
የላቦራቶሪ ሙከራ ከተደረገባቸውና ለሰው ከሚውሉ የባህል መድኃኒቶች መካከል የደም ግፊትን ለመቆጣጠር የሚውለውና በተለምዶ ‹‹ሽፈራው›› (ሞሪንጋ) እየተባለ የሚጠራው ዕፀዋት፣ ጦስኝና የጦስኝ ዘሮች እንዲሁም ለቆላ በሽታ ሕክምና ይውላሉ የተባሉት የጠጅ ሳርና ነጭ አዝሙድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በእንስሳት ላይ ሙከራ ከተደረገባቸው ውስጥም፣ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ጠቃሚ የሆነውን፣ የእንስሳት ቆዳ ጥራት በመቀነስ የሚታወቀውን የእንስሳት ጥገኛ በሽታን ማጥፋት የሚያስችሉ የጠጅ ሳርና የባህር ዛፍ ዘሮችም ይገኙበታል፡፡
ለሰው የሚውሉ የባህል መድኃኒቶች በላቦራቶሪ ተሞክረው ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ወይም ፍንጭ የታየባቸው ሲሆን፣ ለእንስሳት ተብለው የተሞከሩ ዕፀዋት ግን ውጤታማነታቸው ወይም ፈዋሽነታቸውን መረጋገጡ ይፋ ከሆነው ጥናት ለመረዳት ተችሏል፡፡