የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2012 በጀት ዓመት አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ክንውኖችን የሚያመለክተውን ሪፖርቱን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህ ዓመታዊ ሪፖርት በተለይ የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት የ2012 አጠቃላይ አፈጻጸምና የገንዘብ እንቅስቃሴን የተመለከተው መረጃ ተጠቃሽ ነው፡፡
ባንኮችና የብድር ዕድገት
በሪፖርቱ መሠረት፣ 18ቱም ባንኮች በ2012 የሒሳብ ዓመት የሰጡት አዳዲስ ብድሮች ከቀደመው ዓመት በ14.8 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ 271.8 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድርም ለቀዋል፡፡ ከአዳዲስ ብድሮቹም 44.7 በመቶው በግል ባንኮች የተሰጠ ሲሆን፣ ቀሪው 55.3 በመቶ በመንግሥት ይዞታ ሥር ባሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል የተሰጡ መሆኑ ታውቋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከተሰጠው አጠቃላይ ብድር ውስጥ 17.9 በመቶ የሚሆነው ለማዕድን፣ ለኃይል፣ ውኃና ለሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ሲሆን፣ 15.9 በመቶው የሚሆነው ደግሞ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የተለቀቀ ብድር መሆኑን ያመለክታል፡፡ 14.1 በመቶ ለዓለም አቀፍ ንግድ፣ 13.4 በመቶ ለአገር ውስጥ ንግድ፣ ለ9.4 በመቶ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ 9.2 በመቶ ለግብርና እንዲሁም 9.2 በመቶ ለትራንስፖርትና መገናኛ የብድር አቅርቦት አግኝተዋል፡፡ የቀረው የብድር መጠን ደግሞ ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የቀረበ መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
ሀብት አሰባሰብና ትሪሊዮን ብር የተሻገረው ቁጠባ
2012 በጀት ዓመት መገባደጃ ላይ ከፋይናንስ ተቋማቱ በቁጣባ፣ በዕዳና በብድር መልክ የተሰበሰበው ጠቅላላ የሀብት መጠን የታየበት ዕድገት 0.1 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በዚህ የዕድገት ምጣኔ መሠረት የተሰበሰበው ጠቅላላ የሀብት መጠን 333.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
የባንኩ ዘርፍ ተቀማጭ ዕዳ መጠን በቅርንጫፍ ማስፋፊያ አፈጻጸሙ በጉልህ ታግዞ የ15.8 ዓመታዊ ዕድገት በማሳየት 1.0 ትሪሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የቁጠባ ተቀማጭ መጠኑ በ20.9 በመቶና የመጠባበቂያ ቁጠባው የ13 በመቶ ዕድገት ማሳየቱም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ ሆኖም የጊዜ ገደብ ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ግን በ1.1 በመቶ ቀንሷል፡፡ ከአጠቃላይ ተቀማጭ ቁጠባ 56.6 በመቶ፣ ከመጠባበቂያ ቁጠባ 34.2 በመቶ እንዲሁም የጊዜ ገደብ ተቀማጭ 9.2 በመቶውን ድርሻ ይዘዋል፡፡
በአጠቃላዩ የሀብት ማሰባሰብ ረገድ የግል ባንኮች ድርሻ ሲታይ 714 አዳዲስ ቅርንጫፎች መከፈታቸውን ተከትሎ በቀደመው ዓመት ከነበረበት 39.6 በመቶ ወደ 42.6 በመቶ አድጓል፡፡ መጠነ ሰፊ የቅርንጫፍ ማስፋፊያ በማድረጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻውን ከአጠቃላይ ተቀማጩ 57.3 በመቶን ማሰባሰብ ስለመቻሉ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
ብዙዎቹ ባንኮች ተቀማጭና ብድር በማሰባሰብ ረገድ በብቁ መልኩ የተንቀሳቀሱ በመሆናቸው፣ ከባንክ ሥርዓቱ በብድር ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራው ያን ያህልም ጉልህ ያልሆነ የገንዘብ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አጠቃላይ ያለባቸው የብድር መጠን በቀደመው ዓመት ከነበረው 72.2 ቢሊዮን ብር፣ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ምክንያትነት ከፍ ብሎ 80 ቢሊዮን ብር ላይ መቆም ችሏል፡፡ ለአጠቃላይ ብድሩ የአገር ውስጥ ምንጮች 85 በመቶ፣ የውጭ አገር ምንጮች 15 በመቶውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ በ2012 በጀት ዓመት የተጣራው ብድር 8.3 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ከዚህም 68.2 በመቶ ከአገር ውስጥ 31.8 በመቶ ከውጭ ምንጮች የተገኘ ነው፡፡
በተጨማሪም በ2012 በጀት ዓመት ባንኮች 183.3 ቢሊዮን ብር በ17.2 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ገንዘብ መጠን መሰብሰብ ችሏል፡፡ 50.7 በመቶውን የግል ባንኮች ከሰጡት ብድር የተሰበሰበ ነው፡፡
የብድር ክምችት
የአገሪቱ ባንኮች የብድር አሰባሰብን በተመለከተ እንደተጠቀሰው፣ በባንኮቹ የተከማቹ ብድሮች በ20.4 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑን ነው፡፡ በሰኔ ወር 2012 መጨረሻ ላይ የተከማቸው የብድር መጠን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ስለመሆኑም ያመለክታል፡፡ ከተከማቸው ብድር ውስጥ 29.5 በመቶውንና የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የማዕድን፣ የኃይልና ውኃ ሀብት ዘርፍ ሲሆን፣ ኢንዱስትሪ 21.5 በመቶ፣ ዓለም አቀፍ ንግድ 13 በመቶ፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን 13 በመቶ፣ የአገር ውስጥ ንግድ 8.5 በመቶ፣ ትራንስፖርትና መገናኛ 6.7 በመቶ እንዲሁም ሌሎች 9.6 በመቶ ድርሻ ይዘው ይከተላሉ፡፡ ከተከማቹ ብድሮች ውስጥ የግሉ ዘርፍ ድርሻ 484.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላላው ከተከማቹ ብድሮች ውስጥ የ47 በመቶውን ድርሻ ይዟል፡፡ ይህ ከግሉ ዘርፍ የሚጠበቀው የተከማቹ ብድር የ28.3 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ያሳየ መሆኑን ከሪፖርቱ መገንዘብ ተችሏል፡፡ ቀሪውና የ53 በመቶ ድርሻ ከመንግሥት ተቋማት የሚጠበቅ የተከማቸ ብድር ነው፡፡
የብሔራዊ ባንክ ፋይናንስ ተኮር ተግባራት
ሪፖርቱ ከዳሰሳቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ የብሔራዊ ባንክን ፋይናንስ ተኮር ተግባራትን የሚመለከተው ይገኝበታል፡፡ በዚህም መሠረት ብሔራዊ ባንክ እስከ ሰኔ 2012 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ከማዕከላዊ መንግሥት የሚፈልገው የገንዘብ መጠን ከቀደመው 2011 በጀት ዓመት የ18.3 በመቶ ዕድገት አሳይቶ፣ 230.2 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህም 86.5 በመቶ በመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ፣ እንዲሁም 15.5 በመቶ በቀጥተኛ ቅድመ ክፍያ መልክ የተመዘገበው ነው፡፡ ለማዕከላዊ መንግሥት የሚቀርበው ቅድመ ክፍያ ማደጉና ይኼውም ወደ ቦንድ የተቀየረ በመሆኑ በ2012 በጀት ዓመት ከነበረው በ83.4 በመቶ ቀንሷል፡፡
በተመሳሳይም ብሔራዊ ባንክ ከልማት ባንክ የሚጠብቀው የተከፋይ መጠን ደግሞ በ11.5 በመቶ ዕድገት አሳይቶ 58.1 ቢሊዮን ብር መድረሱንም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
የመንግሥት ተቀማጭና የፋይናንስ ተቋማት በብሔራዊ ባንክ ያላቸው መጠበቂያ ክምችት ደግሞ በ38.5 በመቶ ዕድገት በማሳየት ሰኔ 2012 መጨረሻ ላይ 142.6 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ተጠቅሷል፡፡ ይኼውም የፋይናንስ ተቋማት ቁጠባን የ36.8 በመቶ ዕድገትና የ53.4 በመቶ የመንግሥት ቁጠባ ዕመርታን መሠረት ያደረገ መሆኑንም አመላክቷል፡፡
የፋይናንስ ገቢዎች ልማትና የግምጃ ቤት ሰነድ ጨረታ
የመንግሥት ወጪዎችን ለመሸፈንና በባንኩ ሥርዓት ውስጥ ከመጠን ያለፈ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ለመቋቋም በኢትዮጵያ ውስጥ የፋይናንስ ግብይትና የአክሲዮን ግብይት ብቸኛ መንገዶች የግምጃ ቤት ሰነዶችና የመንግሥት ቦንዶች መሆናቸውን ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡
በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት ለሽያጭ የቀረበው የግምጃ ቤት ሰነድ ምንም እንኳን የፍላጎት መጠኑ 242.16 ቢሊዮን ብር የነበረ ቢሆንም፣ የ10.7 ቢሊዮን ብር ወይም 4.6 በመቶ ብልጫ አሳይቶ 231.49 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በዚህም መሠረት በዓመቱ ውስጥ የተሰጠው የግምጃ ቤት ሰነድ መጠን 234.84 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ በመንግሥት በኩል ከታኅሳስ 2013 ጀምሮ የግምጃ ቤት ሰነድ ግብይት ወደ ገበያ መር የግምጃ ቤት ጨረታ ውድድራዊ ግብይትና የግምጃ ቤት ሰነድ አክሲዮኖች ወደ ሦስት ዓመት ቦንድነት እንዲቀየሩ ባወጣው መመርያ መሠረት፣ የወቅቱ ተከፋይ የግምጃ ቤት ሰነድ መጠን በ82.8 በመቶ ቀንሶ፣ 23.7 ቢሊዮን ብር እንደደረሰም ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡
በገበያው ላይ የተከሰቱ ለውጦችን ተከትሎ የግምጃ ቤት ሰነድ ጨረታ የወለድ ምጣኔ ስለመወሰኑ የሚያመለክተው ሪፖርት፣ በግምጃ ቤት ሰነድ ግብይት ላይ የባንኮች ተሳትፎ ጉልህ መሻሻል የታየበት እንደነበር ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት ከአጠቃላዩ የግምጃ ቤት ሰነዶች ተከፋይ የንግድ ባንኮች ድርሻ በ23.6 በመቶ 5.60 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ባንክ ያልሆኑ ተቋማት 76.4 በመቶው ወይም 18.12 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡
የግምጃ ቤት ሰነድ አማካይ ትርፍ ምጣኔ የ176.16 በመቶ ከፍተኛ ዓመታዊ ዕድገት አስመዝግቦ፣ ከ1.741 በመቶ ወደ 4.808 በመቶ መሸጋገር የግምጃ ቤት ሰነድ ገበያ ወደ ውድድራዊ የጨረታ ግብይት ሥርዓት ያደረገው ሽግግር ተጠቃሽ ውጤት ሆኖ እንደሚታይ ያመለክታል፡፡ ከፍተኛው የትርፍ ተመላሽ በ5.131 በመቶ ምጣኔ በ28 ቀን የግምጃ ቤት ሰነድ እንዲሁም ዝቅተኛ የሆነው የ4.294 በመቶ ምጣኔ በ91 ቀናት የግምጃ ቤት ሰነድ ላይ የተመዘገበ ነበርም ብሏል፡፡
የፋይናንስ ዘርፍ ዕድገት
የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት አቋም የሚያመለክተው የሪፖርቱ ክፍል የአገሪቱ የባንኮች ቁጥር 18 የደረሰ መሆኑንና ከእነዚህም 16 የግልና ሁለት የመንግሥት መሆናቸውን በመጠቆም ይጀምራል፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቁጥር 18 መድረሱን፣ ከእነዚህ ውስጥም አንዱ መንግሥታዊ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 17ቱ የግል መሆናቸውንም ያሳያል፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ቁጥር በዓመቱ መጨረሻ ላይ 41 እንደነበሩ በመግለጽ፣ ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ አሥራ አንድ የመንግሥት፣ 13 የግልና 17 መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተያዙ መሆኑን አመልክቷል፡፡
በ2012 ሒሳብ ዓመት 947 አዳዲስ ቅርንጫፎችን የከፈቱት እነዚህ ተቋማት የባንክ ቅርንጫፎች ቁጥር በቀደመው ዓመት ከነበረው 5,564 ቁጥራቸው፣ ወደ 6,500 ከፍ ሊል ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ይህ የባንኮች ቅርንጫፎች ዕድገት ማዕከላዊ ስታትስቲክስ በ2012 የሕዝብ ቁጥር ትንበያ መሠረት 102,2 ሚሊዮን እንደሚሆን፣ የሚያሳይ በመሆኑ፣ በዚህ የሕዝብ ቁጥር ሥሌት መሠረት የባንክ ቅርንጫፎች ከሕዝብ ቁጥር አንድ ቅርንጫፍ 15,702 ሕዝብ መሆኑን የሚያመለክት ሆኗል፡፡ እንደ ሪፖርቱ 34.1 በመቶ ገደማ የሚሆነው የባንኮች ቅርንጫፎች በአዲስ አበባ የሚገኙ ናቸው፡፡
ከቅርንጫፎች ማስፋፋት ጋር በተያያዘ በ2012 በጀት ዓመት ከፍተኛውን ቅርንጫፎች በመክፈት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀዳሚ ሲሆን፣ በዓመቱ ውስጥ 247 ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ 226 አዋሽ ባንክ 58 ቅርንጫፎችን በመክፈት ተከታይ ሆነዋል፡፡ ኅብረት ባንክ 57፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ 47፣ ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ 39፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክና አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ እያንዳንዳቸው 37 ቅርንጫፎችን ከፍተዋል ብሏል፡፡
በዚህም ከአጠቃላዩ የቅርንጫፎች ስብጥር የግል ባንኮች ድርሻ በቀደመው ዓመት ከነበረው 69.7 በመቶ መጠነኛ ዕድገት አሳይቶ፣ 70.5 በመቶ ደርሷል፡፡ ኢንዱስትው ያለው ጠቅላላ ካፒታል በ11.2 በመቶ አድጎ በሰኔ 2012 መጨረሻ 112.9 ቢሊዮን ብር መድረሱም ታውቋል፡፡
ኢንሹራንስ ኩባንያዎች
አንድ አዲስ የኢንሹራንስ ካምፓኒ ወደ ኢንዱስትሪው የተቀላቀለ በመሆኑ የመድን ሰጪ ተቋማን ቁጥርን 18 አድርሶታል፡፡ 37 አዳዲስ ቅርጫፎች መከፈታቸውንም ተከትሎ የቅርንጫፎቻቸውን ቁጥር 605 አድርሶታል፡፡
54.4 በመቶ የሚሆነው የመድን ሰጪ ቅርንጫፎች መቀመጫ አዲስ አበባ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 85.31 በመቶው የግል መድን ሰጪ ተቋማት ቅርንጫፎች ናቸው፡፡ የመድን ሰጪ ተቋማት አጠቃይ ካፒታል በ17.9 በመቶ አድጎ 9.7 ቢሊዮን ብር ስለመድረሱ የሚያመለክተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋዊ መረጃ፣ ከዚሁም 70.7 በመቶው የግል መድን ሰጪዎች ድርሻ ሆኗል፡፡ ለቀሪው 29.7 በመቶ ድርሻ የመንግሥት ይዞታ በሆነው መድን ሰጪ ድርጅት የተያዘ ነው፡፡
ማክሮ ፋይናንስ ተቋማትና አምስቱ ግዙፍ ተቋማት
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውሰጥ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በመድረስ የሚታወቁ የጥቃቅንና አነስተኛ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ዓመታዊ ክንውናቸው በዚህ ሪፖርት ተለይቶ ቀርቧል፡፡
በዚህም መሠረት የጥቃቅንና አነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ቁጥር በ2012 መጨረሻ 41 የደረሱ ሲሆን፣ ጠቅላላ ካፒታላቸው በ17.3 ዕድገት አሳይቷል፡፡ 19.4 ቢሊዮን ብር ሲደርስ ጠቅላላ ሀብታቸው በ10.5 በመቶ ዕድገት አሳይቶ 92.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የቁጠባ መጠናቸው በ6.7 በመቶ አድጎ 44.7 ቢሊዮን ብር ሲደርስ፣ ተሰብሳቢ ብድራቸውም በ10.5 በመቶ አድጎ 64.9 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ አምስቱ ግዙፍ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ተብለው የሚጠቀሱት አማራ፣ ደደቢት፣ ኦሮሚያ፣ ኦሞና አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ከዘርፉ አጠቃላይ የካፒታል መጠን 82.6 በመቶውን ሲይዙ 41ዱ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ካሰባሰቡት ጠቅላላ ቁጠባ ውስጥ እነዚህ አምስቱ ትልልቅ ተቋማት 90.1 በመቶ የሚሆነውን ቁጠባ የያዙ ናቸው፡፡ ከብድር አንፃርም እነዚህ አምስት ተቋማት 85.9 በመቶም ይይዛሉ፡፡ እንዲሁም ማክሮ ፋይናንስ ካላቸው ሀብት 86.3 በመቶ የሚሆነውም የአምስቱ ትልልቅ ተቋማት ይዞታ ነው፡፡