የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በአዲስ አበባ ከተማ በነበረው ቆይታ ከስድስት ወራት ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ብር ማሰባሰቡን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የህዳሴ ግድቡ ዋንጫ የአሸኛኘት መርሐ ግብር ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲከናወን ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፣ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ ከአዲስ አበባ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡ ዋንጫው በከተማዪቱ በነበረው ቆይታም በመንፈቅ ውስጥ ብቻ ሁለት ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንም ገልጸዋል፡፡
ዋንጫው በሁሉም ክፍላተ ከተማና ወረዳዎች ሲዘዋወር የተገኘው ገቢ ከቦንድ ግዥና ከስጦታ መሆኑ ታውቋል፡፡
ምክትል ከንቲባዋ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ ‹‹ማደሪያ ላልነበረው ዓባይ ማደሪያውን ላበጃችሁ፣ ከታሪክ ተናጋሪነት ወደ ታሪክ ሠሪነት ላሸጋገራችሁን፣ በዓለም አደባባይ ለዓባይ ሞግታችሁ፣ የጉባ በረሃ ንዳድን ተቋቁማችሁ፣ በክብር ከዚህ መድረክ ላይ እንድንቆም ላበቃችሁን ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ከልብ የሆነ ምስጋናን አቀርባለሁ፤›› ብለዋል፡፡
የተጀመረውን ጉዞ ከግብ ለማድረስም ያሉትን አንጡራ ሀብቶች ለመጠቀምና ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ሁሉም ሰው ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡
‹‹ዓባይ ስም ብቻ አይደለም፣ አሻጋሪ ሐሳብም ነው፡፡ ዓባይ ብርሃን ብቻም አይደለም፣ ምግብም ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ ‹እራትም መብራትም የምንለው፤›› ሲሉ ያስገነዘቡት፡፡
ዋንጫው፣ ሰዎች የህዳሴ ግድቡን የዕለት ተዕለት አጀንዳቸው እንዲሆን ያስቻለና በርካቶችም በግድቡ ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ዕድል የፈጠረ መሆኑን የተናገሩት፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን ከአዲስ አበባ ከንቲባ የተረከቡት የቀጣይ ተረኞች ሐረሪ ክልልና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተወካዮች ናቸው፡፡